አሜሪካዊቷን ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ለማስለቀቅ የተደረገው የእስረኞች ልውውጥ እንዴት ተካሄደ?

ብሪትኒ ግሪነር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ ውስጥ ለወራት ታስራ የነበረችውን አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግሪነርን እንዲያስፈቱ እና ወደ አገሯ እንዲመልሱ የሕዝብ ግፊት በርትቶባቸው የነበሩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመጨረሻ ተሳክቶላቸዋል።

እንደ ጀግና የምትታየው ስፖርተኛዋ ተፈትታ ወደ አገሯ እንድትመለስ ደከመች ሰለቸኝ ሳትል ከፊት ሆና ዘመቻውን ስትመራም የነበረችው የትዳር አጋሯም ቼሪል እፎይ ብላለች።

“ደህና ናት። በአውሮፕላን ውስጥ ናት። ወደ አገሯ፣ ወደ ቤቷ እየመጣች ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ባይደን ለሕዝባቸው ንግግር አድርገዋል።

ግሪነር በሩሲያ የቆየችበትንም ሰቆቃ የተሞላበት ወቅት “የገሃነም ወራት” ሲሉ ጠርተውታል።

አጋሯ ቼሬልም ፈገግ ብላ የታየች ሲሆን ለጋዜጠኞች “በከፍተኛ ስሜት ላይ ነኝ። [ፕሬዝዳንቱ] ሳቄን መልሰውልኛል” ብላለች።

በእስረኛ ልውውጥ የተፈታችውን ብሪትኒን ለመመለስ ዘጠኝ ወራት ወስዷል።

ምንም እንኳን በርካቶች ደስታቸውን ቢገልጹም የባይደን አስተዳደር በእስር ላይ ያለውን ሌላኛውን የአሜሪካ ዜጋ ፖል ዊላን ማስፈታት አለመቻሉ ደስታውን ሙሉ አላደረገውም።

በጦርነቱ ዋዜማ በቁጥጥር ስር የዋለችው ብሪትኒ

ብሪትኒ በቁጥጥር ስር የዋለችው ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በሞስኮ አየር ማረፊያ ላይ ነበር።

ትንሽ መጠን ያለው የካናቢስ (ዕጸ ፋርስ) ዘይት በሻንጣዋ ውስጥ መገኘቱ ነበር ለእስር የዳረጋት።

ብሪትኒ ጥፋተኛ መሆኗን ብታምንም፣ ሆን ብላ ያደረገችው እንዳልሆነ ገልጻለች።

የባይደን አስተዳደር በስህተት እንደታሰረች በተደጋጋሚ ሲገልጽም ቆይቷል። እነዚህን እስረኞች እንደታገቱባት ስትገልጽ የቆየችው አሜሪካ ቅድሚያ እነዚህን ታጋቾች ለማስለቀቅም ልዩ ልዑክ እስከማቋቋም ደርሳለች።

ሆኖም የብሪትኒ የመለቀቅ ጉዳይ ውስብብ ሁኔታዎችን ያስተናገደ ነበር። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አሜሪካ ዩክሬንን እያስታጠቀች እና ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገችበት ባለበት ወቅት መሆኑ ነው።

ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት በሩሲያ በእስር ላይ የነበረውን አሜሪካዊ የባሕል ኃይል አባል ትሬቨር ሪድን በሚያዝያ ወር ማስለቀቅ ችሏል።

ሁለቱ አገራት ፖለቲካዊ ውጥረታቸውን ወደ ጎን ማድረግ እንደሚችሉ ባሳየ ድርድር በአሜሪካ በኮኬይን ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል ታስሮ በነበረውን ሩሲያዊ አብራሪ መቀያየር ቻሉ።

የትሬቨር መለቀቅ እንዲሁም የብሪትኒ እስር የዓለምን ቀልብ መሳብ ሌሎች የታሰሩባቸውም ቤተሰቦች በአንድነት እንዲቆሙና በዋይት ሐውስ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል።

ቪክቶር ቦውት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የድርድሩ ስልት ምን ይመስላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐምሌ ወር ላይ ብሪትኒ በሩሲያ ላልተወሰነ ጊዜ ልታሰር እችላለሁ የሚል ፍራቻ እንዳላት እና እንዳይረሷትም በመለመን ለፕሬዝዳንት ባይደን በእጅ የተጻፈ ደብዳቤ ላከች።

ከቀናት በኋላ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የሩሲያ አቻዎቻቸው በእስረኞች ልውውጥ እያቀረቡ ያሏቸውን ተጨባጭ ነገሮች ሊቀበሉ እንዳልቻሉ በመግለጽ ብስጭታቸውን በአደባባይ ገለጹ።

የብሊንከን በይፋ እንዲህ መናገር በዲፕሎማሲው ዓለም ያልተለመደ ነው ተብሏል። የታጋቾቹም ሆነ የእስረኞች ልውውጥ ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ነበር የሚካሄደው።

ሩሲያውያን ነውጠኛውን የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ እና በአሜሪካ 25 ዓመት እስር የተፈረደበትን ቪክቶር ቦውት እንደሚፈልጉ ግልጽ ሆነ።

