ከወራት በፊት ተሰርዞ የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዛሬ እንደሚወጣ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office Of Addis Ababa
በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ላይ ባጋጠመ ማጭበርበር ከወራት በፊት ተሰርዞ የነበረው ዕጣ ዛሬ ህዳር 6፣ 2015 ዓ.ም እንደሚወጣ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዳስታወቀው በዛሬው ዕለት ስምንት ሰዓት የሚከናወነው የዕጣ ስነ ስርዓት 25 ሺህ 791 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለቆጣቢዎች ያስረክባል።
ለቆጣቢዎች የሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በ20/80 ፣ 18 ሺህ 930 እንዲሁም በ40/ 60፣ 6 ሺህ 843 ቤቶች መሆናቸውንም ከአዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
በተጨማሪም ከፍተኛ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ባለ ሶስት መኝታ ቤቶችም በዛሬው ዕጣ መካተታቸው ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ቢወጣባቸው ከፍተኛ ማጭበርበርና ሙስና ተፈጽሞባቸው በሚል ኦዲት ተደርጎ እጣው ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ መደረጉን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ያስሚን ዋሃቢረቢ መጥቀሳቸው ተገልጿል።
በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ አካላትም በህግ ተጠያቂ መሆናቸውም ተገልጿል።
በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነውና ውዝግብ ባስከተለው ዕጣ ውስጥ መሳተፍ የነበረባቸው 79 ሺህ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ቢሆኑም፣ በድብቅ የተዘጋጁ 172 ሺህ ያህል ሰዎች በዕጣው ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርገዋል ተብሏል።
በዚህም 93 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተገቢ ባልሆነ መንገድ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት በተዘጋጀው ዕጣ ውስጥ መካተታቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ የተፈጠሩ ችግሮቹን አርሞ ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ የእጣ ማውጫ ስርዓቱን በማልማት የመረጃ ማጥራትና ማደራጀት ስራና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል።
ከእጣ ማውጫ ስርዓቱ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ለውጥ ያስረዱት ኃላፊዋ የቤት ዕጣ ማውጫ ስርዓቱ በአዲስ መልክ ከፍተኛ ልምድ ባለው በኢንፎርሜሽንመረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንዲለማ መደረጉም ተጠቅሷል።
የዕጣ ማውጫ ስርዓቱን በድጋሚ የመፈተሽ ስራውንም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ፣ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር ተቋማት የተውጣጣ ቴክኒካል ኮሚቴ በመስራት አረጋግጧል ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ዕጣ የሚወጣላቸው 20/ 80 ስቱዲዮ ባለ 1 እና ባለ 2 ነባር ተመዝጋቢዎችና ዝቅተኛውን ለ60 ወራት የቆጠቡ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባለ 3 መኝታ ነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች፣ ዝቅተኛውን የ84 ወራት ቁጠባ መጠን ያሟሉ ናቸው።
የ40/ 60 ተመዝጋቢዎች ከ40 በመቶ እና ከዚያ በላይ የቆጠቡ እንደሆኑ የገለጹት ዳይሬክተሩ ከባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት በ20/ 80፣ 93 ሺህ 352፣ በ40/ 60 ቤቶች 53 ሺህ 540 በአጠቃላይ 146 ሺህ 892 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ተብሏል።












