ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዳኛ ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተው መሞታቸው ተረጋገጠ
በዲሞክራቲክ ኮንጎ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከነበሩ ግለሰብ ጋር በተያያዘ የቀረበን የሙስና ክስ እያዩ የነበሩት ዳኛ በልብ ድካም መሞታቸው ከተገለፀ በኋላ በተደረገ ምርመራ ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተው በደረሰባቸው ጉዳት መሞታቸውን የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፍትህ ሚኒስትሩ፣ ሴሌስቲን ቱንዳ ያ ካሴንዴ ግድያውን የሚመረምር ቡድን መቋቋሙን አስታውቀዋል።
በግንቦት ወር ዳኛ ራፋኤል ያኚ በልብ ድካም መሞታቸው ተገልጾ ነበር።
እኚህ ግለሰብ ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋር በተያያዘ የቀረበውን የሙስና ክስ እያዩ ነበር ተብሏል።
ነገር ግን የአስከሬን ምርመራ ተደርጎ ጭንቅላታቸው ላይ ስለት ባለው መሳሪያ መመታታቸውንና የሞታቸው መንስኤም ይሄ መሆኑ ተረጋግጧል ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ ሴሌስቴን ቱንዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ማክሰኞ እለት ተናግረዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ አክለውም የሟች አስከሬን ላይ በተደረገው ምርመራ " መርዝ በአነስተኛ መጠን" መገኘቱን አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ካሜሬ፣ በአንድ ወቅት የፕሬዝዳንት ፍሌክስ ሺሴኬዲ መንግሥት ቁልፍ ሰው የነበሩ ሲሆን 50 ሚሊየን ዶላር የሕዝብ ሃብት በመመዝበር ክስ ቀርቦባቸዋል።
ግለሰቡ ግን ምንም አይነት ወንጀል አልፈፀምኩም ሲሉ አስተባብለዋል።
የካሜሬ ደጋፊዎች ክሱ ፖለቲካዊ ሴራ ነው ያሉ ሲሆን ይህም ግለሰቡ ወደፊት ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ ያለመ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ እንዲህ አይነት ክስ ሲቀርብ ካሜሬ የመጀመሪያው ሰው ናቸው።
ይህንን የወንጀል ጉዳይ የሚከታተለው ችሎት ከዳኛው ሞት በኋላም መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።