ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያ ከ‹‹አሊባባው ጃክ ማ የተላከልኝን እርዳታ›› ተሰርቄያለሁ አለች
የኬንያ የወንጀል ምርመራ ፖሊሶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቻይናው ቢሊየነርና የአሊባባ ኩባንያ ባለቤት ጃክ ማ ተልከው የነበሩ ቁሳቁሶችን ማን እንደሰረቃቸው እየፈለግን ነው ብለዋል፡፡
የኬንያ ፖሊስ እንደሚለው የኬንያ መንግሥት የተሰረቀው ለኮሮናቫይረስ የተላኩ በርካታ ቁሳቁሶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብም ጭምር ነው፡፡
የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶቹ የቀዶ ጥገና ጓንቶች፣ የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችና በሐኪሞችና ነርሶች የሚለበሱ ጋውኖችን ያካተተ ነው፡፡
የኬንያ ፖሊስ ይህን መግለጫ የሰጠው ኬቲኤን የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከቻይና መንግሥት በእርዳታ የተሰጠ ግምቱ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሕክምና ቁሳቁስ እንዴት እንደተሰወረ ካጋለጠ በኋላ ነው፡፡
ቴሌቪዥን ጣቢያው ባሰራጨው የምርመራ ዘገባ አንድ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከቻይና ባለሀብቶች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ የግል ኩባንያ እነዚህ እርዳታዎች ኬንያ አየር መንገድ ሲደርሱ ይህ ኩባንያ የቁሳቁሶቹ ተረካቢ ሆኖ እንደቀረበ ያጋልጣል፡፡
ኬንያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከቻይናው ቢሊየነር ጃክ ማ በተጨማሪ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ እና ከአውሮጳ አገራት እርዳታ ተለግሷታል፡፡
ሆኖም የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ እጥረት በልገሳ የተገኙ ቁሳቁሶች የት ገቡ የሚል ጥያቄ አስነስቶ ቆይቷል፡፡
በኬንያ እስከ ዛሬ 3 ሺህ 727 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 104 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የኬንያ የጤና ባለሞያዎች እንደሚሉት ይህ በሽታ በማኅበረሰብ ደረጃ መሰራጨቱ የተረጋገጠ ሲሆን በመስከረም ወር የሟቾች ቁጥር በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር እየተጠበቀ ነው፡፡
የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሙታይ ካግዌ ሌቦቹን የገቡበትን ገብተን እንይዛቸዋለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ኬንያዊያን ፌስቡክን በመሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ያለውን ሙስናና መንግሥታቸው ሙሰኞችን ለመያዝ የሚያሳየው ዳተኝነት እንዳስቆጣቸው እየገለጹ ነው፡፡