በጦርነቱ የቆሰሉ የትግራይ ተዋጊዎች በክልሉ ባለሥልጣናት ችላ ተብለናል ይላሉ

የሕክም እና የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተው የነበሩ የጦር ቁሰለኞች

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA

የምስሉ መግለጫ, የሕክም እና የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተው የነበሩ የጦር ቁሰለኞች

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶሺዎች መሞታቸው እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይነገራል።

ከእነዚህም መካከል ከትግራይ ኃይሎች ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ ጉዳት የደረሰባቸው ቁስለኞች ከጦርነቱ በኋላ የሕክምና እና የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ።

በዚህም ሳቢያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ብሶታቸውን ለማሰማት በመቀለ ከተማ ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ያሉበትን ሁኔታ ሕዝብ እና የክልሉ ባለሥልጣናት እንዲያውቁ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የተለያየ አይነት ጉዳት ደርሶባቸው ድጋፍ ጠባቂ የሆኑት እነዚህ የትግራይ ኃይል ተዋጊዎች፤ ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ ባለሥልጣንት ተዘንግተናል ሲሉ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

በጦርነቱ ቆስለው ድጋፍ ፈላጊ ከሆኑት መካከል አንዱ መድሃኔ ሕሉፍ ነው። መድሃኔ ከእርስ በርስ ጦርነቱ በፊት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የኮንስትራክሽን ምህንድስና መምህር ነበር።

በልጅነቱ የደርግ ሥርዓትን ለመጣል የተደረጉ የጦርነት ታሪኮችን ሲሰማ እንዳደገ የሚናገረው መድሃኔ፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት “በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግፎች የትግራይ ኃይሎችን እንዲቀላቀል ምክንያት ሆነኝ” ይላል።

የቀድሞው የዩኒቨርሲቲ መምህር ከትግራይ ኃይሎች ጎን ተሰልፎ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሠራዊትን ለመዋጋት ብረት ካነሳ በኋላ መስከረም 30/2015 ዓ.ም. ዓዲ ዳዕሮ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ቀኝ እጁን ተመትቶ ነበር የቆሰለው።

የጦርነቱ ተፈላሚዎች ግጭትን በዘላቂነት በማቆም ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ከተስማሙ ከወራት በኋላም መድሃኔ ከጉዳቱ ሳያገግም በትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች ትኩረት መነፈጉን ይናገራል።

“ሕክምና ብሎ ነገር የለም። ከእናቶች በተሰበሰበ ልብስ [ጨርቅ] ቁስልን መጥረግ ብቻ ነው” ሲል ሁኔታው ያስረዳል።

እንደ መድሃኔ ሁሉ አዲ ዳዕሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. በነበረ ውጊያ ጉዳት የደረሰበት ታደለ ተከስተ፣ መቀለ ከተማ አቅራቢያ አሪድ ተብሎ በሚጠራ ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ በቂ የሕክምና ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ማዕከሉን ጥሎ ወጥቶ በግሉ መታከሙን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።

የትግራይ ኃይሎች የነበሩት የጦር ጉዳተኞቹ ካሉበት ሁኔታ አንጻር በቂ ሕክምና እና ምግብ አላገኘንም በማለት “ተዘንግተናል” በሚል በተሽከርካሪ ወንበር እና በክራንች ተደግፈው አደባባይ ወጥተዋል።

“ከዚህም በፊት ሃያ እና ሰላሳ ሆነን ቅሬታችን እናሰማ ነበር” ያለው መድሃኔ የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት ወደ መቀለ ከተማ ባመሩበት ወቅት ፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ሊበትኗቸው ሞክረው እንደነበረ ያስታውሳል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እነዚህን የጦር ጉዳተኞች አነጋግረውና ይቅርታ ጠይቀው ጥያቄያቸው በቅርቡ እንደሚመለስ በመግለጽ እንዳሰናበቷቸው በተደረገው ውይይት ተሳታፊ የሆነበሩ የጦር ጉዳተኖች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመድኃኒት እና የምግብ እጦት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ታደለ በነበረበት ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ “ለስሙ ሕክምና አለ፤ ነገር ግን መድኃኒት እና ምግብ የለም” ይላል።

ታደለ እና መድሃኔ “በእርዳታ ለመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰጡ መድኃኒቶች በሕገ-ወጥ መንገድ በግል መድኃኒት ቤቶች ይሸጣሉ” የሚል ቅሬታ በጦር ጉዳተኞቹ ዘንድ አለ ይላሉ።

ታደለ “አብዛኞቹ መድኃኒቶች በግል መድኃኒት ቤቶች ነው የሚገኙት። ፋርማሲዎቹ ታዲያ ከየት ነው መድኃኒቱን የሚያመጡት?” በማለት ይጠይቃል።

መድሃኔ ደግሞ “ለምሳሌ በመገጣጠሚዬ ውስጥ የሚገቡ ትናንሽ ብረቶች አሉ። በሆስፒታል ውስጥ እንደሌለ ተነገረኝ። ነገር ግን በግል መድኃኒት ቤት ውስጥ አግኝቻለሁ” ይላል።

የመድሃኔ እና ታደለን ጥርጣሬ እውነታነት የሚያጠናክሩት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በአይደር ሆስፒታል የጤና ባለሙያ የሆኑ ሐኪም ናቸው።

እኒህ ሐኪም ከዓለም ጤና ድርጅት በእርዳታ ለሆስፒታሉ የተላኩ መድኃኒቶች “በሕገ-ወጥ መንገድ ሆስፒታል ሳይደርሱ ወይም ከሆስፒታል እንዲወጡ እየተደገ በግል መድኃኒት ቤቶች እንዲሸጡ እየተደረጉ ነው” ይላሉ።

“ሁኔታውን ተጠቅመው ለመበልጸግ የሚንቀሳቀሱ በጣም ብዙ ናቸው። ይህ እውነት ነው። ይህንን ሁኔታ ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሰው ሁሉ ያውቃል” በማለት በሆስፒታሎች እና በጤና ጣቢያዎች የማይገኙ መድኃኒቶች በግል መድኃኒት ቤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ የአይደር ሆስፒታል አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ታደለ ክልሉ ከእርስ በእርስ ጦርነቱ ገና አለማገገሙን እንዲሁም አስተዳደሩ አዲስ መሆኑን እንደሚረዳ በመጥቀስ፤ “የታገልኩለትን አላማ አውቃለሁ። ለምን ቆሰልኩ አልልም። ነገር ግን የደረሰብኝ ጉዳት ተጠግኖ ምግብ ሊሰጠኝ ግን ይገባል” ትኩረት እንዲደረግላቸው ጠይቋል።