ሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃት ደርሷል በሚል ከዩክሬን እህል እንዳይወጣ አዘዘች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደቦች በኩል እህል ወደ ውጭ እንድትልክ የሚያስችላት ዓለም አቀፍ ስምምነት መቋረጡን ሩሲያ አስታወቀች።
ሩሲያ ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት ለመቋረጡ ምክንያት ያለችው ዩክሬን መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት በጥቁር ባሕር መርከቦች ላይ አድርሳለች በሚል ነው።
ይህ ጥቃት የደረሰው በሴባስፖል ክሬሚያ መሆኑም ተነግሯል።
ዩክሬን ጥቃት አድርሳለች የሚለውን ክስ አልቀበለውም ብላለች ።
ይልቁንም ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የሩስያን እርምጃ "የሚጠበቅ ነበር” ብለውታል።
ሩሲያ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባታቀርብም የብሪታንያ ወታደሮች በቅዳሜው ጥቃት እጃቸው አለበት ስትል ከሳለች።
በተጨማሪም ባለፈው ወር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን በማፈንዳት ወንጀል እንዲሁ ዩናይትድ ኪንግደምን ከሳለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር በአጸፋው በሰጠው ምላሽ ሩሲያ “በከፍተኛ መጠን በሐሰት እየሸቀጠች ነው” ሲሉ ወርፈዋታል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው በሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዘው የቅዳሜው ጥቃት በተደረሰው የእህል ስምምነት ጭነት የሚያመላልሱ መርከቦች ላይ ያነጣጠረ ነው።
በዚህም አንድ መርከብ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።
ጥቃቱ ደረሰ ከተባለበት ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ሩሲያ በጥቁር ባሕር ለሚመላለሱ የጭነት መርከቦች ደኅንነት ዋስትና ልትሰጥ አትችልም ስለዚህም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተላልፏል” ብሏል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው “ በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች አመራር የዩክሬን ጦር ኃይል የፈጸመው ጥቃት ጋር” ተያይዞ ነው ሲል አፅንኦት ሰጥቷል።
በዚህም የእህል ጭነት የሚተላለፍበት የሰብአዊ ኮሪደር አሠራሩን በሚቆጣጠሩ የሩሲያ መርከቦች ላይ መሆኑም ተገልጿል።
ሩሲያ 16 የአየር እና የባሕር ላይ ድሮኖች መውደማቸውን ገልጻ ጉዳት የደረሰበት አንድ መርከቧ ብቻ መሆኑንም አስታውቃለች።
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ከዩክሬን እህል መውጣት ቀጥ ብሎ ነበር። ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም ሩሲያ በወደቦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች።
ይህም መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል ባለው መተላላፊያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ አስችሏቸው ነበር።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመዋል።
የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?
- ከኦዴሳ እና ሁለት አጎራባች ወደቦች ወደ ኢስታንቡል የባሕር ዳርቻ መተላለፊያ (ኮሪደር) 310 ማይል የባሕር ርዝመት (357 ማይል) እና ሦስት የባሕር ማይል ስፋት ያለው
- መሣሪያ በተጠመደባቸው የወደብ ውሃ ውስጥ የዩክሬን መርከቦች ወደ ውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ የእህል ጭነት መርከቦችን እንዲያጅቡ
- ጭነቶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምታለች
- የሩሲያ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ስጋት ለማስወገድ ቱርክ መርከቦችን እንድትመረምር
- ሩሲያ በጥቁር ባሕር በኩል እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ መላክ ተፈቅዶላታል
- ስምምነቱ ከ120 ቀናት በኋላ ማለትም በኅዳር አጋማሽ ያበቃል












