ሕጋዊ ሰነድ አለን ያሉ በርካታ ኤርትራውያን በመጠለያ ጣቢያ “እንደ እስረኛ” ተይዘናል አሉ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ሕጋዊ ሰነድ ቢኖረንም “እንደ እስረኛ” በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተይዘን እንገኛለን አሉ።

ኤርትራውያኑ ከቀናት በፊት ከሃይማኖታዊ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ሳለ መንገድ ላይ በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ አማራ ክልል ወዳለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መወሰዳቸውን ይናገራሉ።

በአማራ ክልል ዳባት ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አለምዋጭ መጠለያ የሚገኙት ኤርትራውያን፤ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰንዳፋ በሚገኝ ገዳም ፀበል ተጠምቀው ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ሳለ ለገጣፎ ሲደርሱ በኃይል ተይዘው ወደ መጠለያ ጣቢያው ተወስደናል ብለዋል።

ቢቢሲ ከኤርትራውያኑ እንደተረዳው ለገጣፎ ላይ ተይዘው ወደ መጠለያው የተወሰዱት ሰዎች ብዛት 160 ነው።

ይሁን እንጂ ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም. ከመጠለያ ጣቢያው 22 ሰዎች እንዲወጡ መደረጋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኤርትራውያን ተናግረዋል።

ተይዘው ይገኛሉ የተባሉት ሰዎች የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኤርትራውያን እንዲሁም በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መሆናቸውን በመጠላያ ጣቢያው ያሉ ኤርትራውያን ገልጸዋል።

“ከመካከላቸውም ህጻናት እና ሴቶች፣ ከውጭ ቤተሰብ ጥየቃ የመጡ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው አሉ” በማለት አንድ በመጠለያ ጣቢያው ያለ ኤርትራዊ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ሮቤል፤ በግዳጅ ወደ መጠለያ ጣቢያው እንዲገቡ ከተደረጉት መካከል አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ መኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ናቸው ይላል።

የተቀሩት ደግሞ ከውጭ አገር ፀበል ለመጠመቅ የመጡ፣ ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የወጡ እና ሕጋዊ ሰንድ የሌላቸውም ይገኙበታል ብሏል።

ሮቤል ተይዘው የሚገኙበት መጠለያ ጣቢያ ለኑሮ አመቺ ያልሆነ ቦታ ላይ ስለተቋቋመ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን ብሏል። በክረምቱ ዝናብ ምክንያት ባለው ጭቃ መንቀሳቀስም አይቻልም ይላል።

ኤርትራውያኑ እንደሚሉት በመጠለያ ጣቢያው እንደ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች ስላላገኙ በመጠለያነት የሚያገለግለው ድንኳን የሚቋጥረውን ውሃ ለመጠጥነት ለመጠቀም መገደዳቸውን ያስረዳሉ።

ነብሰ ጡር እና የሦስት ልጆች እናት እንደሆነች የምትናገረው ኤርትራዊት፤ ፀበል ለመጠመቅ ብላ ከባለቤቷ ጋር ከቤት ከወጣች በኋላ በመጠለያ ጣቢያው በኃይል መያዟ ጨንቀት ውስጥ እንደከተታት ትገልጻለች።

“ከቤት ስወጣ ጎረቤት ጋር አደራ ሰጥቼ ያስቀምጥኳቸው ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ የሦስት ልጆቼ ጉዳይ አሳስቦኛል” ብላለች።

ይህች የሦስት ልጆች እናት የኤርትራ ፓስፖርት እና ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚያስችላት ሕጋዊ ሰነድ እንዳላት ጨምራ ተናግራለች።

ሰሎሞን የተባለው ኤርትራዊ በበኩሉ በመጠለያ ጣቢያው ተይዘው ከሚገኙት መካከል ከካናዳ፣ ከአሜሪካ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከጀርመን፣ ከሱዳን፣ ከኡጋንዳ እና ከሌሎች አገራት የመጡ ሰዎች እንደሚገኙበት ይገልጻል።

ከሱዳን እንደመጣ የሚናገረው አርዓዶም የተባለ ወጣት ደግሞ ከሦስት ቀን በፊት ወደ ሱዳን መመለስ እንደነበረበት ገልጾ፤ በምን ምክንያት እንደተያዙ የሚነግራቸው አካል እንኳ እንደሌላ ተናግሯል።

ከትናንት በስቲያ ከመጠለያ ጣቢያው እንዲወጡ ተደርጓል የተባሉት ሰዎች በስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ባልደረቦች ታጅበው ወደ ባሕር ዳር መወሰዳቸውን ቢቢሲ ተረድቷል።

ኤርትራውያኑ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያው ለምን ያለፍቃዳቸው እንደተያዙ ቢቢሲ የኤጅንሲውን አመራሮች በተደጋጋሚ ቢጠይቅም “ምናልባት ከሳምንት በኋላ ካልሆነ በቀር አሁን ላይ መናገር አንችልም” የሚል ምላሽ አግኝቷል።

ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ጉዳዩን በተመለከተ ሰኞ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ኤርትራውያኑ ያለ ፍቃዳቸው ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ ተደርጓል የሚሉ ሪፖርቶችን መመልከቱ እንዳሳሰበው ጠቅሷል።

ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞቹ በኃይል ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ ማድረጉ ከአገሪቱ እና ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ጥበቃ ሕግ ጋር የሚጻረር ነውም ብሏል።