ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር መሳሪያ መሸጧን አሜሪካ ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ ዩክሬንን ለማጥቃት የሚውሉ ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ዋግነር ለተባለው የሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ታቀርብ ነበር ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሰች።
አቅርቦቱ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን የሚጥስ ሲሆን በዋግነር ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል አሜሪካ አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ እና ዋግነር ግን ሪፖርቶቹን አስተባብለዋል።
በዩክሬን የሚገኙ የቅጥረኛ ቡድኑ ተዋጊዎች ከ1,000 ወደ 20,000 ማደጋቸውን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስታወቋል።
ቡድኑ በሶሪያ እና በአፍሪካ ሀገራት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን ተደጋጋሚ ከጦር ወንጀሎች እና ሰብአዊ መብት ረገጣ ጋር ስሙ ተነስቷል።
"ዋግነር በዩክሬን ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚደግፉ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎችን በዓለም ዙሪያ እያፈላለገ ነው” ሲሉ የኋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"ሰሜን ኮሪያ ለዋግነር የመጀመሪያውን የጦር መሳሪያ ማድረሷን እናረጋግጣለን። ለእነዚህ መሳሪያዎች ከፍያ ተፈጽሟል" ብለዋል።
ቅጥረኛ ቡድኑ አነስተኛ ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን ከሰሜን ኮሪያ መረከቡን ኋይት ሃውስ ገልጿል።
ኪርቢ አክለውም ዋግነር በየወሩ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ በዩክሬን እያወጣ ነው።
ቡድኑ ከሩሲያ ጦር ጋር ተፎካካሪ ሆኗል ብለዋል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ ዩኬ በዋሽንግተን ግምገማ እንደምትስማማ አስታውቀዋል።
"ፕሬዝዳንት ፑቲን ለእርዳታ ወደ ሰሜን ኮሪያ ፊታቸውን ማዞራቸው የሩስያን ተስፋ መቁረጥ እና ከዓለም መገለሏን የሚያሳይ ነው" ሲሉ ክሌቨርሊ በመግለጫቸው ገልጸዋል።
የዋግነር መሪ የቭጌንይ ፕሪጎዥን "ሀሜት እና መላምት" ሲሉ ጉዳዩን አስተባብለዋል። የሰሜን ኮሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘገባዎቹን "መሠረተ ቢስ" ሲል ጠርቷቸዋል።

"የአቋም ለውጥ የለም። በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል የጦር መሳሪያ ግብይት በፍፁም ተካሂዶ አያውቅም" ሲሉ የሰሜን ኮሪያ ቃል አቀባይ ተናግረዋል.
የዋግነር ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጦር እንቅስቃሴ የገባው እአአ በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን ወደ ግዛቷ በጠቀለለችበት ወቅት እንደነበረ ይታመናል።
የዋግነር ባለቤቱ የሆኑት ፕሪጎዥን “የፑቲን ሼፍ” በመባል የሚታወቁ ከበርቴ ናቸው። 'የፑቲን ሼፍ' የሚለውን ስያሜ ያገኙት የክሬምሊን ምግብ አዘጋጅ እና የሬስቶራንት ባለቤት ስለነበሩ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ወረራ በርካታ ሽንፈቶች ማጋጠሙን ተከትሎ የዋግነር ተጽዕኖ በእጅጉ ተጠናክሯል።
እአአ መጋቢት 2022 ላይ ዋግነር ከ1,000 በላይ የሆነ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደላከ ይታሰብ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ይህ ቁጥር አሁን ከ 20,000 በላይ አድጓል ይላሉ። ይህም ከአጠቃላዩ የሩሲያ ጦር 10 በመቶ ገደማ ደርሷል።
የዋግነር ቁጥር ማደግ በሩሲያ እስር ቤቶች ውስጥ ወንጀለኞችን ዒላማ አድርጎ ከመቅጠሩ ጋር የተያያዘ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ግምቶች እንደሚያመለክቱት ምልመላ በሚካሄድበት ወቅት እስከ ህዳር 2022 ድረስ ባሉት ሁለት ወራት በሩሲያ እስር ቤቶች ውስጥ የተፈረደባቸው ሰዎች ቁጥር ከ 23,000 በላይ ቀንሷል።
ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም ብዙ ወንጀለኞች ዋግነርን ተቀላቅለዋል ተብሎ ይታመናል።
ለስድስት ወራት በጦር ግንባር ከቆዩ በኋላ ክፍያ እንደሚከፈላቸው እና ቅጣታቸው እንሚነሳላቸው ተነግሯቸዋል።












