የተመድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል የፍልስጤም ግዛቶችን መውረሯ ሕገወጥ ነው ሲል ፈረጀ

የእስራኤል ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል የፍልስጤም ግዛቶችን በኃይል መውረሯ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጻረር ነው ሲል ፈረጀ።

እስራኤል በኃይል በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እያደረገች ያለውን የሰፈራም እንድታቆም እና በእነዚህ አካባቢዎች እና በጋዛ ውስጥ የምትካሂደውን ሕገወጥ ወረራ በአስቸኳይ እንድታቆም ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ብያኔውን አስተላልፏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት ምላሽ የፍርድ ቤቱን ብይን “ሐሰተኛ ውሳኔ “ ሲሉ ተችተውታል።

የፍርድ ቤቱ ብያኔ በሕጋዊ መንገድ ተፈጻሚ የመሆን አስገዳጅነት ባይኖረውም ጉልህ የሆነ ፖለቲካዊ ጫናን መፍጠሩ አይቀርም።

ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል ለ57 ዓመታት በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ላይ ሕጋዊነትን በተመለከተ አቋሙን ሲያሳውቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መቀመጫውን በኔዘርላንድ ዘ ሄግ ያደረገው ፍርድ ቤቱ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በኩል የቀረበለትን ይህንን ጉዳይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲመረምር ቆይቷል።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትከተላቸውን ፖሊሲዎች እንዲሁም ስለያዘቻቸው ግዛቶች ሕጋዊ ሁኔታ አስተያየቱን እንዲሰጥ ነበር በጉባኤው የተጠየቀው።

የፍርድ ቤቱን ግኝቶች ያቀረቡት ፕሬዚዳንቱ ናዋፍ ሳላም “እስራኤል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች መቆየቷ ሕገወጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“የእስራኤል መንግሥት በፍልስጤም በሕገወጥ መንገድ የያዛቸውን ይዞታዎች በተቻለ ፍጥነት የመልቀቅ ግዴታ አለበት” ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2005 እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ መውጣቷን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ይህ ግን የእስራኤልን ወረራን ያስቆመ አይደለም ምክንያቱም አሁንም በተለየ መንገድ ግዛቱ በቁጥጥሯ ስር ነው ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም እስራኤል ሰፋሪዎቿን ከዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እንድታስወጣ እና በወረራዋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ፍልስጤማውያንም ካሳ መክፍል አለባት ብሏል።

እስራኤል ከአውሮፓውያኑ 1967 ጀምሮ በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌም ለ700 ሺህ የሚጠጉ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች።

ፍርድ ቤቱ ሰፈራዎቹ ሕገወጥ ናቸው ያለ ሲሆን፣ እስራኤል በበኩሏ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር አይቃረንም ስትል ትከራከራለች።

እስራኤል በሰፊው የተቆጣጠረቻቸውን የፍልስጤም ግዛቶች “የመጠቅለል ፖሊሲ እና አሰራር” እየተከተለች ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ።

ይህም የዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጻረር እንደሆነም ጠቅሶ እስራኤል በተያዙ ግዛቶች የሉዓላዊነት መብት የላትም ብሏል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ተከትሎ የተቆጣጠረችውን ምሥራቃዊ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በመላው ኢየሩሳሌም ሉዓላዊ መብት አለኝ ትላለች።

በተጨማሪም ከተማዋን የማትከፋፈል መዲናዬ ናት የምትል ሲሆን፣ ይህም አቋሟ በበርካታው የዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ሲተችም ይደመጣል።

ፍርድ ቤቱ ከደረሰባቸው ድምዳሜዎች መካከል እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ግዛቶች ውስጥ በፍልስጤማውያን ላይ በሃይማኖት እና በዘር ላይ የተመሠረተ ስልታዊ መድልዎን እየተከተለች ነው ብሏል።

በተጨማሪም እስራኤል የፍልስጤማውያንን የተፈጥሮ ሃብት በሕገወጥ መንገድ በመበዝበዝ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ጥሳለች ብሏል።

ፍርድ ቤቱ አገራት እስራኤል አሁን እያደረገች ያለውን እርምጃ የሚያስቀጥል ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ ወይም ድጋፍ ከማድረግ እንዲቆጠቡም መክሯል።