ውጤቱ ቀስ በቀስ እየታየ ያለው የአጎዋ ተጽእኖ

የ26 ዓመቷ በላይነሽ ቆልቻሞ ዊንሳ ከተንጣለለው የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ተጎራብታ ነው የምትኖረው።

ከአራት ዓመት ከፍ ለሚል ጊዜ ያህል ፓርኩ ለእርሷ እና ለቤተሰቧ ከጎረቤትም በላይ ነበር። የዕለት እንጀራዋን የምታገኘው ፓርኩ ውስጥ ካሉ ሁለት ደርዘን አቅራቢያ ፋብሪካዎች በአንደኛው ተቀጥራ በሚከፈላት 2 ሺህ ሁለት መቶ ብር ነበር።

አሁን የሲዳማ እንዲሁም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች የጋርዮሽ መዲና ሆና እያገለገለች ካለችው ሐዋሳ ወጣ ብለው ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች አንደኛዋ ከሆነችው አለታ ጭኮ መነሻዋን የምትመዝዘው በላይነሽ፣ በፋብሪካው ከመቀጠሯ በፊት ምንም ሙያዊ ትምህርት ያልነበራት እና በየዕለቱ የጉልበት ሥራን በማሳደድ ራሷን ልትደጉም የምትደክም ባተሌ ነበረች።

ቀጣሪዋ ፋብሪካ ታዲያ ሥራ ብቻም ሳይሆን ሥልጠናም ነው ሰጣት። ከዚህም ባሻገር ደምወዟ የሚያቀናጣ ባይሆንም ለሠራተኞች የምግብ አቅርቦት መኖሩ ዕለታዊ ወጪዋን በመቀነስ አግዟታል።

ከመንፈቅ ገደማ በፊት ታዲያ አመለጥኩት ካለችው ሥራ አጥነት ጋር ዳግም እንድትፋጠጥ ግድ ሆነ። ትሰራበት የነበረው የአልባሳት ፋብሪካ በርካታ ሠራተኞችን ሲያሰናብት ከተቀናሾች መካከል ራሷን አገኘችው።

“አሰሪያችን የማመርተውን ምርት የሚቀበለኝ አካል ስለሌለና ገበያ ስላጣሁ ከሁለት ሺህ በላይ ሠራተኞችን ለመቀነስ እገደዳለሁ አለ” ትላለች።

አሁን ከተንቆጠቆጠው የፓርኩ ግቢ ጥቂት መቶ ሜትሮች ገደማ ርቆ ባለው ከጭቃ ከተሰራ የኪራይ ቤቷ በር ላይ ሽንኩርት እና ድንች ደርድራ ለመሸጥና ጥቂትም ቢሆን ገቢ ለማግኘት ትጥራለች።

ድካሟ ግን እምብዛም ስኬትን እያስገኘላት አይደለም፤ “ዝም ብዬ ተቀምጬ ነው ያለሁት” ቢባል ይቀላል ትላለች። “ኑሮ በጣም ከብዷል” በማለት ነው ፈተናዋን ለቢቢሲ የገለፀችው። “ሳሙና፣ ቅባት - አሁን ሁሉም ውድ ነው። ያለሥራ መቀመጥ በጣም ከባድ ነው።”

ከምንም በላይ የሚያሳስባት ደግሞ የሁለት ትንንሽ ልጆቿ ዕጣ ፈንታ ነው።

አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2000 የአፍሪካ ዕድገት እና ልዩ ተጠቃሚነት ድንጋጌን ስታጸድቅ ከተጠቃሚዎቹ መካከል ኢትዮጵያ አንደኛዋ ነበረች።

ይህ በምህፃረ ቃሉ አጎዋ እየተባለ የሚጠራው ድንጋጌ ለተወሰኑ ከሰሃራ በታች ላሉ አገራት ያለ ቀረጥ ምርቶችን ወደ ግዙፉ የአሜሪካ ገበያ በማስገባት እንዲሸጡ ፈቃድን ይሰጣል።

በዚህ ዓመት ወርሃ ታኅሣሥ ገደማ ታዲያ ኢትዮጵያ በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ መስፈርቶችን ተላልፈሻል በሚል ከሌሎች ሁለት አገራት ጋር ከአጎዋ ተሰርዛለች።

