አየር መንገዱ የኤርትራ በረራውን ያቋረጠው በአገሪቱ ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Jonathan Druion

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ ከተገደደባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በአገሪቱ ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ መሆኑ ተገለጸ።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ማክሰኞ ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አየር መንገዱ በኤርትራ ባንክ ያለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዳይችል እንደታገደ ገልጸዋል።

ሐምሌ ወር የኤርትራው ባንክ አየር መንገዱ በኤርትራ ያለውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይወስድ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ስለመታገዱ ከባንኩ መስማታቸውን የተናገሩት አቶ መስፍን፤ “ላለፈው 1 ወር ገንዘብ ማውጣት አልቻልንም። ባንኩ እንዳታወጡ ታግዳችኋል አለን። ባንኩ የሚለው የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ከአገር እንዳያወጣ ከልክሏል ነው” ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አየር መንገዱ ገንዘቡን ከኤርትራ እንዳያወጣ ለምን እንደታገደ ለኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ያቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን ተናግረዋል።

“ኦገስት 31 ከሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ለማስገባት ስንሄድ ባንኩ ሂሳባችሁ ሙሉ በሙሉ ታግዷል። ገቢ እንጂ ወጪ ማድረግ አትችሉም አሉን” ብለዋል አቶ መስፍን።

አየር መንገዱ በኤርትራ ያለውን ገንዘብ ከአገር ማውጣት ብቻ ሳይሆን በኤርትራ እንዳይጠቀም መከልከሉ የአየር መንገዱ ኦፕሬሽን ሙሉ በሙሉ አዳጋች እንዲሆን ማድረጉን አብራርተዋል።

“አየር መንገዱ በቅን ልቦና የኤርትራ መንገደኞችን ለማገልገል ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ በጎ ምላሽ ባለማግኘታችን በረራ ለማቋረጥ ተገደናል፤ በዚህም በጣም አዝነናል።. . . መንገደኞቻችን የምናከብራቸው ደንበኞቻችን ናቸው። በዚህ ምክንያት ይስተጓጎላሉ” ካሉ በኋላ ቀድመው ቲኬት ለገዙ ደንበኞች ገንዘባቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚመለስ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ነሐሴ 28፤ 2016 ጀምሮ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያቋርጥ አስታውቆ ነበር።

አየር መንገዱ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ በለቀቀው መግለጫ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ የተገደደው “በኤርትራ ያለው ምቹ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ ከቁጥጥሩ ውጭ” ስለሆነበት እንደሆነ አሳውቋል።

አየር መንገዱ አስቀድመው ቲኬት የቆረጡ መንገደኞች ያለምንም ወጭ በሌሎች አየር መንገዶች የሚጓዙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ገልጿል። ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የሚሹ ሰዎችም ያወጡት ወጪ ሙሉ በሙሉ እንደሚመለስላቸው ቃል ገብቷል።

ባለፈው ሐምሌ የኤርትራ መንግሥት ከመስከረም 20 ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርጋቸው በረራዎች እንደሚቋረጡ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ይሁንና ይህ በረራ ይቋረጣል ከተባለበት ቀን አስቀድሞ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስመራ በረራዎችን እንደሚያቋርጥ ያስታወቀው።

ባለፈው ሐምሌ የኤርትራ መንግሥት የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ አየር መንገዱ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማብራሪያ እንደሚጠይቅ ማሳወቁ አይዘነጋም።

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅመው ከኤርትራ እና ወደ ኤርትራ ለሚያቀኑ መንገደኞች ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ ለበረራው መቋረጥ ምክንያቶችን አስፍሯል።

በኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በታተመው በመንግሥታዊው “ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ባወጣው ማስታወቂያ አየር መንገዱ እንዲታገድ የተወሰነው "ያልተገባ የንግድ ተግባራት" በመከተሉ ነው ሲል ኩባንያውን መውቀሱ ይታወሳል።

የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ከደረሰባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በአየር መንገዱ ተጓዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት" ይፈጸማል የሚለው ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም ተደጋጋሚ የበረራዎች እና የሻንጣዎች መዘግየት እንደሚያጋጥም ጠቅሶ፤ አየር መንገዱ ለተጓዦች ካሳ ሳይሰጥ ቆይቷል ሲል ይወቅሳል።

የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር መንገዱን ለማገድ ከወሰነበት ምክንያቶች ሌላኛው የበረራ ቲኬቶች ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ ነው የሚል ነበር።

“ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እንዲቀረፉ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጡ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች ውጤት ማስገኘት ባለመቻላቸው ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚደረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች እንዲታገዱ ተደርገዋል” ሲል አቪየሽኑ እግድ መጣሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ አስመራ በረራዎችን ያደርግ ነበር።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ የሳዑዲ አረቢያ፣ የቱርክ እና የግብፅ አየር መንገዶች ወደ አሥመራ መደበኛ በረራዎች አሏቸው።

በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጣልያን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የጣልያን አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ እንዲጀምር ስምምነት መደረሱ ተዘግቧል።

የኢትዮ-ኤርትራ ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአውሮፕላን ጉዞ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ጦርነትም ሆነ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቆይታው የነበሩት አሥመራ እና አዲስ አበባ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ተከትሎ ነበር በረራ የተጀመረው።

በወቅቱ የሁለቱ አገራት መሪዎች “የአሥመራ ዲክላሬሽን” የተሰኘ ስምምነት ተፈራርመው ከአየር በረራ በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩት የየብስ ትራንስፖርት፣ የንግድ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ዕድል ፈጥሮ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱን አገራት የሚያዋስኑ የድንበር በሮች በሙሉ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ታድሶ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሰሜን ኢትዮጵያ የእርሰ በርስ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ መልሶ መሻከሩ ይገለጻል።