በኢንግሊሽ ቻናል ጀልባ ተገልብጦ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ሞቱ

የፈረንሳይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በኢንግሊሽ ቻናል ላይ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን የሆኑ ስደተኞች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት ስደተኞችን ጭና የነበረችው ጀልባ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን በሚያዋስነው የውሃ አካል ላይ ከተገለበጠች በኋላ ቢያንስ 12 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የፈረንሳይ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው በጀልባ መገልበጥ አደጋው ሕይወታቸውን ያጡት አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን ናቸው ብሏል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚንስትር ጀራልድ ዳርማኒን ሕይወታቸው ካለፉ 12 ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

የፈንሳይ የባሕር ድንበር ጠባቂ 50 ሰዎቸን መታደጉን ገልጾ አብዛኛዎቹ ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት መላካቸውን ገልጿል።

ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች በኢንግሊሽ ቻናል በኩል አስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም እንግሊዝ ይደርሳሉ።

ይሁን እንጂ በዚህ የውሃ አካል ላይ በሚያጋጥም አደጋ የበርካቶች ሕይወት ሲያልፍ ቆይቷል።

ባለፉት 9 ወራት ወደ 20ሺህ ሰዎች የውሃ ክፍሉን አቋርጠው እንግሊዝ የገቡ ሲሆን በዛሬው አደጋ የደረሰውን ጉዳት ጨምሮ 30 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተጎጂዎችን ለመርዳት እና የጠፉትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዩኬ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ያቬት ኩፐር በበኩላቸው ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ መናኛ በሆኑ ጀልባዎች በርካታ ስደተኞችን እየጫኑ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ነው ብለዋል።

የዩኬ የአገር ውስጥ ሚንስትሯ አደገኛ የሆኑ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ሰንሰለት በመበጠስ የድንበር ደኅንነትን ማረጋጋጥ ቁልፍ ነው ብለዋል።

በፈረንሳይዋ የድንበር ከተማ ካሌ ስደተኞችን የሚረዳው ‘ኬር4ካሌ’ የተባለ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ስቲቭ ስሚዝ፤ መሰል አሳዛኝ ክስተቶች የሚገጥሙበት መጠን እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚውን በዩኬ እና ፈረንሳይ ያሉ “ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች፤ መግታት የሚቻሉ እነዚህ አሳዛኝ አደጋዎችን የምናስቆም የስንት ሰው ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው? ተብለው መጠየቅ አለባቸው” ብለዋል።