የጀርመን አካል ሆና ለጀርመን ዕውቅና ያልሰጠቸው 'ቀበሌ'

ራሱን 'ቀዳማዊ ንጉሥ ጴጥሮስ' ብሎ የሚጠራው ፒተር ይህ ነው
የምስሉ መግለጫ, ራሱን 'ቀዳማዊ ንጉሥ ጴጥሮስ' ብሎ የሚጠራው የቀበሌዋ አስተዳዳሪ ይህ ነው

ሰሞኑን በጀርመን መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ተጎንጉኗል በሚል በርካቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ይህ የአፍሪካ ብቻ ዜና የሚመስለው ነገር እንዴት በጀርመን ተሰማ ያሉ ብዙ ናቸው።

በምሥራቅ ጀርመን የምትገኘውን ‘ደችላንድ’ ስለማያውቋት ነው እንደዚያ ያሉት። የዚህ መንደር ልብ ተራራ ነው።

ይቺ ትንሽ ቀበሌ ራሷን 'የጀርምን ሥርወ መንግሥት' እያለች ነው የምትጠራው። የሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት ጎንጓኞች የዚህች ቀበሌ አማኞች እንደሆኑ ይጠረጠራል።

ወደዚች መንደር ስትጠጉ ያልተሰመረ ድንበር አለ፤ የማይታይ። በሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ የሚኖር።

ቀበሌዋ መግቢያ ላይ የተሰቀለው ማስታወቂያ ‘እንኳን ወደ ጀርመን ግዛት በሰላም መጡ’ ይላል። በአገሬው ቋንቋ እንዲህ ይላል።

Königreich Deutschland- የደቾች አገር፤ የደቾች ምደር እንደማለት ነው።

የጀርመን ሥርወ መንግሥት ብለው ራሳቸውን ሲጠሩ በታላቅ ኩራት ነው። ይህ ለብዙዎች ፌዝ ሊሆን ይችላል፤ ለቀበሌዋ ነዋሪዎች ግን የምር ነው። የራሳቸው ንጉሥ ሁሉ አላቸው።

የንጉሡ ስም ‘ቀዳማዊ ንጉሥ ጴጥሮስ” ይባላል።

ይህ ንጉሥ የቢቢሲ ጋዜጠኞች መሆናችንን አውቆ በታላቅ አክብሮት ጣሪያና ግድግዳው በጣውላ በተሠራ አዳራሽ ተቀበለን።

ልብ ልትሉ የሚገባው ታዲያ 'ቀዳማዊ ጴጥሮስ' በዚህች ጠባብ አዳራሽ ነበር ከ12 ዓመት በፊት በዓለ ሲመቱ የተከናወነው።

በዓለ ሲመቱን ያከናወኑለት መቶ የማይሞሉ የቀበሌዋ ነዋሪዎች ናቸው። በቃ ንጉሣችን አንተ ነህ አሉት። 'ዓለምን የተሻለች ላደርጋት ቃል ገብቻለሁ' አላቸው።

ከዚያ ወዲያ ባሉ ዓመታት ታዲያ ለዋናዋ አገር ለጀርመን ብዙም ዕውቅና ሳይሰጥ፣ ብዙም ፊት ሳይሰጥ ራሱን 'ንጉሥ' አድርጎ ቀበሌዋን ቀጥ አድርጎ እየመራት ይገኛል።

የራሱን መገበያያ ገንዘብ ሁሉ ማተም ጀምሯል። የቀበሌዋ ነዋሪዎች የራሳቸው ባንዲራ አላቸው። የራሳቸው የዜግነት መታወቂያም ማተም ጀምረዋል። ወደየትም ባይወስድም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብዙዎቹ ጀርመናዊያን 'ቀዳማዊ ንጉሥ ጴጥሮስንና ተከታዮቹን የቀልድና ቧልት ምንጫቸው አድርገው ነበር የሚያይዋቸው። እስከባለፈው ሳምንት ድረስ።

