የኤርትራ መንግሥት ከብሔራዊ አገልግሎት የከዱና ያልተሳተፉትን እያሰሰ መሆኑ ተነገረ

የኤርትራ መንግሥት ለዓመታት ሲተችበት ከቆየው የብሔራዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ አሰሳና ፍተሻ ማካሄዱን ቢቢሲ ከምንጮቹ ተረድቷል።

በዚህም ከሁለት ሳምንት በፊት የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ከአባሓን እና ዲዖት ኮረብታዎች ግርጌ በሚገኙት አኹሩር፣ ምዔላ፣ ዓዲ-ቆንጺ፣ ዓዲ-ፊኚሕ፣ ሔቦ መንደሮች ከፍተኛ አሰሳ ሲያካጊዱ መሰንበታቸው ተነግሯል።

በየመንደሩ የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ከሠራዊቱ የከዱ እና ወደ ሳዋ ላለመሄድ ተደብቀዋል ያሏቸውን ለመፈለግ መኖሪያ ቤቶችን ፈትሸዋል።

የፀጥታ አካላት የሚፈልጓቸውን ሲያጡ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን አስወጥተው ቤታቸውን ማሸጋቸውን፣ አድሓኖም የተባለ ኖርዌይ የሚኖር የአካባቢው ተወላጅ ከአካባቢው ነዋሪዎች የሰማውን በመጥቀስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ወታደሮቹ ከሠራዊቱ የከዱ እና ወደ ሳዋ የማሰለጠኛ ማዕከል ላለመሄድ የተደበቁ ወጣቶችን ስም ዝርዝር ከአካባቢው አስተዳደር ይዘው በመምጣት እየፈተሹ፣ ሲያጧቸው ቤቱን ስለሚያሽጉት ህጻናትና እናቶች አስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ብሏል አድሓኖም።

ለረጅም ጊዜ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ይህ የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት የጊዜ ገደብ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በቂ ክፍያም ስለሌለው በርካታ ወጣቶች የእረፍት ጊዜ ፈቃድ እየጠየቁ የጉልበት ሥራ እየሰሩ ወላጆቻቸውን ሲደግፍና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እንደሚገደዱ አንዳንዶች ይናገራሉ።

ይህ ሁኔታ በቅርቡ አሰሳ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ኤርትራ ያሉ ወጣቶችን የሚመለከት ሲሆን፣ ከአገልግሎቱ ከመሸሽ ባሻገር ወጣቶቹ በስደት ወደ ሌሎች አገራት ለመሄድ ከሚያስገድዷቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ይነገራል።

በምሥራቅ ኤርትራ ተዳፋት አካባቢ በሚገኙት በአብዛኞቹ የጸንዓደግለ መንደሮች ሰፊ የግጦሽ ሳር ካለባቸው አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችም ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት እራሳቸውን እየደበቁ ይገኛሉ ተብለወል።

ከዚህ ገደብ የለሽ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽም በትውልድ ቀያቸው በሚገኝ በረሃ ውስጥ ተደብቀው ሕይወታቸውን እየመሩ እንደሚገኙ ሚላን ውስጥ የሚኖረው አብርሃም መሃረና ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአሁኑ ጊዜ የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ኃይል በማሰማራት በየመንደሩ እያሰሰ “ልጆቻችችሁን አምጡ እያለ ቤታቸውን እያሸገ ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ወላጆቻቸውን ሜዳ ላይ እየበተነ” እንደሚገኝ ገልጿል።

በኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ዕድሜያቸው የደረሰ ወጣቶች ብሔራዊ አገልግሎት ውስጥ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው።

ከዚህ አዋጅ በኋላ ትምህርታቸውን የጨረሱም ሆነ ያቋረጡ ወጣቶች 18 ዓመት ሲሞላቸው የስድስት ወራት የውትድርና ሥልጠና እና ዓመታዊ አገልግሎት መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።

ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በድንበር ይገባኛል ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ወደ የአገሪቱን ሠራዊት የሚቀላቀል እንጂ አገልግሎቱን ጨርሶ የሚሰናበት ኤርትራዊ ወጣት የለም ሲሉ አንዳንዶች ይናገራሉ።

እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋች ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከ18 ወራት ወዳልተገደበ የግዳጅ ሥራ የተሸጋገረው የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት ለስደትና ለሰብዓዊ መብት ቀውሱ ዋነኛ መንስኤ ነው ይላሉ።

የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ጋይም ክብረአብ እንዳሉት በአገር ልማት ስም በተለያዩ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የግል ንግዶች ውስጥ ለመሥራት የሚገደዱ የብሔራዊ አገልግሎት አባላት በጨካኝ ወታደራዊ ቅጣትና ስቃይ ተማረው አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት እና ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እየተሰደዱ ነው።

ዶ/ር ጋይም በአንድ ወቅት ከብሔራዊ አገልግሎቱ ሸሽቶ ድንበር ሲሻገር የተገኘ አባል በጥይት እንዲመታ የሚል ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበር ያስታውሳሉ።

የኤርትራ መንግሥት ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበውና ትግራይ ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥት በመደገፍ በግጭቱ መሳታፉን በተመለከተ የተለያዩ ሪፖርቶች መስክረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በህወሓት ወረራ ሊፈጸምበን ነው በሚል ሁሉም ኤርትራውያን ‘ታሪካዊ ግዴታዊ መድረክ’ ባለው ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ እያቀረበ ነው የሚለው አቶ አብራሃም መሀረና፣ የአሁኑ አፈሳም ለዚሁ ዓላማ የታሰብ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል።

ኤርትራ ዋነኛ የስደተኞች ምንጭ ተብላ እንደተጠቀሰች የሚያስታውሰው አቶ አብርሃም በጸንዓደግለና በሌሎች አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ሕዝቡን እያማረረ ቤቱንና መሬቱን ጥሎ እንዲሰደድ እያስገደደው እንደሆነ ይገልጻል።

“ወታደሮቹ ከዚህ በፊት እረኞች እንኳን ገብተውበት ወደማያውቁ የስያሕና ዓሊገደን በረሃዎች እየወረዱ ወጣቶቹን እንደጠላት እያደኗቸው ነው” በማለት በኤርትራ መንግሥት ኃይሎች የተጀመረውን ዘመቻ ስፋት ያስረዳል።

“ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን በዚህ አሰሳ ምክንያት በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርሰው በደል ነው” ሲል አብርሃም በመንግሥት አካላት የሚፈጸመውን ድርጊት አስከፊነት ገልጿል።

አቶ አድሃኖም በበኩሉ “የኤርትራ ሕዝብ ለአገሩ ነጻነት በርካታ ወጣቶችን ሰውቶ ሲያበቃ፣ በድንበር ሰበብ በተፈጠው ጦርነትም በራሱ ፈቃድ የቀሩት ልጆቹ እንዲዘምቱ አድርጎ ነው የአገሩን ሉዓላዊነት ያስጠበቀው። ይህንን በራሱ ፈቃድ የሚዘምትን ሕዝብ በአደንና በአሰሳ ለማሰማራት መመኮር ተቀባይነት የለውም” ይላል።

በተጠቀሱት አካባቢዎች ሰፍሮ የሚገኘው የኤርትራ ሠራዊት ለሚያካሂደው አሰሳ አመቺነት ሲል መንገዶችን መዝጋቱን አቶ አብርሃም ጨምሮ ተናግሯል።

በኬላዎች አካባቢ ጥብቅ ፍተሻ እና ቁጥጥር መኖሩን የሚናገረው አቶ አብርሃም “በጠንካራ ቁጥጥሩ የተነሳ በአትክልት ቦታዎች ላይ የሚገኝ ምርትን የሚሰበስበው ጠፍቶ እየባከነ ነው” ሲል ያክላል።

አቶ አድሃኖም ጸንዓደግለ አካባቢ በሚደረገው አሰሳ እና አፈሳ የተነሳ ሁለት ወጣቶች በጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን ገልጾ፣ የመንግሥት እርምጃ ወደ አጎራባች ማዕረባ አካባቢዎችም እየተስፋፋ ይገኛል ብሏል።

እንደ አድሃኖም እንደሚገልጸው የመጀመሪያው ዙር ብሔራዊ አገልግሎት በ1994 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኤርትራ ወጣቶች የኪስ ገንዘብ ብቻ እየተሰጣቸው ለ20 ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ቤተሰቦቻቸው እንደታፈሱባቸው የሚገልጹት እነዚህ ግለሰቦች የኤርትራ ሕዝብ ከመንግሥቱ እንዲህ አይነት ከባድ ግፍ እንደማይጠብቅ፣ ወጣቱን እና አረጋውያንን ማፈሱን እንዲያቆም ይጠይቃሉ።

ቢቢሲ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚገኙ ኤርትራውያን መንግሥታቸው ላይ ያቀረቡትን ውንጀላ እና ክስ ተከትሎ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።