በአፍሪካ አየር ላይ ‘የአንበሳውን ድርሻ’ እየያዘ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 

75 ዓመታት በሙሉ ስመ ገናና ሆኖ ዘልቋል-የኢትዮጵያ አየር መንገድ።

ለስመ ገናናነቱም መገለጫ ከሆነው አንዱ ከበርካታ አየር መንገዶች ልቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደጋጋሚ ሽልማቶችን መቀዳጀቱ ነው። 

የአውሮፕላን ጭነት ዘርፍ የደንበኞች መስተንግዶ ሽልማትን በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜም ያሸነፈው በቅርቡ ነው።

አየር መንገዱ የዘንድሮውን፣ የ2022 የአፔክስ ክልላዊ የመንገደኞች ምርጫ ሽልማት ላይ በአፍሪካ ምርጥ አገልግሎትን በመስጠት 'Best Entertainment ' እና 'Best cabin service ' በሚል ዘርፎች አሸናፊም ሆኗል።

ለተወዳዳሪነቱ በርካቶች የሚመሰክሩለት አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የዘርፈ ብዙ ሽልማቶች ተሸላሚና በአፍሪካ ትልቁ የአየር ዕቃ ጭነት አገልግሎት ሰጪም ነው።

በርካታ ሽልማቶችን በማሸነፍ በዓለም ላይ ስመ ጥርና በአቪየሽን ኢንዱስትሩው ዘርፍም ከሚጠቀሱት አንዱ አድርጎታል።

ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ታሪክን ስንዳስስ አየር መንገዱ ሲ-47 በተባሉ ቀደምት አውሮፕላኖች በአውሮፓውያኑ 1946 ሥራውን መጀመሩን ከድረ ገጹ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

በወቅቱም ካይሮ፣ ጅቡቲ እና ኤደን ከመጀመሪያ መዳረሻዎቹ መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።

ጅማ ደግሞ ቀዳሚዋ የአገር ውስጥ መዳረሻ ነበረች። 

ሥራውን ሲጀምር የነበሩት ሲ-47 አውሮፕላኖች ቁጥር በዚያው ዓመት ዘጠኝ ደረሱ። 

እነዚህ አውሮፕላኖች ቀደም ሲል ለአሜሪካ ጦር ግልጋሎት የሰጡ ሲሆን ተጣጣፊ መቀመጫዎችም የተገጠሙላቸው ነበሩ። 

ከሸራ ከተሰሩት መቀመጫዎች በተጨማሪ የተሳፋሪዎችን ዕቃ ለመጫን መተላለፊያዎቹ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። 

ፊት ለፊት ‘ተፋጠው’ የሚሄዱባቸው መቀመጫዎች የተገጠሙላቸው አውሮፕላኖችም ነበሩት። 

በመቀጠልም መዳረሻዎቹን በማሳደግ አየር መንገዱ ወደ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን እና ቦምቤይ በረራዎችን ማድረግ ጀመረ። 

በዚህ መንገድ ወደ ስኬት መንደርደር የጀመረው አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከ22 በላይ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት። 

ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችንም ያካልላል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት አየር መንገዶች አንዱ ነው።

በአህጉሩ ያለውን ተቀባይነት ለማስፋትም ደፋ ቀና እያለ ሲሆን በዋነኝነትም በአህጉሪቱ ውስጥ በሚገኙ የአየር መንገዶች ድርሻ መግዛትን ተያይዟል።

አየር መንገዱ በዘርፉ የአህጉሩን ‘የአንበሳ ድርሻ’ ለመያዝ እንደቻለም አስታውቋል ። 

በተለያዩ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች ድርሻ በመያዝም ስድስት የሚበልጡ የአፍሪካ አገራትን ደርሷል።

በአውሮፓውያኑ 2025 ቀዳሚው የአፍሪካ አየር መንገድ ለመሆን ዕቅድ አውጥቶ እየተገበረም ነው። 

ይህንን እቅድ ለማሳካት ደግሞ ከአንዳንድ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በሽርክና በመሥራት ላይ ይገኛል። 

በአስተዳደራዊ እና በስትራቴጂክ አጋርነት ከእነዚህ አገራት አየር መንገዶች ጋር ይሠራል። 

በተጨማሪም በአንዳንድ አገራት ያሉ አየር መንገዶችን ድርሻ እስከ መግዛትም ደርሷል።

በአንዳንድ በረራዎች ወቅት የተለያዩ አየር መንገዶች ስም እና አርማ ባረፉባቸው አውሮፕላኖች በረው ይሆናል።

እነዚህ አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በሽርክና የሚሠሩ አየር መንገዶች ሊሆኑም ይችላሉ። 

ለመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያለው ተሳትፎ ምን ይመስላል? የተወሰኑትን እንመልከት። 

ኮንጎ

'ኤይር ኮንጎ' የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አየር መንገድ ሲሆን ከፍተኛ ባለቤትነቱን የአገሪቱ መንግሥት ነው የተቆጣጠረው።

የአገሪቱ መንግሥት ከአየር መንገዱ ድርሻ 51 በመቶውን ይይዛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ በመያዝ ሥራቸውን በጋራ ያከናውናሉ። 'ኤይር ኮንጎ' ከአስር የሚበልጡ አውሮፕላኖች ባለቤት ነው።