ግለሰቡ ሩሲያ አደገኛ በሆኑ የአየር ጉዞዎች አደጋ ወደተሞላባቸው ስፍራዎች የሚሄድ ነጋዴ ነው የሚል ስም አትርፏል።

ቪክቶር ከሩሲያ የስለላ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንደነበረው ግልጽ ባይሆንም፣ የሩሲያ እና የአሜሪካ ተንታኞች የሚስማሙበት ጉዳይ በደኅንነት መረጃ የካበተ ስለመሆኑ ነው። ለዚህም ነው ሩሲያ አጥብቃ እንዲመለስላት ስትሟገት የቆየችው።

ይህም ለአሜሪካ ፈታኝ ጥያቄ በመሆኑ፣ ለዚህም ነበር አስተዳደሩ በድርድሩ ውስጥ ለአራት ዓመታት ያህል በእስር ላይ የሚገኘውን የኮርፖሬት ደኅንነት ሥራ አስፈጻሚ ዊላንን ለማካተት አጥብቆ የጠየቀው።

ግለሰቡ በስለላ ወንጀል ተከሶ የ16 ዓመት እስራት ተፈርዶበት በሩሲያ እስር ላይ ይገኛል። 

ድርድሮቹም ለተወሰነ ወራት ፍሬ ሊያፈሩ ያልቻሉ ሲሆን፣ ብሪትኒም የዘጠኝ ዓመት አስር ተፈረደባት። የጠየቀችውም ይግባኝ ውድቅ ተደርጎ ራቅ ወዳለ እስር ቤትም ተላከች።

ለቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ ሁኔታዎች ጨለሙባት። ድንገትም ነው የእስረኛ ልውውጡ ዜና ይፋ የሆነው።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ሁለቱም የሩሲያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተስፋ እንዳለ ቢጠቁሙም የእስረኛ ልውውጡ ጉዳይ ድንገት ነው የተነገረው።

ግሪነር እና ባውት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግሪነር እና ባውት

የእስረኞች ልውውጥ

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ስምምነቱ ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ መደረሱን ነው።

ዋነኛው የስምምነቱ ነጥብም ሁለት እስረኞችን በአንድ መለወጥ የሚል ቢሆንም፣ ሩሲያ ብሪትኒን ብቻ እንደምትለቅ አስታወቀች።

“ይህ ስምምነት የትኛው አሜሪካዊ ነው ወደ አገሩ መምጣት ያለበት የሚል ምርጫ አልነበረም” በማለት የተናገሩት አንቶኒ ብሊንከን “ምርጫው አንድ ወይም ምንም ነበር” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን በጣም አሳዛኝ ውሳኔን መቀበል ነበረባቸው፤ ይህም ብሪትኒን በቦውት መለወጥ። በዚህም ሁለቱ እስረኞችም አቡ ዳቢ አውሮፕላን ማረፊያ መንደርደሪያ ላይ እንዲተላለፉ በማድረግ ልውውጡ ተካሄደ።

ብዙም ሳይቆይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ የጋራ ሽምግልና ጥረታቸው ብሪታትኒ እንድትፈታ ረድቷል ሲሉ መግለጫ አወጡ።

ፕሬዝዳንት ባይደን ለልውውጡ የሚሆን ቦታ ስላቀረበች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ቢያመሰግኑም፣ ነገር ግን ዋይት ሐውስ መደበኛ አደራዳሪ የሚለውን ሚና ሀሳብ ዝቅ አድርጎታል።

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር ሳዑዲ አረቢያ ጉዳዩን ከሞስኮ ጋር በማንሳት ቢያመሰግኑም ድርድሩ በአሜሪካ እና በሩሲያ ብቻ የተካሄደ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ዊላን በስምምነቱ ውስጥ አለመካተቱ እንዳሳዘናቸው እና ከእስር እንዲፈታ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ከዊላን ጋር ተያይዞ ያለው ዋነኛ ችግሮች “ሐሰተኛ የስለላ ወንጀል ክስ” ነው ሲሉ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

በግልጽ እንደሚታየው ለሩሲያውያን ከሰላይ ይልቅ የስፖርት ኮከብን መለወጥ እንደ ትልቅ ጉዳይ አይተውታል ብለዋል።

ብሪትኒ ታዋቂ በመሆኗ እስሯ የሚዲያ ቀልብን የሳበ ቢሆንም ከዘጠኝ ወራት በላይ በእስር ላይ የቆዩ ሌሎች አሜሪካውያንም እንዳሉ ማስታወስ ይገባል ተብሏል።

በተጨማሪም አሜሪካ እንደ ልዕለ ኃያል አገርነቷ ሳይሆን ልታሳካ የምትችለው ጉዳይ ውስንነትና ከፍተኛ ዋጋ መክፈል እንደነበረባት አስታዋሽ ነው ተብሏል።

“ሌላኛው ወገን ሁልጊዜም ተጠቃሚ ይሆናል” ሲሉም የአሜሪካ እስረኞች ተወካይ ሮጀር ካርስተንስ በቅርቡ ተናግረዋል።

በአሁኑ ስምምነት አሜሪካ “የሞት ነጋዴ” በመባል የሚታወቀውን የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ከአንድ ግራም ያነሰ የካናቢስ ዘይት ይዛ በተገኘችው የስፖርት ኮከብ ለመለወጥ ተገደደች።

ሁለቱ አገራት ያካሄዱት የእስረኞች ልውውጥ በዚህ ዓመት ሁለተኛው ነው።

ሆኖም ይህ የእስረኞች ልውውጥ ሩሲያ እና አሜሪካ ግንኙነታቸው እንደሸከረ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ያሉ ድርድሮች እና ንግግሮችን እንደሚቀጥሉ ያሳያል።