የትግራይ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር የሚደራደር ቡድን ማቋቋማቸውን ገለጹ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሃያ ወራት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ለሚደረገው ድርድር የሰላም ቡድን መቋቋሙን የህወሓት ቃል አቀባይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናገሩ።

ከትግራይ ክልል ጋር ለሚደረገው ድርድር የመንግሥት ተደራዳሪ ኮሚቴ ሥራ መጀመሩን ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ካደረገው ስብሰባ በኋላ ማስታወቁ ይታወሳል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለድርድር የሚሆን ልዑክ ወደ ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ እንሆናለን ማለታቸውን በዘገባው ያስነበበው ኤአኤፍፒ፣ በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚገኙ አባላት ያሉት ኮሚቴም ተቋቁሟል ብለዋል።

ተደራዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ እንዲሁም ቁጥራቸውን በተመለከተ ግን የተባለ ነገር የለም።

ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ምንም አይነት ድርድር ሊመራ የሚችለው በአፍሪካ ኅብረት ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በኅብረቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ የገለጹት የትግራይ አመራሮች ድርድሩ በኅብረቱ ጥላ ስር ብቻ እንዲሆን እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

“ሁሉንም የድርድር ሂደቶች ለአፍሪካ ኅብረት መስጠቱ ለእኛ በጣም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ማንኛውም ድርድር በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ሚና የተጫወቱትን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ማካተት አለበት ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም የትግራይ አመራሮች የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ያላቸው ቅርበት እንዳሳሰባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ወር ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርና ለሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በላኩት ደብዳቤ ተቋሙ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

“የአፍሪካ ኅብረት በጦርነቱ እንዲሁም በጦር ኃይሎች የደረሰብንን ግፍ እንዳላየ ዝምታን መምረጡ የኅብረቱ መሠረታዊ መርሆች ክህደት ነው። የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር እንዲሁም ከፍተኛ ተወካያቸው በኅብረቱ አሰራር የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤትን የሚያቋቁም ፕሮቶኮል መሰረት አቋም አለመውሰዱን በመጥቀስ የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጡም ስንል በተደጋጋሚ አውግዘናል። በትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት አቋም መሰረት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመራር ከውድቀቶቹ ተምሮ አመኔታውን ለማግኘት ሥራ መስራት አለበት” ብሏል ደብዳቤው።

አቶ ጌታቸው በተጨማሪም በአማራ ክልል ዘንድ የይገባኛል ጥያቄ ያለበትና በአሁኑ ወቅት በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያለው ምዕራብ ትግራይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም በማለት መናገራቸውን ዘገባው አስነብቧል።

ከትግራይ በኩል ከምዕራብ ትግራይ በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለድርድር አይቀርብም በሚል በተደጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ የለም።

የሰላም ውይይቱን በተመለከተ “ሕገ መንግሥታዊነትን ባከበረ፣ የአገርን መሠረታዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ” መሆን እንዳለበት ገዥው ፓርቲ ብልጽግና መወሰኑ ከመግለጽ በተጨማሪ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

በመንግሥት በኩል የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ የአሰራርና ሥነ ምግባር አካሄድ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማስተላፉ እንዲሁም ንዑሳን ኮሚቴዎች መደራጀታቸውንና ኃላፊነት ተከፋፍሎ ሥራ መጀመሩ ባለፈው ሳምንት ተገልጿል።

የመንግሥት ተደራዳሪ ኮሚቴ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን ሰባት አባላት እንዳሉትም ተገልጾ ነበር።

ከአቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኮሚቴው ውስጥ ተካተዋል።

በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር፣ የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ አምባሳደር ሐሰን አብደልቃድር የኮሚቴው አባል ናቸው።

ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር መቼ ውይይት እንደሚጀመርም ሆነ፣ የት ይሆናል የሚለው ላይ እስካሁን ከሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በኩል የተገለጸ መረጃ ባይኖርም ከትግራይ በኩል የኬንያ መዲና ናይሮቢ ትሁን የሚል ላይ ሃሳብ ቀርቧል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብዓዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።