በላይነሽ ከዚህ ውሳኔ ሰለባዎች አንደኛዋ ናት።

“ያልተጠበቀ ውሳኔ”

አቶ ህብረት ለማ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ከ20 በላይ ባለሀብቶችን የሚወክለው ማኅበር የጋራ ተግዳሮቶችን እንዴት ለመፍታት ይቻላል በሚሉ የፖሊሲ ጉዳዮች ከመንግሥትም፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትም፣ ከምርት ተቀባይ አካላትም ጋር ይመክራል።

ከስምንት ወር በፊት አንስቶ ተግባራዊ የሆነው ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት የመፋቅ ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ባሉት ጥቂት ወራት “ብዙዎችችን እውን አይሆንም የሚል ተስፋ ነበረን” ይላሉ።

እንዲያም ሆኖ ውሳኔውን አጣዳፊና ለዝግጅት ጊዜ ያልሰጠ ነበር ይሉታል።

“መረዳት ያለብን ነገር ይሄ ድንገተኛ ውሳኔ እንደበር ነው፤ የአንድ ወር ወይንም የሁለት ወራት የመዘጋጃ መስኮት ነው የነበረን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ ገዢዎች ትዕዛዛቸውን ወደሌላ ስፍራ ለማዛወር፣ አምራቾችም አማራጭ መላዎችን ለመሻት በቂ ጊዜ አልነበራቸውም።

እ.ኤ.አ በ2020 የአጎዋ መርሀ ግብር ተጠቃሚዎች የነበሩ አገራት 38 ነበሩ። ከጥር አንድ 2022 ጀምሮ ግን ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ጊኒ ከዝርዘሩ ተፍቀዋል።

ለውሳኔውም በምክንያትነት ጊኒ እና ማሊ ህጋዊነት የጎደለው የመንግስት ለውጥ አድርገዋል የሚል ውንጀላ በልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሲቀርብባቸው፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በሰሜናዊ ክፍሏ በተፋፋመው የእርስ በእርስ ጦርነት “በመንግሥት እና በሌሎችም አካላት” ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያላቸው ሰብዐዊ መብቶች በአስከፊ ሁኔታ ተጥሰውባታል ተብላ ተወቅሳለች።

ከውሳኔው ወራትን አስቀድሞ የመንግሥት ሹማምንት ለተደቀነው አደጋ ተገቢ የሆነ አትኩሮት አልሰጡም ሲሉ የሚተቹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በፓርኩ ከፍተኛ ሚና ያላቸው አንድ ባለሙያ ናቸው።

በአንድ በኩል አሜሪካ ከማስጠንቀቅ ባለፈ በትክክልም እርምጃ አትወስድም የሚል እምነትና ተስፋ ነበረ የሚሉት እኝህ ባለሙያ “ችግሩ ግን ይህ ተስፋ ያለምንም ማስረጃ እንዲሁ አየር ላይ የተንሳፈፈ መሆኑ ነው።”

ከዚህም በዘለለ እርሳቸው “የአጎዋ-አድዋ ውዥንብር” ሲሉ የገለፁት ከመንግሥት በኩል ሲንፀባረቅ የነበረ የተምታታ አቋም መፍትሄው ላይ ላለመረባረብ ፈተና ፈጥሯል ይላሉ።

“በአንድ በኩል እንደ አጎዋ ዓይነት መርሀ ግብሮችም ሆኑ እርዳታ አያስፈልጉንም የሚል አቋም የሚንፀባረቅ ይመስል ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ የውትወታ ሥራዎችን ለመስራት እንዲሁም ተገቢ የሙግት ደብዳቤዎችን ለመፃፍ የታየው ዳተኝነት ዋጋ አስከፍሏል ባይ ናቸው።

“ርብርቡ የመጣው ከረፈደ በኋላ ነው።” 

“ትልቁን ገበያ” ማጣት

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ካሉ ኩባንያዎች አንዱ ናሳ ጋርመንትስ ፒኤልሲነው። ሁለት የአልባሳት ማምረቻዎች አሉት። በአንደኛው ፋብሪካው ሱሪዎችን በሌላኛው ደግሞ ከወገብ በላይ የሚደረጉ አልበሳትን ያመርታል።

