አሜሪካ የቅርጫት ኳስ ጀግናዋን ለማስፈታት ‘የሞት ነጋዴውን’ ከእስር ፈታች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያና አሜሪካ ወራትን ባስቆጠረ ድርድር የተሳካ የእስረኛ ልውውጥ አድርገዋል።
በቅርጫት ኳስ የኦሎምፒክ ጀግና የሆነችው አሜሪካዊቷ ብሪትኒ ግራይነር ላለፉት 9 ወራት በሩሲያ እስር ቤት ቆይታ ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት ይህችን ዝነኛ ለማስፈታት ከፍተኛ የደኅንነት ሰዎችን ያሳተፈ ድርድር ሲካሄድ ቆይቶ በመጨረሻ ተሳክቶለታል።
ሩሲያ ይቺን የቅርጫት ኳስ ጀግና የምቀይረው በቪክቶር ቡት ብቻ ነው በማለቷ ይኸው ተፈጻሚ ሆኗል።
ቪክቶር ቡት ሩሲያዊ ዜጋ ሲሆን እጅግ አደገኛ የተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ነጋዴና አዘዋዋሪ ነው።
ሆሊውድ በርሱ ሕይወት ላይ ‘ሎርድ ኦፍ ዎር’ የተሰኘ ፊልም እስከመሥራት ደርሷል።
ቪክተር ቡት ላለፉት 12 ዓመታት በአሜሪካ እስር ቤት ነበር።
25 ዓመታት ጽኑ እስር ተፈርዶበት የነበረው ይህ ዓለም አቀፍ የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ነጋዴ ቡት በመጨረሻ ዝነኛዋን ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግራይነርን ለማስፈታት ሲባል ተለቋል።
ሁለቱ እስረኞችን ለማስፈታት ሁለት የግል አውሮፕላኖች ከሞስኮና ከዋሺንግተን እስረኞችን ይዘው ወደ አቡ ዳቢ የበረሩ ሲሆን በአቡዳቢ አየር ማረፊያ እስረኞቹ ሲለዋወጡ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስረኛ ልውውጡ እንዲሰምር የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን ሁነኛ ሚና ተጫውተዋል ነው የተባለው።
በተለይ ከፑቲን ጋር ጥብቅ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት ልዑል ቢን ሰልማን ከዚህ የእስረⶉች ልውውጥ በሻገር የዩክሬንና የሩሲያ የጦር ምርኮኞችን ልውውጥ ያሳለጡ ሰው እንደሆኑ ይነገራል።
ጆ ባይደን የእስረኛ ልውውጡ ተደርጎ ብሪትኒ ወደ አገሯ አሜሪካ በማቅናት ላይ ሳለች ከዋይት ሐውስ በሰጡት አጭር መግለጫ “ጀግኒትን በስልክ አወራኋት። ጥሩ ስሜት ላይ ናት። ለማገገም ጊዜ ያሻት ይሆናል’ ሲሉ ለአሜሪካዊያን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የዚች ቅርጫት ኳስ ተጫዋች የፍቅር አጋር የሆነችው ቼሬል ግራይነር “ባለቤቴ በመፈታቷ ወደር የሌለው ደስታ ተሰምቶኛል’ ብላለች።
በተመሳሳይ ‘የሞት ነጋዴው’ በሚል ቅጽል የሚታወቀው ቪክቶር ቦት ሞስኮ መድረሱ ተሰምቷል።
ቦት ሞስኮ ሲደርስ ለሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንደተናገረው፣ "ድንገት ሌሊት ላይ መጥተው ተነስ ሻንጣህን ሸክፍ አሉኝ፤ በቃ ይኸው ነው” ብሏል።
ቦት ከአውሮፕላኑ ደረጃዎች ሲወርድ እቅፍ አበባ ለእናቱና ለባለቤቱ ሲያበረክት ታይቷል።
ይህ ግለሰብ የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ ነበር በአሜሪካ ደኅንነቶች ሲታደን ቆይቶ በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ በቁጥጥር ሥር የዋለው።
ቦት ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያን ለድሃ አገራትና ለአሸባሪዎች በማስተላለፍ የሩሲያ ቀኝ እጅ ነበር ትላለች አሜሪካ።
ሩሲያ ይህ ሰው በአሜሪካ በቁጥጥር ሥር መዋሉ አበሳጭቷት ቆይቷል።
የቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ ግራይነር በበኩሏ በቁጥጥር ሥር የዋለችው በሞስኮ አየር መንገድ የካናቢስ ዘይት በሻንጣዋ ይዛ በመገኘቷ ነበር።
ይህቺን አሜሪካዊት ለማስፈታት ድርድር ሲጀመር አሜሪካ የቀድሞውን የባሕር ኃይል ባልደረባ ፖል ዊላንን
ከርሷ ጋር አብሮ እንዲፈታላት ጠይቃ ነበር።
ነገር ግን ሩሲያ ይህን ሰው ለመልቀቅ አልፈቀደችም። ፖል የታሰረው በፈረንጆች 2008 ለአሜሪካ ሲሰልል በመገኘቱ ነው።
የ32 ዓመቷ ብሪትኒ ግራይነር በቅርጫት ኳስ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊ ለፊኒክስ ሜርኩሪ የምትጫወት ዕውቅ ስፖርተኛ ናት።












