ከህወሓት በወጡ አመራሮች የተቋቋመ ሁለተኛ ፓርቲ በመቀለ መሥራች ጉባኤ እያካሄደ ነው

የውድብ ወለዶ ትግራይ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግዑሽ ግደይ

የፎቶው ባለመብት, sm

የምስሉ መግለጫ, የፓርቲው ምሥረታ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግዑሽ ግደይ፤ በአቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅት የክልሉ ማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካከል በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት ከፓርቲው በወጡ የቀድሞ አመራሮች የተቋቋመ፤ "ውድብ ወለዶ ትግራይ" (የትግራይ ትውልድ ፓርቲ) የተባለ አዲስ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ በመቀለ ከተማ መሥራች ጉባኤ ማድረግ ጀመረ።

የህወሓት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ አመራሮች በነበሩ ግለሰቦች አስተባባሪነት ምሥረታውን እያካሄደ ያለው ፓርቲው፤ በቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።

ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ዓ.ም. በመቀለው ፕላኔት ሆቴል መሥራች ጉባኤ እያደረገው ያለው ፓርቲ አስተባባሪዎች መካከል ሦስቱ በአቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች የነበሩ ናቸው።

አቶ ግዑሽ ግደይ የማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ አቶ ተክላይ ፍቃዱ ደግሞ ሰሜን ምዕራብ ዞንን እንዲመሩ በቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ተሾመው ነበር። ሌላኛው አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ትኩዕም በተመሳሳይ የትግራይ ክልል ምሥራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ።

የህወሓት አባል እና አመራር የነበሩት ሦስቱ አስተባባሪዎች ከፓርቲው የወጡት በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ ነው።

በወቅቱ የነበረውን መካረር ተከትሎም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸውን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ካመሩት አመራሮች መካከል ናቸው።

በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሚመራው ቡድን እና በቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ክንፍ መካከል የተፈጠረው መካረር የትግራይ አመራሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲጓዙ አድርጓል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው በተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ክንፍ "ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ" (ስምረት) የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ሂደት መጀመሩ አይዘነጋም።

ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ፍቃድ ያገኘው ስምረት፤ በመቀለ ከተማ በከፈተው ቢሮ ላይ ዘረፋ እንደተፈጸመበት ገልጾ ነበር።

በትግራይ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ ሌሎች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች "ትግራይ ፒስ ፎርስ" (የትግራይ ሰላም ኃይል) የተባለ ታጣቂ ቡድን መሥርተው እየተንቀሳቀሱ ነው።

አጎራባች በሆነው አፋር ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ይህ ኃይል፤ በተለያዩ ጊዜያት ከትግራይ ኃይሎች ጋር መጠነኛ ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበረም ተነግሯል።

የውድብ ወለዶ ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, sm

መሥራች ጉባኤውን እያደረገ ያለው "ውድብ ወለዶ ትግራይ"፤ ከህወሓት አመራርነት በወጡ ግለሰቦች አስተባባሪነት እየተቋቋመ ያለ ሁለተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኗል።

የውድብ ወለዶ ትግራይ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግዑሽ፤ የፖለቲካ ፓርቲውን ለመመሥረት "የተገደዱት ከትግራይ ፖለቲካ ስለተገፉ" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ትግራይ ውስጥ የለውጥ ፍላጎት አለ፤ የወጣቱ ትውልድን የለውጥ ፍላጎት እውን ለማድረግ ትውልድ የሚባል አዲስ ፓርቲ ይዘን መጥተናል" ብለዋል።

የውድብ ወለዶ ትግራይ፤ የአባላት ፊርማ ማሰባሰብ እና መሥራች ጉባኤ ማድረግ የሚያስችለውን ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘው ሐምሌ 2017 ዓ.ም. ነው።

ከዚህ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ላይ የተቀመጠውን የአራት ሺህ መሥራች አባላት ፊርማ ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

አቶ ግዑሽ፤ በዛሬው መሥራች ጉባኤ የፖለቲካ ፓርቲው የአባላት መተደዳደሪያ ደንብ እና "ማኒፌስቶ" ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል። ሊቀመንበርን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የፓርቲ አመራሮች ምርጫ እንደሚካሄድም አክለዋል።

ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተሉ ጥያቄ የቀረበላቸው አስተባባሪው፤ ፓርቲው "የትግራይን ክብር እና ሥርዓት ባስጠበቀ መልኩ የሚቀበለው የሀገር ውስጥ እሳቤ" እንደሚኖር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ውድብ ወለዶ ትግራይ በዚህ ዓመት እንደሚደረግ በሚጠበቅው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳለው ገልጸዋል።

በ2018 ዓ.ም. ምርጫ "ለማሸነፍ እንደሚተጉ" ያስረዱት አቶ ግዑሽ፤ "ካላሸነፍን ደግሞ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ሆነን በክልሉ እንቀጥላለን" ብለዋል።

የፓርቲው መሥራች ጉባኤ ተሳታፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Laza Tigrigna

የምስሉ መግለጫ, የፓርቲው መሥራች ጉባኤ ተሳታፊዎች