በኤርትራ 17 የወንጌል አማኞች መታሰራቸው ተነገረ

ቢያንስ 17 ኤርትራዊያን የወንጌላዊ እምነት ተከታዮች መታሠራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት እያካሄዱ ባሉበት ወቅት እንደነበረ ተነግሯል።

የቢቢሲ ምንጮች እንደሚሉት አማኞቹ ከአሥመራ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው ማይስርዋ እሥር ቤት ተወስደዋል። ይህ እሥር ቤት ከዚህ በፊት በእምነታቸው ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች የተወሰዱበት ነው። የኤርትራ መንግሥት ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ በርካታ የወንጌላዊ ቤተ-እምነቶችን የዘጋ ሲሆን፤ ቁጥራቸው የበዛ አማኞችም ለእሥር ተዳርገዋል። በዚህ ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል ተብሏል።

በዚህም ሳቢያ ለ20 ዓመታት ያክል ለፍርድ ሳይቀርቡ እሥር ቤት ያሉ ግለሰቦች እንዳሉም ከዚህ በፊት ተዘግቧል።

የወንጌላዊ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ተቀባይነት ያላቸው የኦርቶዶክስ እምነት ቀሳውስትና ዶክተሮችም በዚህእሥር ቤት ይገኛሉ።

ዶክተር ፍፁም ገብረንጉሥ፣ ዶክተር ተኽለዐብ መንግሥተዐብ፣ ዶክተር ክፍሉ ገብረመስቀል፣ ፓስተር ኪዳኔ ወልዱ እንዲሁም ኃይሌ ናይእዝጊ በፈረንጆቹ ከ2004 ጀምሮ በእሥር ላይ ከሚገኙ መካከል ናቸው።

ከኤርትራ ውጭ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችና መሪዎች ምንም እንኳ ከእሥር ቢለቀቁም ኤርትራ ውስጥ ያለው የእምነት ነፃነት እንዳልተሻሻለ ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት በኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አስተባባሪ "ኤርትራ የሰብዓዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊው ማኅበረሰብ እንዲበለጽግ የሚያስችል ተቋማዊና ሕጋዊ ሥርዓት አልዘረጋችም" በማለትየኤርትራ ሁኔታን ገልፀውት ነበር።

ሕገ መንግሥት አለመኖር፣ ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት አለመዘርጋቱ ኤርትራ ውስጥ የሕግ የበላይን አለመኖሩን የሚያሳይ ነው ብለው ነበር።