ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን አንድ ቢሊየን ዶላር ያህል ገቢ አጥቷል
ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በተፈጠረው መስተጓጎል ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣ ተገለጸ።
የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በአየር መንገዶች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ማምጣቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ይናገራሉ።
ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኛ በረራዎች መቆማቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ያንን ተከትሎ ደግሞ ከየካቲት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድርጅቱ መንገደኛ በማጓጓዝ ሊያገኘው ይገባ የነበረው ወደ አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ ሳያገኝ መቅረቱን ገልፀዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የዓለም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ከተደረገ ወራት አልፈዋል። ይህ ማለት በአየር የሚደረግ ጉዞ ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
ይህም በአየር መንገዶች ዓይን በሚታይበት ወቅት በአሁን ሰዓት ብዙ አየር መንገዶች አውሮፕላኖቻቸውን አቁመዋል ይላሉ ይላሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው። "የመንገደኛ በረራ ቆሟል። በኢትዮጵያ አየር መንገድም ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኞች አውሮፕላኖቻችን ቆመዋል።"
"ይኼ ለአንድ አየር መንገድ እጅግ በጣም ትልቅ የፋይናንስ ቀውስ ነው የሚያመጣው። ይህም ምንም የሚካድ አይደለም እጅግ ተጎድተናል" በማለትም የዚያን ያህል ደግሞ አየር መንገዱ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ሥራ ሰርቷል ሲሉ ድርጅቱ የሰራቸውን ሥራዎች ዘርዝረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢበርም ባይበርም በወር አምስት ቢሊየን ብር ያወጣል ያሉት አቶ ተወልደ ከመጋቢት ወር ጀምሮ የመንገደኞች ጉዞ በሚቆምበት ጊዜ የድርጅቱን ቋሚ ወጪዎች ለመሸፈን፣ አውሮፕላን ለመግዛት የተበደርውን ብድር ከነወለዱ መመለስ ይተበቅበታል።
በተጨማሪም አውሮፕላኖችን የተከራየንበት ወርሃዊ የኪራይ ወጪ ለመክፈል፣ እንዲሁም የሠራተኛ ደሞዝ፣ ጥቅማጥቅም፣ አበል፣ ለመሸፈን የሚያስችለውን "በየወሩ አምስት ቢሊየን ብር በየወሩ እንዴት ነው የምናገኘው? ይህ ወረርሽኝ ከቀጠለስ ምን እናደርጋለን?" በማለት መወያየታቸውን ይጠቅሳሉ።
በዚህ ወቅት "መጀመሪያ እድገት የነበረውን ስትራጂያችንን ወደ ሕልውና ማረጋገጥ ለወጥን" በማለትም ከመንገደኛ ማጓጓዝ ባሻገር ያለውን እድል በመፈተሽ የጭነት አገልግሎት መስጠትን በወቅቱ ያገኙት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ በዚህ ረገድ አስር 777 በጭነት ትራንስፖርት ምርጥ የሚባሉ አውሮፕላኖች፣ በተጨማሪም ሁለት 737 አውሮፕላኖች ስላሉት፤ እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ቶን ማስተናገድ የሚችልና ከነሲንጋፖር ከነሆንክ ኮንግ ከነአምስተርዳም ጋር ሊወዳደር የሚችል በጣም ዘመናዊ የካርጎ ተርሚናል ስላለው ይህንን እንደ ዕድል መጠቀማቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በዚያ ወቅት የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶች በጣም የሚፈለጉበት ጊዜ ነበር ያሉት አቶ ተወልደ ያለውን የገበያ ፍላጎት በመመልከት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ በርካታ ጭነቶችን ማጓጓዛቸውን ያስረዳሉ።
የድርጅቱ ገበያ እየጨመረ ሲመጣም ቁሳቁሶቹን በጭነት አውሮፕላኖች ብቻ ማንሳት ስላልተቻለ በፍጥነት የ25 የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወንበራቸውን በማውጣት ወደ ወደ ካርጎ ማዞራቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህንን በማድረጋቸው የተገኙ ጥቅሞችን ሲገልጹም ሠራተኛ ከሥራ አለማሰናበታቸውን፣ የሠራተኛ ደሞዝ አለመቀነሱን እና ነጥቅማጥቅሙ መከፈሉን፣ ሶስተኛ ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ ከማንም አለመጠየቃቸውን ያነሳሉ።
አክለውም ለጊዜው ሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር አልወሰድንም፤ ብድራችንም እንዲራዘምልን አልጠየቅንም በማለት በኮቪድ-19 ወቅት በወሰዷቸው እርምጃዎች ያገኟቸውን ስኬቶች ይዘረዝራሉ።
አየር መንገዱ ይህንን ሲያደርግ በዚህ በወረርሽኝ ጊዜ ህይወት የማትረፍ ሥራ መስራቱን ያነሳሉ። "የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ስፔንን ረድቷል። የኮቪድ-19 መከላከያ እቃዎችን በማቅረብ። ያ ማለት ሕይወት አትርፈናል ማለት ነው።"
ፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብራዚል እና አፍሪካ ሊደርስ ይችል የነበረውን ቀውስ መከላከል የሚያስችሉ የመከላከያ እቃዎችን ሕክምና መሳሪያዎችን በወቅቱ በማድረሳቸው ምክንያት አገሮችና ሕዝቦች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ክብርና ውለታ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
"የጃክማ ፋውንዴሽን እርዳታን ከቻይና አምጥተን በስድስት ቀን ውስጥ አፍሪካ ውስጥ አከፋፍለናል" ያሉት አቶ ተወልደ "ፍጥነታችን በጣም ተደንቋል።" ሲሉ የአፍሪካ አገሮችም የአሊባባ ፋውንዴሽንም በሥራው መደነቃቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህንን ተከትሎም የዓለም የምግብ ድርጅት አዲስ አበባን የተባበሩት መንግሥታት በሙሉ የሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈያ አድርጓታል ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ራሳችንን ጠቅመን፣ አየር መንገዱን አድነን፣ ሠራተኞቻችንን ሳንበትን፣ የሠራተኞቻችንን ደሞዝ ሳንቀንስ እና ሕይወት ማትረፍ በመቻላችን እንደ አንድ ዜጋ ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስፈላጊውን የግንዛቤ መስጫ ትምህርቶችን በማድረግና ጥንቃቁዎችን በመውሰድ ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ የድርጅቱ ሠራተኞች በጤና እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም አምስት ሠራተኞቹ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በማስታወስ ሁሉም ማገገማቸውንና አሁን ደግሞ ባለፈው ሳምንት ሁለት ሠራተኞች ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸው በድርጅቱ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ውስጥ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ ሥራዎችን በአግባቡ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገለፁት አቶ ተወልደ "በረራ ባለማቋረጣችን ለዚህ ልምድ አግኝተናል" ብለዋል።