ማንቸስተር ዩናይትድ ከቼልሲ - ማን ያሸንፋል? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን ያሰናበተው ማንቸስተር ዩናይትድ በካራባዎ ዋንጫ በሜዳው ሌስተር ሲቲን አስተናግዶ 5 - 2 ረምርሟል። የዩናይትድ ተጫዋቾች ይህን አቋማቸውን እሑድ ከቼልሲ ጋር ሲገናኙ ይደግሙት ይሆን?
“ኤሪክ ቴን ሃግ ስለተሰናበቱ ብቻ ዩናይትድ በውጤት ላይ ውጤት ይደራርባል የሚል ግምት የለኝም” ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።
“ከሌስተር ጋር የነበረው ጨዋታ ሁሌም አሠልጣኝ ሲሰናበት ክለቦች ላይ የሚታየው መነቃቃት ውጤት ነው” የሚል እምነት አለው።
ሱተን 380 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ውጤት ገምቷል። በ10ኛው ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎችን ውጤትም እነሆ እንዲህ ገምቷል።

ቅዳሜ
ኒውካስል ከአርሰናል
ባለፈው የውድድር ዓመት አርሰናል ወደ ኒውካስል ሜዳ መጥቶ በአጨቃጫቂ ሁኔታ መሸነፉ ይታወሳል። የአርሰናል ተጫዋቾች ቁጭት ውስጥ ናቸው ብዬ አስባለሁ።
ኒውካስል ባለፉት አምስት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም። ነገር ግን በእነዚህ ጨዋታዎች ለጎል የሚሆኑ ኳሶች ማግኘት ችለው ነበር።
የአርሰናል የአጥቂ መስመር ጉዳይም ያሳስበኛል። አንዳንድ ጊዜ የሚያገኟቸውን ዕድሎች ሲያባክኑ አስተውያለሁ።
መድፈኞቹ የሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ ጥሏቸው እንዳይሄድ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት አለባቸው። ነገር ግን ውስጤ የሚነግረኝ ውጤቱ አቻ እንደሚሆን ነው።
ግምት፡ 1 - 1
ውጤት፡ 1 - 0
ኢፕስዊች ከሌስተር
ባለፈው ሳምንት ከዚህ በኋላ ኢፕስዊች ያሸንፋል የሚል ግምት አላስቀምጥም ብዬ ነበር። ሐሳቤን ቀይሬአለሁ።
ከብሬንትፈርድ ጋር በነበራቸው ጨዋታ አንድ ተጫዋች በቀይ ተሰናብቶባቸው 3 - 2 እየተመሩ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ነገር ግን በስተመጨረሻ ያለምንም ነጥብ ከሜዳ ወጥተዋል።
ሌስተርም ያሸንፋል ብዬ አልገምትም። ኢፕስዊች ይህን ጨዋታ ካላሸነፉ እንዴት እንደሚቀጥሉ አላውቅም።
ግምት፡ 2 - 1
ውጤት፡ 1 - 1

ቦርንመዝ ከማን ሲቲ
ይህም ለመገመት የሚከብድ ጨዋታ ነው። የማንቸስተር ሲቲ አቋም አምና እንደምናውቀው አይደለም። ቢሆንም ግጥሚያዎቻቸውን በድል እየተወጡ ነው።
ይህ ጨዋታ ለሲቲ ቀላል ይሆናል ብዬ አላምንም። ሲቲ የተወሰኑ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት አጥቷል። ነገር ግን ሲቲ መሰል ጨዋታዎችን በድል መወጣት ያውቅበታል።
ቦርንመዝ ጎል ያስቆጥራል የሚል ግምት ቢኖረኝም ሲቲ ያሸንፋል እላለሁ። ቦርንመዝ ልክ ከአርሰናል ጋር እንደነበረው ጨዋታ በማጥቃት እንደሚጫወቱ እገምታለሁ። ይህ አጨዋወት ደግሞ ለሲቲ የተመቸ ነው።
ግምት፡ 1 - 2
ውጤት፡ 2 - 1
ሊቨርፑል ከብራይተን
ብራይተን መልካም ሳምንት አላሳለፈም። ባለፈው የሊጉ ጨዋታ በ93ኛው ደቂቃ በተቆጠረበት ጎል 1 አቻ ተለያይቷል። በካራባዎ ዋንጫ ደግሞ በሜዳው በሊቨርፑል ተሸንፏል።
ወደ አንፊልድ መጓዝ ከባድ ነው። ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ነገር ግን ይህን ጨዋታ አቻ ይለያያሉ ብዬ አላስብም።
እርግጥ ነው ብራይተን ቁጭ ብሎ የሚመለከት ቡድን አይደለም። ቢሆንም ሊቨርፑል ይህን ጨዋታ እንደሚረታ አልጠራጠርም።
ግምት፡ 2 - 0
ውጤት፡ 2 - 1
ኖቲንግሃም ፎረስት ከዌስት ሃም
ዌስት ሃም ባለፈው ሳምንት ዩናይትድን አስተናግደው ማሸነፍ ቢችሉም 3 ነጥብ በማግኘታቸው ዕድለኛ ናቸው እላለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ አከራካሪ ፍፁም ቅጣት ከማግኘታቸውም በላይ ዩናይትድ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ኳስ ማባከኑን ተመልክተናል።
በተቃራኒው ኖቲንግሃም ፎረስት ዘንድሮ ጥሩ ብቃት እያሳዩ ነው። የፎረስቱ ክሪስ ዉድ በፕሪሚዬር ሊጉ ካልተዘመረላቸው አጥቂዎች አንዱ ነው። ዉድ ያስቆጥራል፤ ፎረስትም ያሸንፋል ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ውጤት፡ 3 - 0
ሳውዝአምፕተን ከኤቨርተን
ኤቨርተን ባለፈው ሳምንት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል አስቆጥሮ አቻ ተለያይቷል። ጨዋታው 1 - 1 ይጠናቀቃል ብዬ ገምቼ ነበር። አሁንም ግምቴ ተመሳሳይ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች የሚጫወቱት ጨዋታ ያስገርመኛል። ሳውዝአምፕተን ነፃ እግር ኳስ ነው የሚጫወተው፤ ኤቨርተን ደግሞ ቢቆጠርበት እንኳ ተጋድሎ አቻ ከመውጣት ወደ ኋላ የሚል ቡድን አይደለም።
ግምት፡ 1 - 1
ውጤት፡ 1 - 0
ዎልቭስ ከክሪስታል ፓላስ
ዎልቭስ ፕሪሚዬር ሊጉ የከበደው ይመስላል። እርግጥ ነው እስካሁን አንድም ጨዋታ ባያሸንፉም ጥሩ ኳስ እያሳዩን ይገኛሉ።
ዎልቭስ በዚህ ጨዋታ ይሸነፋሉ ብዬ አልገምትም። ጥያቄው ያሸንፉ ይሆን? የሚል ነው። ክሪስታል ፓላስ ባለፈው እሑድ ቶተንሀምን መርታታቸው በራስ መተማመን ይሰጣቸዋል።
ጨዋታው በጠባብ ጎል የሚጠናቀቅ ይመስለኛል። ግምቴ ለዎልቭስ ነው።
ግምት፡ 1 - 0
ውጤት፡ 2 - 2

እሑድ
ቶተንሃም ከአስተን ቪላ
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ባልልም አቻ እንኳ ቢሆን በጎል የታጀብ እንደሚሆን አምናለሁ።
የቶተንሃም አጨዋወት ቢያስደስተኝም የተወሰኑ ተጫዋቾቻቸው መጎዳታቸው ምናልባት ውጤት ሊያሳጣቸው ይችላል።
ቶተንሀም በሁሉም ውድድሮች ካለፉት 10 ጨዋታዎች ስምንቱን ማሸነፍ ችለዋል። ነገር ግን በስፐርስ መተማመን ከባድ ነው።
ስፐርስ ኳስ ይዘው ይጫወታሉ ብዬ አስባለሁ። ቪላ ግን ጎል ከማስቆጠር ወደኋላ አይልም። የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ኳስ ከመረብ ለማሳረፍ ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።
ብዙ ግቦች እናያለን። አሸናፊ ማየታችንን ግን አላውቅም።
ግምት፡ 2 - 2
ማንቸስተር ዩናይትድ ከቼልሲ
ሩበን አሞሪም አዲሱ የማንቸስተር ዩናይድ አሠልጣኝ መሆኑ የተረጋገጠ ይመስላል። ነገር ግን ወደ ኦልድ ትራፈርድ የሚመጣው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው።
እስከዚያው ሩድ ቫን ኒስትልሮይ ቡድኑን ይዞ ይቆያል። በሳምንቱ አጋማሽ በካራባዎ ዋንጫ ከሌስተር ጋር የነበረውን ጨዋታ በድል አጠናቋል።
ቼልሲ በካራባዎ ጨዋታ በኒውካስል ተሸንፎ ቢሰናበትም ያሰለፋቸው ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቋሚ የፕሪሚዬር ሊግ ተሰላፊ አይደሉም። ይህ ደግሞ ዋናዎቹ ተጫዋቾች እንዲያርፉ ዕድል ይሰጣል።
ቼልሲ በቅርቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ወደ ፊት ገፍቶ ከመጫወት የሚመለስ ቡድን ሆኖ አላገኘሁትም።
ውስጤ የሚነግረኝ ቼልሲ ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ነው። ነገር ግን ቼልሲ መከላከል ካልቻለ ለዩናይትድ የሚመች ነው ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ሰኞ
ፉልሃም ከብሬንትፈርድ
ፉልሃም ይህን ጨዋታ ያሽንፋል ብዬ አስብ ነበር። ነገር ግን ብሬንትፈርድ ወደ ክራቨን ኮቴጅ ሲመጣ የሚያስመዘግበውን ውጤት ስመለከት ግምቴን ተጠራጠርኩት።
ከ1990 ጀምሮ በፉልሃም ሜዳ 12 ጨዋታዎች አድርገዋል። በስድስት ጨዋታዎች ድል ሲቀናቸው፤ አምስት ጊዜ አቻ ወጥተው አንድ ጊዜ ተሸንፈዋል።
ያም ሆነ ይህ ውስጤን አምነዋለሁ። ፉልሃም አጨዋወታቸው ግሩም ነው። በዚህኛውም ጨዋታ ድል ይቀናቸዋል እላለሁ።
ግምት፡ 2 - 1












