ትራምፕ ለሦስተኛ ዙር ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምሁራን በአገሪቱ ህገ መንግሥት የተከለከለ ስለመሆኑ ለሚስማሙበት ለሦስተኛ ዙር የፕሬዝዳንትነት ዘመን እያሰቡ ነው መባሉን አስተባብለዋል።
"የስምንት ዓመት ፕሬዝዳንት እሆናለሁ፣ የሁለት ጊዜ ፕሬዝዳንት እሆናለሁ፣ ያ ሁሌም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስብ ነበር" ሲሉ ትራምፕ እሁድ በተላለፈው እና ከኤንቢሲ ጋዜጤኛ ከክሪስተን ዌልከር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
የ78 ዓመቱ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ለሦስተኛ ጊዜ አልፎ ተርፎ አራተኛ የስልጣን ዘመን ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት "ቀልድ አለመሆኑን" ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
በኋላ በሰጡት መግለጫ ደግሞ ያንን የተናገሩት "የውሸት የዜና ማሰራጫዎችን" ለመወረፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የእርሳቸው ኩባንያ የሆነው "ዘ ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን" የሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው በጥር 2029 ካበቃ በኋላ በስልጣን ለመቆየት ሊፈልጉ ይችላሉ ተብሎ የሚገመተውን የ"ትራምፕ 2028" ኮፍያዎችን እየሸጠ ነው።
አርብ ዕለት በፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደገው ቃለ ምልልስ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት የመቀጠሉን ሃሳቡ እንዲያጤኑ ከብዙ ሰዎች "ጥያቄዎች" እንደቀረቡላቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ የሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የመጀመሪያዎቹን 100 ቀናት ካከበሩ ከቀናት በኋላ "ብዙ ሰዎች [ያንን] እንዳደርግ ይፈልጋሉ" ብለዋል።
ትራምፕ "እኔ እስከማውቀው ድረስ ይህ የማይፈቀድ ነገር ነው። ይህ ሕገ መንግሥታዊ ይሁን አይሁን አላውቅም እንዲደረግ የማይፈቅዱት ወይም ሌላ ነገር ነው" ብለዋል ትራምፕ።
አክለውም "የ 2028ቱን ኮፍያ የሚሸጡ ብዙ ሰዎች አሉ" ብለዋል።
"ይህን ለማድረግ የምፈልገው ነገር አይደለም" ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጄዲ ቫንስን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮንን ጨምሮ የእርሳቸውን ቦታ ሊተኩ የሚችሉ ሪፐብሊካኖችን ዘርዝረዋል።
የሕገ መንግሥቱ 22ኛ ማሻሻያ "ማንም ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዚዳንትነት መመረጥ የለበትም" ይላል።
ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ከሴኔቱ እና ከተወካዮች ምክር ቤት የሁለት ሦስተኛው ይሁንታን እንዲሁም የአገሪቱን የስቴት መንግሥታት የሦስት አራተኛውን ይሁንታ ይጠይቃል።
ሆኖም አንዳንድ የትራምፕ ደጋፊዎች በፍርድ ቤት ያልተፈተሸ ክፍተት በሕገ መንግሥቱ ላይ እንዳለ ይጠቁማሉ።
በኤንቢሲ በእነዚህ ፅንሰ-ሀሳቦች ዙሪያ አነጋግሯቸው የሚያውቅ ሰው ስለመኖሩ የተጠየቁት ትራምፕ "እንደ [እኔ] ደጋፊ ብዙ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ተናግረዋል" ሲሉ መልሰዋል።
ታሪፍ 'የሽግግር ጊዜ'
በቃለ መጠይቁ ወቅት ትራምፕ በኢኮኖሚው አያያዝ ላይ የተሰነዘረውን ትችትም ውድቅ አድርገዋል።
የታሪፍ እቅዳቸው ዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚዎችን ካሽመደመደ፣ ከ2022 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ኢኮኖሚ እንዲቀንስ ካደረገ በኋላ፣ "እነሆ፣ አዎ፣ ሁሉም ነገር መልካም ነው" ብለዋል።
"ይህ የሽግግር ወቅት ነው። በአስደናቂ ሁኔታ እንደምንሰራ አስባለሁ" ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆሉን ሊቀጥል ይችላል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "ማንኛውም ነገር ሊከሰት ይችላል። ግን እኔ እንደማስበው በአገራችን ታሪክ የላቀ ኢኮኖሚ ይኖረናል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቆየት ብሎም ታሪፍ ቋሚ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለ በማከል ለጠያቂው "አንድ ሰው ይተዉታል ብሎ ካሰበ ለምን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይገነባሉ?" በማለት ተናግሯል።