ከእነዚህም ውስጥ ዳሽ 8-400፣ ቦይንግ 737 እና ቦይንግ 787 ተጠቃሽ ናቸው።

ለአየር መንገዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ያቀርባል።

ዛምቢያ

የዛምቢያ አየር መንገድ የዛምቢያ ሪፐብሊክ አየር መንገድ መሆኑን ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ የሚያስረዳ ሲሆን መቀመጫውም ሉሳካ ነው። 

በቅርቡ ሥራ ከጀመረው አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

ቀሪው ድርሻ የአገሪቱ ነው።

ሥራቸውንም በቦምባርዲየር ኪው-400 ጀምረዋል።

አየር መንገዱ ቀደምት ከሚባሉት አንዱ የነበረ ሲሆን የኋላ ኋላ ግን በደረሰበት ኪሳራ ከሥራ ውጭ ሆኖ ነበር።

ሞዛምቢክ

በሞዛምቢክ የሚገኘው አየር መንገድ- የኢትዮጵያ ሞዛምቢክ አየር መንገድ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። 

ይህ ጥምረት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።

ሥራው ሲጀመር በዋናነት የአገር ውስጥ በረራ ላይ ትኩረት አድርጎ ነው።

በአገር ውስጥ ከዘጠኝ በላይ መዳረሻዎች ነበሩት። 

ለእነዚህ በረራዎች ኪው 400 የሚባሉ አውሮፕላኖችን ይጠቀማል። 

የኮቪድ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ሥራቸው ተቋርጦ ቢቆይም በኋላም ወደ በረራ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 99 በመቶ የሚደርስ ድርሻ እንዳለው ታውቋል።

መቀመጫውን ማፑቶ ሞዛምቢክ አድርጓል።

የዓለም አቀፍ በረራዎቹን በቅብብሎሽ በአዲስ አበባ በኩል ነው የሚያደርግ ይሆናል።

ቶጎ

'ኤስካይ' ዋና መቀመጫውን ቶጎ ሎሜ ያደረገ አየር መንገድ ነው።

ኤስካይ በዋናነት ትኩረቱን በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ አገራት ላይ አድርጓል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምዕራብ አፍሪካ ለሚሰጠው አገልግሎት ድጋፍ ያደርጋል።

ሁለቱ አየር መንገዶች በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል። 

ይህ ስምምነት የቴክኒክ እና የስተራቴጂያዊ አጋርነት መሆኑ ተጠቅሷል። 

አየር መንገዶቹ መንገደኞችን በመለዋወጥም አብረው ይሠራሉ። 

ማላዊ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶም አገልግሎቱን አስፋፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

ማላዊ አየር መንገድ የሃገሪቱ ንብረት ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህን አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ይዟል።

የአየር መንገዱን አስተዳደር ሥራዎችንም ያከናውናል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በማላዊ አየር መንገድ መካከል በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 11/2007 ተፈረመ።

በዚህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና አዲስ የተቋቋመው የማላዊ አየር መንገድ የበረራ መርሃ ግብራቸውን በማጣጣም ለመንገደኞች ምርጥ አማራጮችን ያቀርባሉ ተብሏል።

አየር መንገዱ በኪው 400 እና ቦይንግ ቢ737-700 በተሰኙ አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል። 

ቻድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አየር መንገድ ለመመስረት ከቻድ መንግሥት ጋር የተስማማው በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2018 ነበር።

'ቻዲያ' አየር መንገድ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

49 በመቶ ድርሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን መቀመጫውንም በቻድ ዋና ከተማ አድርጓል።

ሥራው የተጀመረው ስምምነቱ በተፈረመበት ዓመት በአገር ውስጥ በረራ ነው።

በአዲስ አበባ በኩል ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከተቀረው ዓለም ጋር ይገናኛል።

ኢኳቶሪያል ጊኒ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢኳቶሪያል ጊኒው ሲ2-ሲዬባ ኢንተርኮንቲኔንታል ጋርም ውል አለው።

አየር መንገዱ መቀመጫውን ኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ አድርጓል።

ሁለቱ አየር መንገዶች አስተዳደራዊ ስምምነት የደረሱት በአውሮፓውያኑ የካቲት 2018 ነው።

ለዓለም አቀፍ በረራዎች አዲስ አበባ ማዕከል ሆና ታገለግላለች።

በተጨማሪ. . .

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ውል በመፈጸም በጋራ ይሰራል።

በዚህም በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ አልሟል። 

ባወጣው የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በአውሮፓውያኑ 2025 የአህጉሪቱ ተቀዳሚ አየር መንገድ ለመሆን በመሥራት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስገባትም ይታወቃል። 

ከአንድ ወር በፊት አምስት ቦይንግ ቢ777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት አዟል። 

አየር መንገዱ ከ80 በላይ የቦይንግ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ላይ ይገኛል። 

በአፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ አየር መንገዶችም ቀዳሚው በመሆን ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት በነበሩት ሰባት ተከታታይ ዓመታትም 25 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል።