ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ቢሮዎች በአንድ ሕንድ-ብሪታኒያዊ ክስ ቀረበባቸው
በፑንጃብ ፖሊስ ተይዞ ሰቆቃ የደረሰበት አንድ ሕንድ-ብሪታኒያዊ ግለሰብ የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ኤጀንሲዎች ለሕንድ ፖሊስ መረጃ በመስጠታቸው ደርሶብኛል ላለው ኢ-ፍትሃዊነት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ክስ አቀረበ።
ጃግታር ሲንግ ጆሃል የተሰኘው ግለሰቡ ዱምባርተን በተሰኘች የሕንድ ከተማ እ.ኤ.አ በ2017 በአንድ የማን እንደሆነ ባልታወቀ መኪና ተጠልፎ መወሰዱን ቤተሰቦቹ ገልጸው ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእስር ላይ የቆየው ግለሰቡ በኤሌክትሪክ ንዝረት የሚፈጸም ማሰቃየትን ጨምሮየተለያዩ ግፎች ተፈጽመውብኛል ሲል ተናግሯል።
ይሀንን ተከትሎም ነበር በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ላይ ክሱን የመሰረተው።
በተለያየ ጊዜ የተተካኩ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ለሕንድ መንግሥት ቢያነሱም የሕንድ ባለሥልጣናት ግን ስቃይ ወይም እንግልት አልደረሰበትም ሲሉ አስተባብለዋል።
ባሳለፍነው ግንቦት ወር ጆሃል ግድያ ለመፈጸም በማሴር እና የአሸባሪ ቡድን አባል በመሆን ወንጀል ተከሷል።
የክሱ ሙሉ ዝርዝር በመጪው መስከረም ወር ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሞት ፍርድ ሊጣልበት ይችላል።
ሪፕሪቭ የተሰኘው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ያዋሉት የብሪታንያ የስለላ መሥሪያ ቤት በሰጠው ጥቆማ አማካኝነት መሆኑን የሚያስረዳ አስተማማኝ ማስረጃ ያለውን ሰነድ ለቢቢሲ አሳይቷል።
የዩኬ መንግሥት በበኩሉ በሂደት ላይ ባለ የሕግ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ ገልጿል።
ሪፕሪቭ የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ከግለሰቡ ጋር የተያያዙ በርካታ ሰነዶችን ማመሳከሩን ገልጿል።
በተለይም የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ መሥሪያ ቤት በሚቆጣጠረው የምርመራ ኃይል ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የወጣው ሰነድ በምስጢራዊ መንገድ መረጃውን ማስተላለፉን ማረጋገጡን ተቋሙ ይገልጻል።
"ግለሰቡ ስቃይ እንደደረሰበት ለብሪታኒያ ባለሥልጣን ተናግሯል" ሲልም ያክላል።
ምንም እንኳን እነዚህ ምጢራዊ ሰነዶች ላይ የጆሃል ስም ባይጠቀስም የሪፕሪቭ መርማሪዎች በተጠቀሱ ቀናት፣ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ያደረጓቸውን ጥረቶች ብሎም የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ያወጧቸውን መረጃዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በርግጥም ሰነዱ የጆሃልን ሁኔታ የሚያስረዳ ነው የሚለውን በጥብቅ ያምናሉ።
የሕንድ ባለሥልጣናት ተከሳሹ ጆሃል ከሲክ ብሔርተኝነት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚሏቸው ግድያዎች ውስጥ እጁ እንዳለበት በመጥቀስ ክስ መስርተዋል። ጆሃል በበኩሉ ምንም ዓይነት ጥፋት አልሰራሁም ሲል ክሱን ውድቅ አድርጓል።
ጆሃል ለሲክ ሕዝብ የሰብአዊ መብት የሚሟገት እና ንቁ ጦማሪ የነበረ ሲሆን ይህ እንቅስቃሴው የሕንድ ባለሥልጣናት ትኩረት ውስጥ እንደከተተው ይነገራል።
ወንድሙ ጉርፕሬት ለቢቢሲ እንደገለፀው ግን ጆሃል ሕገወጥነው ተብሎ የሚታሰብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የለም።
ጆሃል በአሁኑ ጊዜ በደልሂ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል። በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ በድብቅ ታስሮ ለሰዓታት በጭካኔ ሲመረመር መቆየቱን ብሎም ከጠበቆችም ሆነ ከዩኬ ቆንስላ ባለሥልጣናት ጋር እንዳይገናኝ መከልከሉን ገልጿል።
እንዲሁም በባዶ ወረቀት ላይ እንዲፈርም መገደዱን እና ቀጥሎም ይህ በሐሰት የእምነት ቃሉን እንደሰጠ ተደርጎ መቅረቡን ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በዚህ ዓመት በሚያዝያ ወር ወደ ሕንድ ባደረጉት ጉዞ የጆሃልን ጉዳይ ከሕንድ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ ጋር እንዳነሱት ገልጸው ነበር። ከእርሳቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቴሬዛ ሜይም እንዲሁ ጉዳዩን ለሕንድ መንግሥት አንስተው ተወያይተው ነበር።
"የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ መረጃ ልውውጥ ከተፈጸመ ስቃይ ጋር ተያይዞ ስሙ የተነሳበት ይህ አስደንጋጭ ጉዳይ የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ መሻሻል እንዳለበት በግልፅ ያሳያል" ሲሉ የዩኬ የፓርላማ አባል ስቲቭ ቤከር ክሱን አስመልክቶ አስተያየት ሰጥተዋል።
ከስ የቀረበባቸውን ሦስት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ወክሎ ምላሽ የሰጠው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ "በሂደት ላይ ባለ የሕግ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አይደለም" ብሏል።