ትራምፕ የንግድ ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት አሜሪካውያን በሱቆች ውስጥ የሚሸጡ ሸቀጦችን ለማጤን መዘጋጀት አለባቸው ሲሉም አስተባብለዋል።
". . . 30 አሻንጉሊቶች አያስፈልጋቸውም እያልኩ ነው። ሦስት ሊኖራቸው ይችላል" ብለዋል።
"250 እርሳሶች አያስፈልጋቸውም፣ አምስት ሊኖራቸው ይችላል።"
ትራምፕ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች የተወሰኑ መብቶችን ስለሚያረጋግጠው ስለ አምስተኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተጠይቀዋል።
ተቺዎች ፕሬዝዳንቱ 'ሕገ ወጥ' ያሏቸውን ስደተኞች ከአገር የማባረር ዕቅድ ይህን ሂደት የጣሰ መሆኑን እና አስተዳደራቸውም እስካሁን ድረስ በማንኛውም ወንጀል ያልተከሰሱ ሰዎችን ከአገር እንዳባረራቸው እና በዚህም ምክንያት ሕጋዊ መከላከያ ለማቅረብ ምንም ዕድል እንዳላገኙ ይናገራሉ።
"የዩናይትድ ስቴትስን ሕገ መንግሥት እንደ ፕሬዚደንት ማክበር አያስፈልግም?" ስትል የጠየቀችው ዌልከርን "ሕገ መንግሥቱን ማቆየት፣ መጠበቅ እና መከላከል" የሚፈልገውን የፕሬዚዳንቱን ቃለ መሃላ አፍርሰው ሊሆን እንደሚችል ጠቁማለች።
ትራምፕ "አላውቅም፤ መልስ መስጠት አለብኝ እንደገና ለእኔ የሚሰሩ ድንቅ ጠበቆች አሉኝ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተናገረውን በግልጽ ይከተላሉ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ባለፈው ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋይት ሐውስ በአጋጣሚ ወደ ኤል ሳልቫዶር እስር ቤት የተባረረውን ስደተኛ ለመመለስ "ለማመቻቸት" መስራት እንዳለበት ወስኗል።
የትራምፕ አስተዳደር የማዕከላዊ አሜሪካዊቷን አገር ስደተኛው ወደ አሜሪካ እንድትመልስ የማስገደድ ስልጣን እንደሌላቸው ተከራክረዋል።
ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅልል ወታደራዊ ኃይል የመጠቀምን ሃሳብ "መተው" እንደማይችሉ ገልጸው፣ ነገር ግን የዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ጎረቤት 51ኛ የአሜሪካ ግዛት እንድትሆን ለማስገደድ በካናዳ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር እንዳላሰቡ ጠቁመዋል።
ትራምፕ የካናዳ መራጮች የሊበራል ፓርቲ መሪ ማርክ ካርኒን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ከመረጡ ከቀናት በኋላ "ከካናዳ ጋር አላየውም" ሲሉ ወግ አጥባቂ ፓርቲን በሚያስገርም ሁኔታ ውድቅ አድርገዋል።
ትራምፕ ንግግራቸውን በመቀጠል "እኛ የምንጠብቃቸው መስሎአቸው ነው" ብለዋል።
ካርኒ ማክሰኞ በዋይት ሐውስ ትራምፕን ሊጎበኙ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልጣን ዘመናቸው የኢሚግሬሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ስላደረጉት ውሳኔ እና ድንበሩ አሁን "አስተማማኝ" ስለመሆኑ ተጠይቀዋል።
"እስከ ዛሬ ከነበረን እጅግ አስተማማኝ ድንበር አለን" የሚል ምላሽ የሰጡት ትራምፕ፤ የኢሚግሬሽን አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሕገ-ወጥ ስድተኞች ድንበር ጥሶ መግባት ባለፉት አሥርተ ዓመታት ዝቅተኛው ደረጃ ላይ መውደቃቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን እንደቀጠለ ተከታይ ጥይቄ ቀርቦላቸዋል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍርድ ቤት ስርዓት እንጂ በድንበር ላይ አይደለም ሲሉ መልሰዋል።
"በአሁኑ ጊዜ ዋናው አንገብጋቢ ጉዳይ እኛ ከአገር ልናስወጣቸው የምንፈልጋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉን። ሁሉም ሰው ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ የሚፈልጉ ዳኞች ደግሞ አሉ" ብለዋል ።
"በኢሚግሬሽን ላይ አጠቃላይ አስቸኳይ ሁኔታ ነው" ሲሉ ትራምፕ ለኤንቢሲ የገለፁ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ትዕዛዙን የማንሳት እቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።












