በጌዴኦ ዞን በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች 26 ሰዎች መሞታቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Gedeo Zone Government Communication
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ባለፈው ሳምንት በተከታታይ ቀናት በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የ26 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአደጋው የሞቱ 15 ሰዎች አስከሬን እስካሁን ድረስ ባይገኝም በአከባቢው በድጋሚ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ምክንያት ፍለጋው እንዲቆም መደረጉንም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በጌዴኦ ዞን በሚገኙት ራጴ እና ቡሌ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የደረሱት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 20 እና በማግሥቱ ረቡዕ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም. ነው።
የማክሰኞ ዕለቱ የራጴ ወረዳ አደጋ የተከሰተው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ እንደነበር ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ጫራቃ እና ሀሮ በተባሉ ቀበሌዎች በደረሰው በዚህ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰባት ሰዎችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።
የመጀመሪያው የመሬት መንሸራተት ከማጋጠሙ አስቀድሞ በነበሩት ሁለት ቀናት ተከታታይ ከባድ ዝናብ እንደነበር አደጋው በደረሰበትም ሌሊትም በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እንደጣለ ተገልጿል።
ዋና አስተዳዳሪው ዶ/ር ዝናቡ እንደሚናገሩት፤ በማግስቱ ረቡዕ ዕለት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ሁለተኛ አደጋ የደረሰው አጎራባች በሆነው ቡሌ ወረዳ በሚገኘው አጋምሳ ቀበሌ ነው።
"ቡሌ ወረዳ ላይ [የመሬት መንሸራተት] የደረሰው ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ምንም ባልተጠበቀ ሰዓት ላይ ነው" ሲሉ ከዚህ ቀደም "በአካባቢው ይህ አይነቱ አደጋ ደርሶ የማያውቅ መሆኑ" ነዋሪዎች እንዳይገምቱ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Gedeo Zone Government Communication
በዚህ አደጋ 17 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የሚገልጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ ከእነዚህ ውስጥ አስከሬናቸው የተገኘው የሁለቱ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ያልተገኙት 15 ሰዎች በመሬት ናዳው መቀበራቸው የታወቀው ከአደጋው የተረፉ የቤተሰብ አባሎቻቸው በማስመዝገባቸው እንደሆነ ዶ/ር ዝናቡ አስረድተዋል።
"[አደጋው ከደረሰበት ቦታ] ቀጥሎ ባለ ማሳ ላይ የነበሩ የተረፉ ሰዎች አሉ። ዝርዝራቸውን ማግኘት የተቻለው ከእነዚህ ከተረፉት ነው" ብለዋል። የቤተሰብ አባላቱ "እርማቸው እያወጡ" መሆኑንም አክለዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት በመሬት ዳናው ተቀብረዋል የተባሉትን 15 ሰዎች የመፈለግ ስራው እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቅሰዋል።
እንደ ዶ/ር ዝናቡ ገለጻ ይህ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ የተደረገው አከባቢው ላይ "የሰው እንቅስቃሴ የሚበዛ ከሆነ" መሬቱ በድጋሚ ሊናድ ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Gedeo Zone Government Communication
"መሬቱ የተቆረጠበት ቦታ ከ30 ሜትር የማይተናነስ ነው። ቦታው ላይ ያለው ተንሸራትቶ የመጣ አፈር ስለሆነ አሁንም አካባቢው ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ (turbulence) የሚበዛ ከሆነ፣ የሰው ቁጥር የሚበዛ ከሆነ አሁንም የመናድ እድል አለው" ሲሉ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረበትን ምክንያት ገልጸዋል።
"የነበረው አማራጭ ሰዉን ከአካባቢው ማስወጣት" እንደነበር የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ "ከፍተኛ ስጋት ያለበት ቦታ ስለሆነ ሰው ወደዚያ እንዳይሄድ" መደረጉንም ጠቅሰዋል። "ቦታው እንኳ ለማሽን ለሰውም አስቸጋሪ ነው" ሲሉም ፍለጋውን ለመቀጠል አለመቻሉን አክለዋል።
ዶ/ር ዝናቡ፤ አደጋ በደረሰባቸው ሁለት ወረዳዎች የሚገኙ አራት ሺህ ገደማ ነዋሪዎችም ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲዘዋወሩ መደረጉንም ተናግረዋል።
ከረጲ ወረዳ የተፈናቀሉት ነዋሪዎች ያረፉት በአካበቢው በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የቡሌ ወረዳ ተፈናቃዎች ደግሞ "ባዶ ቦታ ላይ ድንኳን ተተክሎ" እንዲያርፉ መደረጉን ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምን አደጋ ከደረሰባቸው የራጴ እና ቡሌ ወረዳዎች አካባቢዎች በተጨማሪ በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኙ ሌሎች 13 ቀበሌዎችም የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥም የሚችልባቸው "ተጋላጭ አካባቢዎች" ተብለው እንደተለዩ አስረድተዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪው ዶ/ር ዝናቡ፤ "ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለያዩ ምልክቶች አሉ። የመሬት መሰነጣጠቅ ባህሪ እያሳየ ነው። እነዚህ መሰነጣጠቅ ባህሪ እየታየባቸው ባሉ አካበቢዎች ከፍተኛ ገደልም ያለበትም ስለሆነ ባለሙያ እየገባ ህዝቡ እንዲወጣን [ነው]" ሲሉ እየተወሰዱ ያሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን ገልጸዋል።















