በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተጫዋቿን ያለፈቃዷ የሳሙት የቀድሞው የስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የስፔን የቀድሞ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሊዊስ ሩቤለስ በሴቶች ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ እግር ኳስ ተጫዋቿን ጄኒ ሄርሞሶን ያለ ፈቃዷ በመሳም ጥፋተኛ ተባሉ።
በፆታዊ ጥቃት ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ጥፋተኛ ያላቸው የስፔን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10 ሺህ ዩሮ እንዲቀጡ ወስኗል።
አቃቢያነ ሕግ ግለሰቡ እስራት እንዲፈረድባቸው ሀሳብ አቅርበው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2023 ዓለም ዋንጫ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን ማሸነፏን ተከትሎ በተደረገ የሜዳሊያ ስነ ስርዓት ላይ ሩቢሌስ ተጨዋቿን በመጎተት ከንፈሯን መሳማቸው ውዝግብ ፈጥሮ ነበር።
ድርጊቱ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን የእግር ኳስ ፕሬዝዳንቱ ከስራቸው እንዲሰናበቱ ጥሪዎች ቀርበዋል።
ሩቢሌስ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨዋቿን ከመሳማቸው በፊት ፈቃዷን ስለማግኘታቸው "ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ" ነኝ ብለዋል።
ድርጊታቸውን ፍቅራቸውን የገለፁበት መንገድ አድርገው የገለፁት ሊዊስ ሩቤለስ፤ አስበውበት ሳይሆን በቅፅበታዊ ስሜት ያደረጉት እንደሆነ ተናግረዋል።
እግር ኳስ ተጨዋቿ ባለፈው ወር ለቀድሞው የእግር ኳስ መሪ እንዲስሟት ፈቃድ እንዳልሰጠች እና ሁነቱ "በሕይወቴ እጅግ ደስተኛዋን ቀን ጥላሸት ቀብቷል" በማለት ቃሏን ሰጥታለች።
ሊዊስ ሩቤለስ ተጫዋቿን 'በፈቃዴ ነው' እንድትል ጫና በማድረግም ተከሰው የነበረ ቢሆንም፤ ከዚህ ክስ ነፃ ሆነዋል።
የስፔን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የ2023 ዓለም ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ድርጊቱን ሚሊዮኖች በቴሌቪዥን መስኮት እንዲሁም በስታዲየም ሙሉ ታዳሚዎች ተመልክተውታል።
ድርጊቱ "ሚ ቱ" የተባለውን የሴቶች የመብት ንቅናቄ በስፔን የሴቶች ስፖርት ላይ ያቀጣጠለ ሲሆን፤ ተጨዋቾቹም በፆታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን አድልዎ እንዲታገሉ እድል ሰጥቷል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ከአባልነታቸው ካሰናበታቸው እና የስፔን አቃቤ ሕግ ምርመራ ከከፈተ በኋላ ለሳምንታት ስራቸውን አልለቅም ሲሉ የቆዩት ሊዊስ ሩቤለስ እ.አ.አ መስከረም 2023 ከኃላፊነታቸው ለቀዋል።
ከእርሳቸው ጋር ሌሎች ሦስት የቀድሞ ባልደረቦቻቸው የተጨዋቿን ምስክርነት ለማስቀየር ጫና በማድረግ ተከሰው የነበረ ሲሆን፤ ከክሱ በነፃ ተሰናብተዋል።












