ቡና እንዴት በዓለማችን በብዙዎች የሚወደድ አነቃቂ ፍሬ ሊሆን ቻለ?

አንድ ስኒ ቡና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንቅልፍ ከማትተኛው የኒው ዮርክ ከተማ እስከ ኢትዮጵያ ተራሮች ድረስ ዝናው የናኘ ነው፤ ቡና። ሚሊዮኖች ሳይጎነጩት መዋል አይቻላቸውም።

ቡና ለ15 ክፍለ ዘመናት የሰው ልጆች ባህል ማዕከል ሆኖ ኖሯል። አንዳንዶች የ17ኛው እና የ18ኛው ክፍለ ዘመን አብርሆት ከቡና ነው የመነጨው ይላሉ።

ዘመነ አብርሆት (ኢንላይትንመንት) የዘመናዊውን ዓለም ባህላዊ እና ፍልስፍናዊ ርዕዮተ-ዓለም የቀረፁ ሐሳቦች የፈለቁበት ጊዜ ነው።

ቡና ውስጥ ያለው አነቃቂ ንጥረ-ነገር ካፌይን ይባላል። ቡና በዓለማችን ካሉ እጅግ አነቃቂ ዕፆች በጣም በርካታ ተጠቃሚ ያለው ነው። አስተሳሰባችንን ሳይቀር እንደሚቀምር ይታሰባል።

ቡና ከየት መጣ?

ቡና ኮፊያ አራቢካ ከተሰኘው ተክል የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ተክል ደግሞ መጀመሪያ የተገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

90 በመቶ የሚሆነው ቡና የሚመረተው እያደጉ ናቸው በሚባሉ አገራት በተለይም ደግሞ በደቡብ አሜሪካ ሲሆን፣ በተቃራኒው አብዛኛው ቡና ጠጪ የሚገኘው በኢንዱስትሪ ዘርፍ ልኅቀት ባሳዩ አገራት ነው።

አፈ-ታሪክ እንደሚለው በ9ኛው ክፍለ ዘመን ካልዲ የተባለው እረኛ ፍየል እየጠበቀ ሳለ ነው ፍየሎቹ የቡና ፍሬ በልተው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሲንቀለቀሉ ያስተዋለው። ካልዲ ይህን ሲመለከት እኔም ልሞክረው ብሎ ፍሬውን መቅመሱ ይነገራል።

ከዚያ በኋላ ነው የአካባቢው ሰዎች የቡና ፍሬን እየዘፈዘፉ፤ ቅጠሉን ደግሞ እየቀቀሉ እንደ ሻይ መጠጣት የጀመሩት።

ታሪካዊ መዛግብት እንደሚያስረዱት የየመን ሱፊዎች ናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የቡና ፍሬን ቆልተው፣ ፈጭተው አሁን እንደምናውቀው ያለ ቡና የጠጡት።

በ15ኛው ክፍለ ዘመን በኦቶማን ግዛተ መንግሥት (ኢምፓየር) ወቅት የቡና መሸጫዎች መታየት ጀመሩ። ይህ ወደ አውሮፓ ተስፋፍቶ ቡና ቤቶች የቢዝነስ፣ የፖለቲካ እና የአዳዲስ ሐሳቦች መፍለቂያ ሆኑ።

የቡና ፍሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኮፊያ አራቢካ የተሰኘው የቡና ተክል መጀመሪያ የተገኘው ኢትዮጵያ ነው

ጀርመናዊውን ፈላስፋ የርገን ሀበርማስን ጨምሮ ሌሎች ተመራማሪዎች እና የ20ኛው ክፍለ-ዘመን የማኅበረሰብ ጥናት ምሑራን (ሶሺዮሎጂስት) የአብርሆት ዘመን ያለ ቡና እውን አይሆንም ነበር ሲሉ ይከራከራሉ።

ሀበርማስ እንደሚለው በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን ቡና መሸጫ ቤቶች “የሒስ ማዕከል” ከመሆን አልፈው ሰዎች ሐሳባቸውን እና አስተያየታቸውን የሚያንሸራሽሩባቸው ሥፍራዎች ነበሩ።

የአብርሆት ዘመን ፈላስፎች ጠንካራ የቡና ሱስ ነበረባቸው የሚሉ መላ ምቶችም ይሰነዘራሉ።

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴይር በቀን 72 ሲኒ ቡና ይጠጣ እንደነበር፤ ጓደኛው ዲዴሮትም 28 ክፍሎች ያሉትን “ኢንሳይክሎፒዲያ” ለመፃፍ ቡናን ያዘወትር እንደነበር ይነገራል።

አሜሪካዊው ፀሐፊ ማይክል ፖላን፤ ኢንሳይክሎፒዲያ የአብርሆት ዘመን ድንቅ ሥራ ነው ይላል።

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴይር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴይር በቀን 72 ሲኒ ቡና ይጠጣ ነበር

የአንትሮፖሎጂ (የሰው ልጅ ጥናት) ፈላስፋው ቴድ ፊሸር በዩናይትደ ስቴትስ ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የቡና ጥናት ዳይሬክተር ናቸው። ምሑሩ፤ ቡና ለካፒታሊዝም ርዕዮተ-ዓለም መበልፀግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ይላሉ።

“ቡና ታሪክን የቀየረ እና እንደ ኢንላይትንመንት እና ካፒታሊዝም ያሉ ሐሳቦች እንዲያድጉ ያደረገ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“ስለ ዲሞክራሲ፣ አመክንዮ፣ ሳይንስ፣ እና ካፒታሊዝም ያሉ ሐሳቦች ቡና በጣም በተለመደበት ወቅት መፍለቃቸው፤ እንዲሁ መገጣጠም ነው ብዬ አላስብም። ቡና ነገሮችን የምናይበትን መነፅር ያሰፋል፤ ትኩረታችንን ይሰበስባል። ለካፒታሊዝም ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብዬ አስባለሁ።”

