አሜሪካ በሩሲያ ላይ 500 አዳዲስ ማዕቀቦችን እንደምትጥል አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን በፈጸመችው ወረራ እንዲሁም በቅርቡ እስር ቤት ሞቶ በተገኘው ተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ጋር በተያያዘ ከ500 በላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን እንደምትጥል አስታወቀች።
እነዚህ ማዕቀቦች በሩሲያ ዋነኛ የካርድ የክፍያ ሥርዓት፣ በፋይናንስ እና ወታደራዊ ተቋማት እንዲሁም በናቫልኒ እስራት ውስጥ የተሳተፉ ባለስልጣናት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካትታል ተብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ ከወታደራዊ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲንን በሰላ በመተቸት የሚታወቀው ናቫልኒ በታሰረበት አርክቲክ ሰርክል ከሞተ ከአንድ ሳምንት በኋላም ነው ምዕራባውያኑ አዳዲስ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ያስታወቁት።
ሐሙስ ዕለት በሳንፍራንሲስኮ የናቫልኒ ባለቤት እና ልጃቸውን ያገኙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለተቃዋሚው ሞት ተጠያቂው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ስለመሆናቸው “ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።
አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለቻቸው አዳዲስ ማዕቀቦች ወደ 100 የሚጠጉ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦችን ያጠቃልላል።
የካርድ የክፍያ ሥርዓት የሆኑት ቪዛ እና ማስተርካርድ በሩሲያ አገልግሎታቸውን ማቋረጣቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የካርድ ክፍያ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን ሚር የተሰኘውንም ይህ ማዕቀብ ዒላማ አድርጎታል።
የሩሲያን የጦርነት አቅም በማጎልበት፣ የአገሪቱን የኃይል ምርት በመደገፍ አስተዋፅኦ ያላቸው እንዲሁም ከኢራን ጋር ድሮኖችን በትብብር የሚሰሩ ኩባንያዎች ማዕቀቡ ይጣልባቸዋል ተብሏል።
ከሩሲያ ውጭም ያሉ በቻይና፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በቬትናም እና በሌችተንስታይን ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ቁሳቁሶችን ወደ ሩሲያ ጦር ከሚልኩ የንግድ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የማዕቀቡ ኢላማ ተደርገዋል።
ማዕቀቡ በሩሲያ ምጣኔ ኃብት ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ሩሲያ ቀድሞውኑ በምዕራባውያኑ ከፍተኛ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ስትሆን በአሜሪካ እና በአውሮፓ እገዳ ያልተደረገባቸው የንግድ ዘርፎች በጣም ጥቂት ናቸው።
የሩሲያ ባንኮች እና ወታደራዊ ኢንተርፕራይዞች ማዕቀቦቹን ለማምለጥ የተለያዩ መንገዶችንም አዘጋጅተዋል ተብሏል።
የዩክሬን ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ባዋሏቸው የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ውስጥ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ስሪት የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማግኘታቸውን ገልጸው ዝርዝሩን ይፋ አድርገዋል። አብዛኛዎቹ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከቻይና በኩል ወደ ሩሲያ የሚላኩ ናቸውም ተብሏል።












