ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና 20 የሕንድ ወታደሮችን ድንበር ላይ ገደለች
ሕንድና ቻይና በሥርዓት ባልተማከለው አወዛጋቢ ድንበራቸው አካባቢ ተጋጭተዋል፡፡
ሁለቱ በዓለም በሕዝብ ብዛት 1ኛ እና 2ኛ የሆኑት አገራት በዓለም ረዥም የሚባሉ ድንበሮችን ይጋራሉ፡፡ አሁን የተጋጩበት ድንበር 3500 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ነው፡፡
በዚህ በሂማሊያ ሰንሰለት ድንበር አቅራቢያ የሁለቱ የኒክሌየር ጦር መሣሪያ ታጣቂ አገራት ግጭት የተከሰተው ከእሑድ ጀምሮ ነበር፡፡
ሁለቱ ኃያል አገራት በዚህ መልኩ ሲጋጩ ከ45 ዓመታት ወዲህ የመጀመርያቸው ነው፡፡ ክስተቱ ወደለየለት ጦርነት የሚያስገባቸው ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም በአካባቢው ውጥረት ነግሷል፡፡
የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስትር በጋልዋን ሸለቆ አካባቢ ከዚህ በፊት የተስማማንባቸውን የቁጥጥር መስመሮች ቻይና ጥሳቸዋለች ሲሉ ከሰዋል፡፡
የቢቢሲ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዘጋቢ ጀምስ ሮቢንስ እንደሚለው ይህ በሂማሊያ ሰንሰለታማ ድንበር የተፈጠረው ነገር በዋዛ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጣጣው ለአካባቢው አገራትም ሊተርፍ የሚችል ነው፡፡
ከዚህ በፊት ተጋጭተው ያውቃሉ?
ትናንት ማክሰኞ ጠዋት የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር በካሽሚር ግዛት ላዳካህ በሚባል አካባቢ ሦስት ወታደሮቹ ከቆሰሉበት በኋላ እንደሞቱ ገልጾ ነበር፡፡
ከሰዓት ላይ ሚኒስቴሩ ባወጣው ሌላ መግለጫ ከቻይና ጋር መጠነኛ ግጭት ድንበር አካባቢ መፈጠሩን አመነ፡፡
በዚህ መግለጫው በግጭቱ ቆስለው የነበሩ 17 ወታደሮች መሞታቸውን ይፋ አደረገ፡፡
ቻይና እስካሁን ቆሰለብኝ ወይም ሞተብኝ ያለችው ወታደር ባይኖርም ሕንድ ድንበሬን ጥሳ ገብታለች ስትል ከሳታለች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፈ ቀላጤ ዣዎ ሊዢያን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሰኞ ለታ የሕንድ ወታደሮች ከአንድም ሁለት ጊዜ ድንበር አልፈው ገብተው ነበር፡፡ ይህ ድርጊት የቻይና ወታደሮችን ያስቆጣ ስለነበር በወታደሮቹ መካከል የለየለት ድብድብ ተደርጓል፡፡ ድብድቡ ወደ መሣሪያ ጸብ በመዞሩ ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡
ሕንድ በበኩሏ በዚህ ግጭት ተኩስ አልነበረም ስትል ክዳለች፡፡ ሆኖም እንዴት መሣሪያ መታኮስ በሌለበት ሁኔታ 20 ወታደሮች በድብድብ ብቻ ሊሞቱ እንደቻሉ ለብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
አንዳንድ ምንጮች በዚህ ግጭት ወታደሮቹ በድንጋይ ተፈነካክተው ነው የሞቱት እያሉ ነው፡፡
የሕንድ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው የሕንድ የድንበር ወታደሮች የሞቱት በተኩስ ሳይሆን በቻይና ወታደሮች በድንጋይ ተደብድበው ነው፡፡
ግጭቱ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
ይህ በዓለም ረዥም ከሚባሉ ድንበሮች አንዱ የሆነው የሁለት ኃያላን አገራት ድንበር መልከአ ምድሩ በተራራ፣ በሀይቆችና በጠመዝማዛ ኮረብታዎች የተሞላ ስለሆነ ለቁጥጥር አመቺ ያልሆነ ቀጠና ነው፡፡
በዚህም የተነሳ የሁለቱ አገራት ወታደሮች በብዙ አጋጣሚ አንዱ የአንዱን መስመር ተላልፎ ይገኛል፡፡
ሕንድ የቻይና መንግስት ወደ ላዳካህ ጋልዋን ሸለቆ በርካታ ወታደሮችን እያሰፈረ ነው ስትል ትከሳለች፡፡
‹‹ቻይና የኔ የሆነ 38ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን ይዛብኛለች›› ስትልም ቅሬታ ታቀርባለች፤ ሕንድ፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት ይህን የድንበር ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ ተሞክሮ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሁለቱ አገራት እስከዛሬ የለየለት ጦርነት ያደረጉት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ይህም በአውሮጳዊያን አቆጣጠር በ1962 ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት ሕንድ በቻይና እንዳይሆኑ ሆና ተሸንፋለች፡፡
ባለፈው ግንቦት የሁለቱ አገራት ወታደሮች በሰሜን ምሥራቅ ሲኪም ግዛት ጸብ ፈጥረው መደባደባቸው ተዘግቦ ነበር፡፡
ከዚያ በፊት በ2017 ቻይና አንድ ድንበር ላይ የሚገኘውን መንገድ አስፋፍታ ለመገንባት ስትሞክር ሕንድ ድንበሬን ነክተሸል በሚል ተጣልታት ነበር፡፡
ሕንድ በበኩሏ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደዚህ ሩቅ የድንበር ግዛት የሚወስድ መንገድ መገንባት በመጀመሯ ቤጂንግ ደስተኛ ሳትሆን ቀርታለች፡፡
ይህ የሕንድ መንገድ ግንባታ እና የጦር አየር ማረፊያ ጥርጊያ ግንባታ ወደፊት ግጭት ቢፈጠር ለሕንድ የሎጂስቲክ ጥቅም ይሰጣል ስትል ነው ቻይና የሕንድ ልማትና ብልጽግና ቀልቧ ሊወደው ያልቻለው፡፡
ሕንድ ከቻይና ሌላ በሂማሊያ ክልል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩበትና 140ሺህ ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ካሽሚርን ይገባኛል ስትል ከፓኪስታን ጋር ትፋጠጣለች፡፡
ፕሬዝዳንት ሞዲ የወታደሮቻቸውን ሞት ተከትሎ ወደ ወዳጃቸው ዶናልድ ትራምፕ ስልክ እንደሚደውሉ እየተጠበቀ ነው፡፡
ሕንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነቷን እያጠበቀች ትገኛለች፡፡