ወቅቱም ነጋዴዎች ቡና ውጤታማነትን እንደሚጨምር ያወቁበት ጊዜ ነበር የሚሉት ፊሸር፤ ለሠራተኞቻቸው የቡና እረፍት ይሰጧቸው እንደነበርም ይናገራሉ።

የቡና ያልተነገረ ጉድ

የቡና ታሪክ ከወቀሳ የፀዳ አይደለም፤ ምክንያቱም ለባሪያ ንግድ መስፋፋት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷልና።

ፈረንሳውያን ከአፍሪካ ያመጧቸውን ባሪያዎች ሄይቲ ውስጥ የቡና እርሻ ላይ ያሠሯቸው ነበር። በ1800ዎቹ ደግሞ ብራዚል ውስጥ የአፍሪካ ባሪያዎች የሚያመርቱት ቡና ከዓለም አንድ ሦስተኛውን ይሸፍን ነበር።

ባለንበት ዘመን ቡና የዓለም አቀፍ ባህል የማዕዘን ድንጋይ ነው። በየቀኑ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ስኒ ቡና ይጠጣል። ለዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት በየዓመቱ ከ90 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያበረክታል።

ቢሆንም “አሁንም ገና ብዙ ይቀራል” የሚለው ሃይፈር ኢንተርናሽናል የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድህነት እና ረሃብን ለማጥፋት የሚሠራ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ እንደሚለው ጥቁር እና ቡና ቀለም ያላቸው ሰዎች የቡና ኢንዱስትሪ የጀርባ አጥንት ቢሆኑም፣ የሚከፈላቸው በጣም ትንሽ ነው።

በ50 አገራት ያሉ 125 ሚሊዮን ሰዎች የቡና ኢንዱስትሪ የገቢ ምንጫቸው ቢሆንም፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን አሁንም ድኅነት ቀፍድዶ ይዟቸዋል።

ቡና በሰውነታችን እንዴት ይሰራጫል?

ካፌይን የተባለው ንጥረ-ነገር ወደ ሰውነታችን ሲዘልቅ ምግብ በሚያልመው ሥርዓት በኩል አልፎ በአንጀት አድርጎ የደም ዝውውራችን ጋር ይደርሳል።

ነገር ግን ሥራውን መሥራት የሚጀምረው የነርቭ ሥርዓታችን ጋር ሲደርስ ነው።

ካፌይን፤ አዴኖሳይን ከተሰኘው ሰውነታችን የሚያመነጨው ያለ ንጥረ ጋር ተመሳሳይነት አለው። አዴኖሳይድ የነርቨ ሥርዓትን በማረጋጋት የልብ-ምት እንዲረጋጋ እና የመዝናናት መጠናችን ከፍ እንዲል የማድረግ አቅም አለው።

ካፌይን ከአዴኖሳይን ጋር ሲደባለቅ የልብ-ምታችን ይጨምራል፣ አእምሯችን ፈጣን ይሆናል፣ የረሃብ ስሜት ይጠፋ እና ንቁ ያደርገናል። ለዚህ ነው የትኩረት መጠናችን ከሌላው ጊዜ የላቀ የሚሆነው።

ካፌይን ‘ሙድ’ የመቀየር ኃይል አለው። ድካም ይቀንሳል፤ አካላዊ ብቃትን ከፍ ስለሚያደርግ አትሌቶች ብዙ ጊዜ ሲጠቀሙት ይስተዋላል።

የካፌይን ኃይል ከ15 ደቂቃ እስከ 2 ሰዓት ድረስ ሊቆይ ይችላል። ሰውነታችን ካፌይንን ከ5 አስከ 10 ሰዓታት ባለው ጊዜ ቢያስወግደውም ከዚህም በላይ ሊቆይ ይችላል።

ቡና ሲቀዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዘርፉ ሰዎቸ ቀን አራት ወይም አምስት ስኒ ቡና በቂ ነው ይላሉ

ባለሙያዎች፤ የካፌይንን ጥቅም ከፍ ለማድረግ በመጠኑ መውሰድ እና ከሰዓት ከመጠጣት ይልቅ በነጋታው ጠዋት በመጠጣት የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ይላሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች ለአንድ ሰው በቀን 400 ሚሊ ግራም ካፌይን በቂ ነው ይላሉ። ይህ ማለት በቀን አራት ወይም አምስት ስኒ ቡና ማለት ነው።

እርግጥ ነው እንደ ሰው ሊለያይ ይችላል፤ ነገር ግን ይህን መጠን ማለፍ የእንቅልፍ እጦት፣ ጭንቀት፣ የሆድ ህመም፣ የልብ ምት መጨመር እና ራስ ምታት ሊያስከትል ይችላል።

የአሜሪካው ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ተመራማሪዎች ደግሞ 1200 ሚሊ ግራም ቡና (12 ሲኒ) በፍጥነት ከወሰድን ሰውነታችን ከቁጥጥራችን ውጪ ሊንቀጠቀጥ ይችላል ይላሉ።

ቡና በመጠኑ መጠጣት ግን የጤና ጥቅም ከመስጠቱ በተጨማሪ ከበሽታ የመከላከል አቅም ያጎለብታል የሚሉት የቲኤች ሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዶክተሩ ማቲያስ ሄን ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት “በቀን ከሁሉት እስከ አምስት ሲኒ ቡና መጠጣት ከስኳር ህመም፣ ከልብ ሕመም እና ከአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ሊታደገን ይችላል።”