አሜሪካ፡ ‘ለሩሲያ ዋንኛ የጦር መሣሪያ አቅራቢ ኢራን እንደሆነች ደርሼበታለሁ’

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ፣ ኢራን የሩሲያ ዋንኛ የጦር መሣሪያ አቅራቢ እንደሆነች አስታወቀች።
እንደ አሜሪካ ከሆነ የሩሲያና የኢራን ወታደራዊ ግንኙነት አሁን አሁን ወደ ሙሉ የጦር አጋርነት እያደገ ይመስላል።
የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንደተናገሩት ሩሲያም ቢሆን ለኢራን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገችላት ነው።
አውስትራሊያ በበኩሏ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሦስት ኢራናዊያን ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጥያለሁ በላለች።
ከዚህ ሌላ አንድ የኢራን ቢዝነስ ላይ ተመሳሳይ ማዕቀብ ጥላለች።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ ድሮን ያቀርባሉ በሚል ነው።
ዩክሬን፣ "እየተደበደብኩ ያለሁት በኢራን ድሮን ነው" የሚል ክስ ማቅረብ ከጀመረች ወዲህ የሩሲያና የኢራን ወታደራዊ ግንኙነት እስከምን ድረስ ነው የሚል ጥያቄን ጭሯል።
ኢራን ለዚህ ክስ መጀመርያ አካባቢ "ፍጹም ሐሰት ነው" የሚል ምላሽ ሰጥታ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ ግን ለሩሲያ ድሮን ሰጥቻለሁ፤ ነገር ግን ድሮኖቹን የሸጥኩላት የዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ነው ብላለች።
ጆን ኪርቢ እንደሚሉት የሩሲያና የኢራን ወታደራዊ ወዳጅነት፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ሰላም ስጋት ነው።
ሩሲያ ከኢራን ጋር አዳዲስ የጦር መሣሪያ ምህንድስና ላይ ትብብር ማድረግ ትፈልጋለች፤ እንደ የአሜሪካ የደኅንነት ምንጮች መረጃ ከሆነ።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢራን የሩሲያ ቁጥር አንድ የጦር መሣሪያ አቅራቢዋና ደጋፊዋ ሆናለች ነው የሚሉት ኪርቢ።
በቅርቡ የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማቶች ከጥቅም ውጭ ያደረጉት ድሮኖች አብዛኛዎቹ የኢራን እንደሆኑ ደርሰንበታልም ብለዋል።
ይህን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ ዩክሬናዊያን በዚህ ክረምት ያለ ማሞቅያ በውርጭ እየተንዘፈዘፉ ለመኖር ተገደዋል።
የኃይል አቅርቦቱ በዋና ከተማዋ ኪየቭ ጭምር የተቆራረጠ ነው።
ሩሲያ ይህን በዩክሬን የኃይል አቅርቦት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የፈጸመችው ኬርሶን ከተማን ለቃ ከወጣች በኋላ በበቀል ስሜት ነው።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ክሌቨርሊ በበኩላቸው የኢራንና የሩሲያ ወታደራዊ ጥምረት ሊያሳስበን ይገባል፤ ለዓለም ሰላም ጸር ነው ብለዋል።
ጄምስ፤ ኢራን በርካታ ድሮኖችን ለሩሲያ አቅርባለች ሲሉም ከሰዋል። በምላሹ ደግሞ ሩሲያ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለኢራን አቅርባለች ይላሉ።
ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን በመፈለጓ ከኢራን ጋር ተወዳጅታለች ሲሉም ከሰዋል።
ዩክሬን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሱባት ያሉትን ‘ካሚካዚ’ የሚባሉትን ድሮኖች ለሩሲያ የሰጠችብኝ ኢራን ናት ስትል ከሳለች።
እነዚህ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በጥቅምት ወር 8 ዩክሬናዊያንን ገድለዋል። በመሠረተ ልማቶች ላይም መጠነ ሰፊ ጥፋት አድርሰዋል።
ኢራን ካሚካዚዎቹ የኔ አይደሉም’ ብላ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ጦርነቱ ከመጀረሙ ብዙ ወራት በፊት ነው ለሩሲያ የሸጥኩላት ስትል አስተባብላለች።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ‘ኢራን ዋሽታለች’ ካሉ በኋላ በቀን እስከ 10 የኢራን ድሮኖችን መተው እየጣሉ እንደሆነ በማስረጃነት አቅርበዋል።
ኢራንና ሩሲያ በቅንጅት የረቀቁ የጦር መሣሪያዎችን በጋራ የማምረት ምስጢራዊ ስምምነት ሳይኖራቸው እንዳልቀረ ምዕራባዊያን የደኅንነት ምንጮች ይጠረጥራሉ።












