ኔታንያሁ የሁቲ ሚሳኤል የእስራኤል ዋና አየር ማረፊያ አካባቢን ከመታ በኋላ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሁቲ አማፂያን የተተኮሰ ሚሳኤል የእስራኤል ዋና አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢን ከመታ በኋላ በታጣቂ ቡድኑ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
ኔታንያሁ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በተለጠፈው የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ "ከዚህ በፊት ጥቃት ሰንዝረናል፣ ወደፊትም እናጠቃለን" ሲሉ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል።
እሁድ ጠዋት በኢራን የሚደገፈው የታጣቂ ቡድን ከየመን የተኮሰው ሚሳኤል በቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ዋና ተርሚናል አካባቢ ማረፉን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በፍንዳታው አራት ሰዎች ሲቆስሉ፣ ሌሎች ሁለቱ ደግሞ ወደ መጠለያ ጣቢያ ሲሄዱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
በጥቃቱ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሰው የለም።
እሁድ ዕለት ሁቲዎች የእስራኤል ጦር በጋዛ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ላቀደችው ምላሽ የአየር ማረፊያዎቿን ዒላማ በማድረግ በእስራኤል ላይ "አጠቃላይ የአየር ላይ እገዳ" እንደሚጥሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ "የሚመታንን ሁሉ ሰባት እጥፍ እንመታዋለን" በማለት ለጥቃቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኔታንያሁ በኋላ በሰጡት መግለጫ "የሁቲዎች ጥቃት ከኢራን የመነጨ ነው" ሲሉ አገራቸው ለሁቲ ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀው ለኢራን ደግሞ "በመረጥነው ጊዜ እና ቦታ" እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው ለጊዜው በረራ ካቋረጠ በኋላ ስራ ጀምሯል።
ይኹን እንጂ ሉፍታንዛ ፣ ኤር ፍራንስ እና ዴልታን ጨምሮ በርካታ ዋና አየር መንገዶች እሁድ ወደ አየር ማረፊያው እና ከአውሮፕላን ማረፊያው የሚያደርጉትን በረራ ሰርዘዋል።
ሚሳኤሉ ሲቃረብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአደጋ ደውሎች ተሰምተዋል።
የእስራኤል አየር ኃይል ደግሞ ሚሳኤሉን ለማክሸፍ ለምን እንዳልተቻለን እያጣራሁ ነው ብሏል።
የመከላከያ ምንጮችን በመጥቀስ የእስራኤል ሚዲያ እንደዘገበው የእስራኤልም ሆነ አሜሪካ ሰራሽ መቃወሚያዎች ሚሳዔሉን ማክሸፍ አልቻሉም ነበር።
የእስራኤል ከፍተኛ የፖሊስ አዛዥ ያየር ሄትሮኒ በሚሳኤል ጥቃቱ የተፈጠረውን ጉድጓድ ለጋዜጠኞች አሳይተዋል።
የአየር ማረፊያው ባለስልጣናት በተርሚናል ሦስት የመኪና ማቆሚያ ስፍራ አጠገብ ካለው መንገድ አጠገብ ሚሳዔሉ ማረፉን ተናግረዋል።
"ከኋላችን ያለውን ትዕይንት ማየት ትችላላችሁ፤ በአስር ሜትሮች ዲያሜትር እና እንዲሁም በአስር ሜትሮች ጥልቀት የተከፈተ ጉድጓድ ነው" ያሉት ሄትሮኒ ምንም የጎላ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።
ኔታንያሁ ስለሚሰጡት የአጸፋ ምላሽ ለመምከር ከሚኒስትሮች እና መከላከያ ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃኖች ዘግበዋል።
በየመን የሚገኘው እና በኢራን የሚደገፍ አማፂ ቡድን ሁቲ በጋዛ ከሚገኘው ሃማስ ጋር በመተባበር በእስራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃት በየጊዜው ቢሰነዝርም በእስራኤል የረቀቀ የአየር መከላከያ በኩል ማለፍ አልቻለም።
ቡድኑ በቀይ ባህር ላይ በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
አሜሪካ የቡድኑን ጥቃት ለማስቆም የቦምብ ጥቃቶች በተደጋጋሚ የፈጸመች ሲሆን ዩኬም ለአሜሪካ የቦምብ ጥቃት ድጋፍ አድርጋለች።












