‘የሆቴል ሩዋንዳ’ፊልም ጀግና ከእስር ተፈቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት በርካቶችን በጀግንነት ህይወታቸውን በማትረፋቸው ‘ሆቴል ሩዋንዳ’ የተባለውን ፊልም ሆሊውድ እንዲሰራ ያነሳሱት የቀድሞው የሆቴል ስራ አስኪያጅ ፖል ሩሴጋቢና ከእስር ተፈቱ።
በሆቴል ሩዋንዳ ላይ ጀግና ተደርገው የተሳሉት ፖል በሩዋንዳዋ ኪጋሊ ታስረው ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት የሩዋንዳ ፍርድ ቤት በሽብር ወንጀል የ25 ዓመታት እስር ፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን በርካቶችም ተችተውት ነበር።
ፖል ከሁለት ዓመት እስር በኋላ ለምን ተፈቱ? ለሚለው የመንግሥት ቃለ አቀባይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የቅጣት ውሳኔው “በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ተቀይሯል” ብለዋል።
የ68 ዓመቱ ፖል ሩሴባጊና በአውሮፓውያኑ 1994 በነበረው የዘር ጭፍጨፋ የ1 ሺህ 200 ሰዎችን ህይወት በማትረፍ ተጠቃሽ ናቸው።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከእስር የመፈታቸውን ዜና “መልካም ውጤት” ብለውታል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም “የፖል ቤተሰቦች በአሜሪካ ለመቀበል በጉጉት እየጠበቁት ነው። እኔም የደስታቸው ተካፋይ ነኝ” ብለዋል በመግለጫቸው።
ፖል ከእስር እንዲፈቱ በኳታር አደራዳሪነት ለዓመታት የፈጀ ውይይት እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተደርጓል።
አብዛኛው ጫና የመጣው ፖል ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ መኖሪያ ካደረጓት ከአሜሪካ ነው።
የባይደን አስተዳደር ፖል “በስህተት ነው የታሰሩት” በማለትም ሲከራከር ቆይቷል።
የፖል ቤተሰቦች የሩዋንዳ መንግሥት በቋሚነት ከሚኖርበት አሜሪካ በ2020 እንዲመለስ አታለውታል ይላሉ።
ፖል ሩዋንዳን ለቀው የወጡት በአውሮፓውያኑ 1996 ነበር።
ታሪካቸውም ለአስር ዓመታት ያህል የማይታወቅ ሲሆን በቤልጂየሟ መዲና ብራስልስ በታክሲ አሽከርካሪነት ይተዳደሩ ነበር።
ጋዜጠኛው ፊሊፕ ጎሬቬች በአውሮፓውያኑ 1998 ስለ ሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በጻፈው መጽሃፉ የፖል ታሪክ ቢካተትም የአለምን ትኩረት የሳበው ግን በአውሮፓውያኑ 2004 የተሰራው ‘ሆቴል ሩዋንዳ’ ፊልም ነበር። ፊልሙ ላይ የፖልን ገጸባሕርይ ወክሎ የተጫወተው ተዋናዩ ዶን ቺያድል ነው።
ከሶስት ዓመት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት ፖል እንደ ደጋፊዎቹ ከሆነ ወደ ብሩንዲ ይወስዳቸዋል የተባለው የግል ጄት ወደ ሩዋንዳ እንደወሰዳቸው ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በሩዋንዳ 2018 እና 2019 ግድያዎች ጥቃቶች ጀርባ ያለውን አማጺ ቡድን በመደገፍ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ከፖል በተጨማሪ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲው የሩዋንዳ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ ቃለ አቀባይ ካሊክስቴ ንሳቢማናም ከእስር ተፈትተዋል።












