በሺዎች የሚቆጠሩ ከ20 በላይ አገራት ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁለት ሳምንት ሊሞላው የተቃረበውን በሱዳን ውስጥ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭትን በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጸ።
የተለያዩ ወታደራዊ ኃይሎችን በሚመሩት በሁለቱ የሱዳን ኃያላን ጄኔራሎች መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ፉክክር ምክንያት በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ አገሪቱ ከባድ ግጭት ውስጥ ገብታለች።
በተለይ ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በአገሪቱ ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በተደረጉ ውጊያዎች ምክንያት ከባድ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።
ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና ዜጎች በየብስ እና በአየር ሱዳንን እየለቀቁ በመውጣት ላይ ሲሆኑ፣ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች የሱዳን አጎራባች ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ከምትዋሰንባቸው ክልሎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከሃያ በላይ የሆኑ አገራት ዜጎች ባለፉት ቀናት ከሱዳን ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ኢትዮጵያውያንም በሱዳን የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ በተጨማሪም በርካታ የሱዳን፣ የቱርክ እና የየመን ዜጎችን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዜጎች በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር በኩል ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን አቶ ግዛቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በሱዳን ያለውን ግጭት በመሸሽ ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ የ23 አገራት ዜጎች መግባታቸውን እና ከዚያም በመነሳት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተጓዙ መሆናቸውን ዞኑ አመልክቷል።
ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ሰዎች መካከል ህፃናት፣ ሴቶች እና አቅመ ደካሞች የሚገኙበት ሲሆን፤ ከድንበር መተላለፊያው የመተማ ዮሐንስ ከተማ በመነሳት በርካታ ሰዎችን የያዙ አስከ 20 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ጎንደር እየሄዱ መሆናቸውም ተገልጿል።
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉትን የተለያዩ ዜጎችን ከመቀበል ባሻገር ጊዜያዊ መጠለያ እና ምግብ እየቀረበላቸው መሆኑን የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት አውሮፕላኖቻቸውን ወደ ሱዳን በመላክ ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን ከዋና ከተማዋ ካርቱም ለማስወጣት የቻሉ ሲሆን፣ ይኸው ተግባርም አሁንም መቀጠሉ ተነግሯል።
በተለይ ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በተፋላሚዎቹ ኃይሎች መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በመጠቀም አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን እያስወጡ ይገኛሉ።
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ የተፈጠሩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም አስከ ማክሰኞ ድረስ የተለያዩ አገራት ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣት መቻላቸው የተለያዩ ምንጮች ዘግበዋል።
በጄኔራል አል ቡርሐን እና በጄኔራል ሔሜቲ በሚመሩት ኃይሎች መካከል በተካሄዱት ውጊያዎች አስካሁን 264 ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ከ420 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። እንዲሁም ከ3,700 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት ሱዳን ውስጥ ከተፈጠረው ወታደራዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ ቢያንስ የስምንት ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉን እና አራት መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቢቢሲ አሳውቋል።
በተፋላሚ ኃይሎቹ ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አስፈላጊውን በማድረግ ላይ መሆኑም ተነግሯል።
ከአል በሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ የአገሪቱ ዋነኛ የሥልጣን አካል የሆነውን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤትን በሊቀመንበርነት እና በምክትልነት በሚመሩት ወታደራዊ ጄኔራሎች መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽሚያ ሳቢያ ሱዳን ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
ግጭቱ በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን በሚመራው የአገሪቱ ጦር እና በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሔሜቲ በሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ጄኔራሎቹ አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር በተያዘው ዕቅድ ላይ ሳይግባቡ ቆይተው ወደ ግጭት አምርተዋል።
ለቀናት በጦር አውሮፕላኖች ጭምር በተደረገው ውጊያ ሱዳናውያን የመሠረታዊ ፍላጎቶች እና የኤሌክትሪክ አቅርቦቶች ተቋርጠውባቸዋል።
ለሦስት ቀናት ይቆያል የተባለውን የተኩስ አቁም ተጠቅመው ከዲፕሎማቶች እና ከውጭ ዜጎች በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ከአገራቸው ለመውጣት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ተዘግቧል።