እ.ኤ.አ በ2019 በአራት ሚሊዮን ዶላር ሥራ የጀመረው ፋብሪካ አሁን ራሱን የአስር ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ወዳለው ድርጅትነት አሳድጓል ይላሉ ኃላፊው ራጋው ፓታር።

ሕንዳዊው ፓታር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉትን አስራ አንድ ዓመታት ኖረዋል። አሁን የሚመሩትንም ተቋም “ሦስተኛው ፕሮጄክቴ” ሲሉ ይገልጹታል። ይህ ፕሮጄክታቸው ግን ከበድ ያለ ፈተናን ደቅኖባቸዋል።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ መርሀ ግብር ከመሰረዟ በፊት የሚመሩት ኩባንያ ከ80 እስከ 85 በመቶ የሆኑ ምርቶቹን ወደአሜሪካ ገበያ ይልክ ነበር።

“አሜሪካ የዓለማችን ትልቁ ገበያ ናት” ይላሉ ፓታር ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ። “ስለዚህ አሜሪካ ምርትህን የማትቀበል ከሆነ፣ መጠኑን መቀነስህ ግድ ይላል።”

ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸሩ ትንሽ ናቸው የሚሏቸውን የአውሮፓንና የካናዳን ገበያዎች እያማተሩ ፊታቸውን ወደዚያ ለማዞር እየሞከሩ እንዳሉ ይናገራሉ ኃላፊው። “አማራጮችን ለመጠቀም እየሞከርን ነው፤ ነገር ግን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።”

ከመንግሥት አካላት ጥሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳለ ይገልፃሉ ፓታር፤ ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት “በተቻለ ፍጥነት ወደ መርሀ ግብሩ የምትመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።”

ይህም እውን ይሆናል የሚል በጎ እምነት አላቸው።

የባለሀብቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጁ አቶ ህብረትም ኢትዮጵያ ምናልባትም እ.ኤ.አ በ2023 ወደ አጎዋ መርሀ ግብር ልትመለስ የምትችልበት “የተወሰነ ዕድል” አለ ይላሉ።

ማኅበራቸውም ይህ እንዲሆን በተቻለው አቅም ምክክር ከመንግሥት ጋር እያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ። ነገር ግን “በቀጣይ ወራት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አንችልም።”

ስማቸውን እንድንገልጽ ያልፈለጉት ባለሞያ የኢንዱስትሪ ፓርኩ እና በውስጡም ያለው የአልባሳት ምርት ኢንዱስትሪ ያጋጠመውን ደንቃራ “የወጀቦች ግጥምጥሞሽ” ሲሉ ነው የገለፁት።

“ፖለቲካዊ ያለመረጋጋቶች፣ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከዚያም የሰሜኑ ጦርነት እና የእርሱ መዘዝ የሆነው ከአጎዋ መሰረዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ተከታትለው ወይንም ተደራርበው የመጡት፤ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በአውሮፓ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ዓለም አቀፍ የሆነ የማጓጓዣ ሰንሰለት ዋጋ ጭማሪ አለ።”

አቶ ህብረት በኮቪድ ወረርሽኝ መግቢያ ወቅት መንግሥት የወሰዳቸውን አስቸኳይ የድጋፍ እርምጃዎች ያደንቃሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ዋጋ ላይ ድጎማ ተደርጎ እንደነበር ያወሱና አሁን ተመሳሳይ የድጋፍ እርምጃዎች የማይወሰዱ ከሆነ ለአምራቾችም ሆነ እነርሱ ለቀጠሯቸው ሠራተኞች፣ ከዚያም ባለፈ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ትልቅ መዘዝ ሊኖረው ይችላል በማለት ያስጠነቅቃሉ። 

ቆይቶ የሚሰማ ህመም

 ኢትዮጵያ ከአጎዋ መርሀ ግብር መቀነሷ ያስከፈለውን እንዲሁም የሚያስከፍለውን ዋጋ በቅጡ ለመረዳት ጊዜ ይፈጃል- እንደአቶ ህብረት ገለፃ።

