ምባፔ ካሜሮንን በመጎብኘቱ ክብር እንደተሰማው ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፈረንሳዩ የእግር ኳስ ኮከብ ካይሊያን ምባፔ የአባቱ የትውልድ ስፍራ የሆነችውን ካሜሮንን በመጎብኘቱ ክብር እንደተሰማው ተናገረ።
“እዚህች ስፍራ በመገኘቴ” በጣም ደስተኛ ነኝ ብሏል ምባፔ።
የአገሬው ሰው ከፍተኛ ፍቅርም እንዳሳየውም ነው የተናገረው።
ምባፔ ካሜሮን ከመድረሱ በፊት ቢቢሲ ያናገራቸው የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በምባፔ ጉዞ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
“ሁላችንም ይህችን ቀን በጉጉት ስንጠብቃት ነበር። በመጨረሻም ደረሰች” በማለት አንድ የእግር ኳስ ተጫዋቹ አድናቂ ለቢቢሲ ኒውስደይ የሬድዮ ፕሮግራም ተናግሯል።
“ለካሜሮን ብቻ ሳይሆን ለመላው አህጉሪቷ ትልቅ ኩራት ነው” ሲል ይህ ደጋፊ አክሏል።
“የምባፔ ወደ ካሜሮን መምጣት የሚያሳየው መቼም ቢሆን አገርህ አገርህ ናት። በመጨረሻም ወደ ቤትህ መመለስ አለብህ” ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
የ24 ዓመቱ ፈረንሳያዊ የእግር ኳስ አምበል እና የፒኤስጂ አጥቂ ምባፔ ትውልዱ በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አባቱ ካሜሮናዊ እንዲሁም እናቱ አልጀሪያዊ ናቸው።
ምባፔ በካሜሮን ቆይታውም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ንጉቴን ጨምሮ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቷል።
ምባፔ ታዳጊ ከሆነ በኋላ ካሜሮንን ሲጎበኝ ይህ የመጀመሪያው ነው።
አለም አቀፉ የስፖርት ኮከብ ከባለስልጣናቱ በተጨማሪ ከሌሎች ታዋቂ እንደ ፍራንሲስ ንጋንኑ የካሜሮን የስፖርት ኮከቦች ጋር መገናኘቱን የሚያሳዩ ፎቶዎችም ወጥተዋል።
ከቺካጎ ቡልስ የቅርጫት ኳስ ክለብ ኮከብ ተጫዋች ጆ አኪም ኖሃም ጋር በኖሃ አደባባይ በበርካታ ታዳሚዎች ተከቦ ቅርጫት ኳስ ሲጫወትም ታይቷል። በኋላም ከካሜሮን ቡድን ቬንት ዲ ኢቱዲ የእግር ኳስ ክለብ በተቃራኒ ጎራ በመሆን እግር ኳስ መጫወቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ምባፔ በዚህ ጉዞው ለሰብዓዊ እርዳታ የተቋቋመ ፋውንዴሽኑን በመወከል የሰብዓዊ ስራዎችን እያከናወነ ነው። ወጣቶች ግባቸውን እንዲያሳኩ ለመርዳት ያለመም እንደሆነም ተገልጿል።












