ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው ስለሚደራደሩት ግለሰቦች ምን እናውቃለን?
አስራ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በሰላም ለመቋጨት መንግሥት ከትግራይ አመራሮች ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ወስኖ ቡድን ሰይሟል።
ይህ ተደራዳሪ ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን ሰባት አባላትን ያካተተ መሆኑን መንግሥት አሳውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት የሰላም ጉዳይን የሚመለከት ኮሚቴ ተዋቅሮ አስፈላጊውን ሥራ እያካናወነ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ተከታታይ ስብሰባዎችን ባለፈው ሳምንት ካካሄደ በኋላ ይፋ እንዳደረገው መንግሥት ጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ መወሰኑን አሳውቋል።
የተደራዳሪ ቡድኑ አባልና የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንደተናገሩት፣ ፓርቲው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለሚያበቃበት ድርድር መመሪያዎችን አዘጋጅቶ የቡድኑን አባላት ሰይሟል።
ከትግራይ አመራሮች ጋር የሚደረገው ድርድር ሂደትም በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ እንደሚሆን አቋሙን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድሩ ሰባት አባላት ያሉት ቡድን ያሳወቀ ሲሆን፣ እነዚህ ተደራዳሪዎች እነ ማን ናቸው?
1ኛ. አቶ ደመቀ መኮንን
አቶ ደመቀ መኮንን የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባል ሲሆኑ በአማራ ክልል እንዲሁም በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ቆይተዋል።
አቶ ደመቀ በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ የሰሩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ ለረጅም ዓመታት ወዳገለገሉበት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስተርነት ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ደመቀ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ በአገሪቱ የሥልጣን እርከን ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለው ሁለተኛው ከፍተኛ መሪ ናቸው። አቶ ደመቀ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ውስጥ ቁልፍ የሆኑትን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን አጣምረው ይዘዋል።
2ኛ. ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ
ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከተሾሙ ወጣት ሚኒስትሮች መካከል አንዱ እንደሆኑ ይነገራል።
ዶ/ር ጌዲዮን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአሁኑ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በሕግ መምህርነት ሰፊ ልምድን አዳብረዋል።
ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በዚህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርስቲ፣ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ እና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተለያዩ የሕግ ዘርፎችን አስተምረዋል።
በሕግ ዘርፍ ከሚጠቀሱ ምሁራን መካከል የሆኑት ዶ/ር ጌዲዮን ለረጅም ጊዜ ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት የረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
3ኛ. አቶ ተመስገን ጥሩነህ
አቶ ተመስገን በአማራ ክልል እስከ ፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል።
በዚህም በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና የቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ሰርተዋል።
በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ እስከ ሻለቃ ማዕረግ የደረሱት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የሠራዊቱ የመረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊም ነበሩ።
አቶ ተመስገን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) መሥራቾች ከሆኑት አንዱ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተቋሙ ውስጥ ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ባሉት ኃላፊነቶች ሰርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም በሚንስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
ከዚያም በኋላ በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ቀውስ ሳቢያ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ የርዕሰ መስተደደርነት ኃላፊነትን በመያዝ ለተወሰነ ጊዜ ሠርተዋል።
ወደ ፌደራል መንግሥቱ መዋቅር የተመለሱት የአገሪቱ ዋነኛ የደኅንነት ተቋም የሆነውን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ነው። አሁንም የተቋሙ መሪ ናቸው።
4ኛ. አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በደቡብ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና በፌደራል በተለያዩ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገለግለዋል።
በፓርቲው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የቆዩት አምባሳደር ሬድዋን ከዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘዋውረው ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሲያድሱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በአሥመራ ሠርተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ከአሥመራ መልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ላለፉት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ለዲፕሎማቶችና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመንግሥትን አቋም በማስረዳት ከፊት ቀዳሚው ናቸው።
አምባሳደር ሬድዋን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንት ጉዳዮች አማካሪ እንዲሆኑ መሾማቸው ይታወሳል።
5ኛ. ሌ/ ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ
የሪፐብሊካን ጋርድ ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ በቀለ፣ በመከላከያ ውስጥ ላለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
በአሁኑ ሰዓትም የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ናቸው።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይም በራያ እንዲሁም በምዕራብ ግንባር ተሳትፎ እንደነበራቸው ይነገራል።
በዚህ ዘመቻ ውስጥ ባበረከቱት አስተዋጽኦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት አድናቆት ከተቸራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል አንዱ ናቸው።
6ኛ. ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር
ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር የአማራ ክልል ውስጥ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቀት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ናቸው።
ዶ/ር ጌታቸው አሁን ካሉበት ከፍተኛው የክልሉ የመሪነት ኃላፊነት ቀደም ብለው የክልሉ የውሃ ሀብት ልማት ቢሮ እና የሙያና ቴክኒክ ቢሮዎችን በኃላፊነት መርተዋል።
7ኛ. አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር
አምባሳደር ሐሰን በከፍተኛ የመንግሥት አመራር ላይ ስለነበራቸው ሚና የሚገልጽ መረጃ ባይገኝም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማቲክ ዘርፍ ውስጥ መስራታቸውን አንዳንድ ምንጮች ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅትም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰሩ ያሉት አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ውስጥ የቦርድ አባል ናቸው።