በጀርመን ሊፈጸም የነበረው መፈንቅለ መንግሥት ሴራው የተጠነሰሰው ከዚህ ንጉሥ ተከታዮች መካከል ባሉ ሴረኞች እንደሆነ ከተነገረ በኋላ ግን ከባድ ድንጋጤ ተፈጥሯል።

‘ንጉሥ ቀዳማዊ ጴጥሮስ’ ግን በነገሩ የለሁበትም፤ እጄ ንጹሕ ነው ብሏል።

ይህ መንደርና ተከታዮቹ ዓለም በውሸታሞችና ገንዘብ አምላኪዎች እየተሽከረከረች ነው ብሎ ያምናል።

በዓለም ላይ የሚመረቱ መድኃኒቶች ዉሸት ናቸው ብለው ያምናሉ።

ለምሳሌ በመንደሪቱ ያሉ ‘ዜጎች’ አንዳቸውም የኮቪድ-19 ክትባት አልወሰዱም። 

እንዲያውም በካፒታሊዝም ሥርዓት በፍጹም አያምኑም። 

ቀዳማዊ ጴጥሮስ አሁን 'ዜጎቼ' የሚላቸው ተከታዮቹ 5ሺህ ደርሰውልኛል ይላል።

የጀርመን ፖሊስ ግን እነዚህ ሰዎች አሻጥረኞች ናቸው ይላቸዋል። በሳይንስ አያምኑም።

አሁን ዓለም ላይ በቆመው የአስተዳደር ሥርዓት አያምኑም።

ካፒታሊዝም ጥቂቶችን ለማበልጸግ፤ ሰፊውን ሕዝብ ለማቆርቆዝ ነው የተዋቀረው ይላሉ። 

እነዚህ የማይጨበጥ ‘አሻጥር ሽረባ’ አማኞች 21ሺህ ደርሰዋል ይላል ፖሊስ።

ባለፈው ሳምንት ፖሊስ 25 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። የጀርመን ፓርላማን ለማውደም፤ መራሔ መንግሥቱንና ሚኒስትሮቻቸውን ለመግደል ሲያሴሩ ነበር ይላል ፖሊስ። 

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ራሱን ‘ንጉሥ ጴጥሮስ ቀዳማዊ’ ብሎ ከሚጠራው ሰው ጋር ጉብኝት እያደረጉ ነው።

ሆኖም አንድ ሰው እየተከታተለ ሁሉን ነገር ይቀርጻል።

ለምን ሁሉ ነገር እንደሚቀረጽ ሲጠየቅ ቀሪው ዓለም ስለኛ የሚያሰራጨውን የሐሰት መረጃ ለመቋቋም ነው ይላል። 

የራሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመጀመርም እየተሰናዳ ነው።

የዚህ ንጉሥ ነኝ ባይ ዕውነተኛ ስም ፒተር ፊዘር ነው።

ከዚህ ቀደም ከንቲባ ለመሆን ተወዳድሯል። ፓርላማ ለመግባት ተወዳድሯል። አልተሳካለትም። 

ያልተሳካልኝ የተገነባዋው ሥርዓት እኔን ለመቀበል ዝግጁ ስላልሆነ ነው፤ ዓለም ለለውጥ ግዝጁ አይደለም ይላል።

የመገበያያ ገንዘባቸው ይህን ይመስላል
የምስሉ መግለጫ, የቀበሌዋ ነዋሪዎች የራሳችን የሚሉት ገንዘብም ማተም ጀምረዋል

ከዚያ ወዲያ ነበር የራሱን 'ጀርመን' በራሱ አምሳያ ለመፍጠር የተነሳው። 

ለእሱ ትክክለኛዋ የጀርመን ሥርወ መንግሥት እሱ የመሠረታት መንደር ናት። 

እርግጥ ነው ጀርመን እንዲህ ዓይነት ራሱን የቻለ ትንሽ መንግሥት መመሥረትን አትፈቅድም።

ነገር ግን መንደሪቱ የሕግ ክፍተቶችን በመጠቀም፣ የራሷ የጤና ሥርዓት እስከመመሥረት ደርሳለች። 

ፒተር መኪና ሲያሽከረክር ያለ መንጃ ፍቃድ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ተከሷል። ለዓመታት እስር ቤት ተወርውሯል።