ምርት ተቀባዮች አስቀድመው ትዕዛዝ ልከው ስለነበር፣ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ላይ (ከጥር በኋላ ባሉት ሦስት ወራት) ተፅዕኖው ብዙም አልታወቀም፤ “የቀረጥ ጭማሪ የሚያስከትለውን የዋጋ ከፍታ ያው ገዢዎች ይሸፍናሉ።”

በትክክል ተፅዕኖው ይስተዋል የጀመረው ግንቦት አካባቢ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ለዚህም በአስረጅነት ቁጥሮችን ያቀርባሉ። “ባለፈው ዓመት ግንቦት መጨረሻ ገደማ 30 ሺህ ሠራተኞች ነበሩ ፓርኩ ውስጥ” ይሉና በዚህ ዓመት ሰኔ አካባቢ ግን ይህ ቁጥር ወደ 26 ሺህ መውረዱን ያነሳሉ።

“እውነታው ከዚህም ይከፋል”- ሁሉም አምራቾች በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማስፋፊያ ለማድረግ እና የሠራተኞቻቸውን ቁጥርም በድምሩ ወደ አርባ ሺህ ለማሳደግ ዕቅድ ነበራቸው። ነገር ግን እነዚህ የማስፋፊያ ውጥኖች አሁን ተሰርዘዋል፤ ተስፋ የተደረጉት አዳዲስ ሥራዎችም ውሃ በልቷቸዋል።

“ፓርኩ ቀጥተኛ ተቀጣሪ ሠራተኞችን ብቻ አይደለም የሚጠቅመው፤ ከተማዋን በጠቅላላ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ህብረት ለሠራተኞች ምግብ የሚያቀርቡ አነስተኛና መካከለኛ ምግብ አብሳይ የአካባቢው ድርጅቶች፣ ከፋብሪካዎቹ ጋር ባንከኞች፣ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ አዋቂዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች በሙሉ ህመሙ ቀስ እያለ እየደረሳቸው ነው ይላሉ።

ባለፉት ዓመታት የታዩ መሻሻሎች የኋሊት እንዳይሸመጥጡ ስጋታቸውን አይደብቁም ህብረት።

“አምስት ዓመት ፈጅቷል ይሄንን ኢንዱስትሪያዊ ባህል ለማዳበር። በሒደት ነው እዚህ የተደረሰው” ይላሉ።

በግራ መጋባት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች

በላይነሽ የግቢ ተጋሪዎቿ፣ ቡና አጣጭ ጓደኞቿ በሙሉ የፓርኩ ሠራተኞች ወይንም የፓርኩ ሠራተኞች የነበሩ ናቸው።

ባለቤቷ ሽመልስ ተስፋዬም ከአስራ አራት ዓመት የውትድርና ሕይወት በኋላ ግዳጁን ጨርሶ የሥራ መስኩን ሲቀይር ፓርኩ ውስጥ ነው የገባው። ለጥቂት ዓመታት በኋላ ፓርኩ ውስጥ ባለ አንድ ፋብሪካ ውስጥ ይሰራ ነበር።

ከአጎዋ መሰረዝ ወራትን አስቀድሞ ከሥራው የተቀነሰው ሽመልስ ሌላ ፋብሪካ ውስጥ ሥራ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበረው። ነገር ግን ፋብሪካዎቹ ሠራተኛ መጨመርን ትተው መቀንስን መያዛቸውን ሲያይ ተስፋው ከስሞ የጉልበት ሥራ ፍለጋ ላይ ተሰማርቷል። “የምችለው ሙያ ፋብሪካው ውስጥ የተማርኩትን የልብስ ሥራ ነው፤ ምን ልስራ?” ይላል።

በፓርኩ ውስጥ ሥራቸውን ያጡና መላ ቅጡ የጠፋባቸው በላይነሽን መሰል ወጣቶች ምናልባት ነገሮች ተስተካክለው ወደ ቋሚ የእንጀራ ገመዳችን እንመለስ ይሆን? ሲሉ ይባዝናሉ።

እስካሁን ሥራቸውን ያለማጣት መልካም ዕድል ያገኙት ደግሞ ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመን ይሆን? እያሉ በስጋት ይናጣሉ። ለአሁኑ ለጥያቄዎቻቸው ምላሹ ከእነርሱ እጅ እጅግ ርቆ ያለ ይመስላል።