ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤጂንግ የተነሳው አዲስ ወረርሽኝ ተከትሎ ተነስቶ የነበረው የጉዞ እገዳ ተጣለ
የኮሮናቫይረስ መነሻ በሆነችው ቻይና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደ አዲስ ጭማሬ በማሳየቱ አንስታቸው የነበሩ አስገዳጅ መመሪያዎች እንደገና ለመጣል ወስናለች። የማህበረሰቡ ስርጭት ቀጥ ብሎ በነረባት ቤጂንግ በዛሬው ዕለት 31 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ከተማዋ በሳምንቱም 137 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።
አዲሱ ጭማሬ ከመመዝገቡ በፊት ለአምሳ ሰባት ቀናት ያህል የማህበረሰቡ ስርጭት አልነበረም።
ወረርሽኙ የተነሳው ዚንፋንዲ ከተሰኘ ትልቁ ገበያ ነው ተብሏል። ገበያው የከተማዋን 80 በመቶ ስጋና አትክልት አቅራቢ ነው።
የሃገሪቱ ሚዲያ እንደዘገበው ቫይረሱ መጀመሪያ የተገኘው ከውጭ የመጣ ሳልመን አሳ ለመቆራረጥ በተጠቀሙበት ጣውላ ላይ ነው ብለዋል። የገበያው ዋና ሃላፊም ሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት ዘገባውን አጣጥለውታል። ገበያው በቀን ከአስር ሺህ በላይ ጎብኚዎች ነበሩት።
አዳዲሶቹ እገዳዎች ምንድናቸው?
በከተማዋ የሚገኙ 27 ሰፈሮች መካከለኛ ስጋት አለባቸው ተብለው የተለዩ ሲሆን ገበያው አካባቢ የሚገኝ አንድ ሰፈር ደግሞ ከፍተኛ ስጋት አለበት ተብሏል።
በመካከለኛም ሆነ በከፍተኛ ስጋት የሚኖሩ ሰዎች ከተማዋን ለቀው መሄድ አይችሉም። ስጋት በሌለባቸው ሰፈሮች የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደፈለጉት መንቀሳሰቀስ የሚችሉትም ተመርምረው ነፃ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው።
ነገር ግን ምርመራው እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም። ሶስት የመርመሪያ ማዕከላት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምርመራ የሚጀምሩት ከሁለት ሳምንታት በኋላ መሆኑን ነው። በ
ተለያዩ መመርመሪያ ማዕከላትም ሰልፎች ታይተዋል።
በርካታ በረራዎችም የተሰረዙ ሲሆን የባቡር አገልግሎቶችም ለሶስት ሳምንታት ያህል ጉዟቸውን እንዲቀንሱ ተደርጓል።
ተከፍተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ መዋኛ ቦታዎች እንዲሁ እንዲዘጉ ውሳኔ ተላልፏል። ስፖርታዊ ውድድሮችም ተቋርጠዋል።
በከተማዋ እግድ የተላለፈባቸው ሰፈሮች የሚኖሩ ባለስልጣናትም ቢሆኑ መንቀሳቀስ አይችሉም በሚል መንግሥት አስጠንቅቋል።
ነገር ግን መንገዶች ክፍት ሲሆኑ ኩባንያዎችና ፋብሪካዎችም ስራቸውን ቀጥለዋል። ከተማዋ ሁለተኛ ደረጃ ስጋት ውስጥ ናትም ተብሏል።
በቻይና በአጠቃላይ ባለፉት ወራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
ቫይረሱ ከተነሳ ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 80 ሺህ ሲሆን ከዚያም በኋላ የተያዙ ሰዎች 3ሺህ 200 ነው።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ሰላሳ ሁለት የማህበረሰብ ስርጭት በመላው ሃገሪቷ የተመዘገበ ሲሆን 27ቱ በቤጂንግ አራቱ ደግሞ በከተማዋ አቅራቢያ በምትገኝ ሄቤ ግዛት ነው።