አሜሪካዊው ሹፌር ትራፊክ እንዳይቀጣው መኪናውን ‘የነዳው’ ውሻዬ ነው አለ

መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ፣ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ በፍጥነት እያሽከረከረ የነበረው ግለሰብ በትራፊክ ሲያዝ ውሻውን ወደ ሹፌር መቀመጫ በማዘዋወር አስቀምጦ ከእስር ለማምለጥ ሞከረ።

ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ በማሽከርከሩ ትራፊክ አሽከርካሪውን ሲያስቆም የሹፌር ወንበር ላይ የግለሰቡ ውሻ ተቀምጦ አግኝቷል።

ግለሰቡ በፖሊስ የተያዘው በሰዓት 30 ኪሎሜትር ፍጥነት የሚነዳበት መንገድ ላይ 52 ፍጥነት ሲያሽከረክ ተገኝቶ ነው።

አሽከርካሪው በፖሊስ እንዲቆም በተደረገበት ጊዜ አልኮል ጠጥቶ እንደነበር ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ ገልጿል።

“ሹፌሩ ውሻውን ወደ አሽከርካሪው መቀመጫ አሸጋግሮ ቦታ ተለዋውጦት ነበር። ይህንንም ሲያደርግ ፖሊስ በቅርብ ርቀት ይከታተል ነበር” ሲልም መግለጫው አትቷል።

በተጨማሪም ሹፌሩ በፖሊስ በተያዘበት ጊዜ መኪናውን እሱ እየነዳ እንዳልነበረ ክዷል።

‘መጠጥ ጠጥተህ ነበር?’ ተብሎ በትራፊክ ፖሊስ ሲጠየቅ ደግሞ በሩጫ ከአካባቢው ለማምለጥ መሞከሩም ተገልጿል።

ሆኖም ግን ከፖሊስ ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ብዙ ርቀት መጓዝ ሳይችል ቀርቷል።

ጥቂት ከሮጠ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደዋለ ተገልጿል።

ግለሰቡ ለፈጸመው ደንብ የመተላለፍ ጥፋት መጠጥ ጠጥቶ በማሽከርከር በፖሊስ ተከሷል።

በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላም፣ መኪናውን አሽከርክሯል የተባለው ውሻ ለሹፌሩ የቅርብ ሰው ተሰጥቷል።

“ውሻው አይከሰስም። ማስጠንቀቂያ ግን ሰጥተነዋል” ሲል የፖሊስ ክፍሉ የስላቅ መልስ ሰጥቷል።