‘ዜጎቼ’ የሚላቸው ተከታዯቹን አጭበርብሯል በሚልም ዘብጥያ ወርዷል።

ይህን ሁሉ አልፎ አዲስ ሥርዓት- አዲስ ግዛት ለመመሥረት ይታትራል።

 አሁን ቀን ተሌት የጀርመን ፖሊስ ይከታተለዋል።

እሱ ግን የንግሥና ክብሩን ጠብቆ ‘ዜጎቼ’ ለሚላቸው፤ ለሚያምኑትና ለሚያምናቸው ሰዎች ማገልገሉን ቀጥሎበታል።

ዜጎቼ የሚላቸው በካፒታሊዝም ሥርዓት ማመን የተውትን ነው። በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከታዮቹን ብዛት እጥፍ አድርጎለታል።

ሰዎች ክትባት መከተብ እንደሌለባቸው ይመክራል።

አሁን ባለው ገንዘብ ሰፋፊ መሬት እየገዛ 'የጀርመን ሥርወ መንግሥትን' እያፋፋ ነው።

አዲሱ የጀርመን ሥርወ መንግሥት ሰዎች የማይበዘበዙበት፤ ደስታና ፍሰሐ የሚዘንብበት ይሆናል ይላል።

ከነዚህ ግዛቴ ከሚላቸው አንዱ ባርዋልዴ መንደር ይባላል። ከበርሊን ወደ ደቡብ የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ ነው።

ቤቶቹ አሮጌና ጥንታዊ ናቸው። ሆኖም ነዋሪዎች ደስተኞችና ተስፈኞች ይመስላሉ።

ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አይልኩም። ግብር አይከፍሉም። በጀርመን ሁለቱም ከባድ ወንጀሎች ናቸው።

እንዴት እንደሚያመልጧቸው እንጃ።

'ንጉሥ ጴጥሮስ ቀዳማዊ’ እንደሚለው አሁን የራሳቸውን የጤናና የሕግ ሥርዓት እያበጁ ነው።

የርሱ አስተዳደር ለ 'ዜጎቹ' አስፈላጊውን ምግብ ያቀርባል።

አሁን በቀጣይነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ዘላቂ አረንጓዴ ልማት ለማምጣት፤ የራሳቸውን መድኃኒት ለማምረት ዕቅድ አላቸው።

“እኛን ብዙ ሰው የሴራ ተንታኞች አድርጎ እያሰበ ያወግዘናል፤ ስለ ዓለም በተጨነቅን፤ ስለ ሕዝብ ባሰብን እንወገዛለን፤ ነገር ግን ብዙዎቻችን ማታ ሲያቃዠን የሚውለው የግል ጉዳያችን ሳይሆን የኅብረተሰብ ችግር ነው” ይላል።

እነ ‘ንጉሥ ጴጥሮስ ቀዳማዊ’ና ተከታዮቹ ለጀርመን ብሔራዊ ቧልቶች ሆነው ቆይተዋል። ከዚህ ወዲያ ግን እንዲያ አይቀጥልም።

ምክንያቱም ሁሉም ነገር ሲጠነሰስ እንዲያ ነበር።

ሒትለርም ከአንድ ስብሰባ ተነስቶ ነው ዓለምን በእሳት የቀቀለው።

ይህ ደግሞ ለጀርመናዊያን የ80 ዓመት መጥፎ ትዝታ ነው።