ሰርጂዮ ራሞስ፡ ጫማ መስቀል አሻፈረኝ ያለው ቱጃሩ እግር ኳሰኛ፤ መጨረሻው የት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ዋንጫ፣ የአውሮፓ ዋንጫ፣ አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፣ አምስት ጊዜ ላ ሊጋ፣ አንድ የሊግ ዋንጫ ያነሳው የ36 ዓመቱ ስፔናዊ ተከላካይ።
ብዙዎች ይህን ድል ቢያገኙ ጫማቸውን ሰቅለው ስፋቱ ፈረስ በሚያስጋልብ ቤት ተንደላቀው ጡረታቸውን ያጣጥሙ ነበር።
ሚሊየነሩ ሰርጂዮ ራሞስ ግን ጫማ መስቀል የሚታሰብ አይደለም የሚል ይመስላል።
ባፈለው ታኅሣሥ ግሎብ ሶከር አዋርድስ የተሰኘው ተቋም ‘የምንም ጊዜም ምርጡ ተከላካይ’ የሚል ክብር ሲሰጠው “ገና ብዙ የማሳካው ሕልም” አለኝ ብሎ ነበር።
ራሞስ፤ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ራሱን አግልሏል፤ ከፒኤስጂ ጋር ያለውም ውል እየተገባደደ ነው።
መራራ ስንብት ከብሔራዊ ቡድን
ብዙዎች የቀድሞው የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ተከላካዩን ከቡድኑ ያሰነብቱታል ሲሉ ጠብቀው ነበር።
ነገር ግን ራሞስ በብሔራዊ ቡድኑ ቦታ እንደሌለው የነገሩት አዲሱ አሠልጣኝ ድ ላ ፉዌንቴ ናቸው።
አሠልጣኙ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ቀትር ላይ ደውለውለት ከብሔራዊ ቡድኑ መሰናበቱን ነግረውታል። አዲሱ አሠልጣኝ ይህን ያደረጉት ሥራዎችን ከታች ለመጀመር ነው ብለው ብዙዎች ያምናሉ።
ነገር ግን ራሞስ እንዲሁ በዝምታ የአሠልጣኙን ውሳኔ ይቀበላል ብሎ መገመት የዋህነት ነው።
ከአሠልጣኙ ጋር በቀጭኑ ሽቦ ካወራ ከአምስት ሰዓታት በኋላ፣ ራሞስ ወደ ማኅበራዊ ሚድያ ገፁ አመራ። “ብዙ አገልግለዋለሁ ካልኩት ቤቴ፤ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን መሰናበቴን ስገልጽ በሐዘን ነው” ሲል ፃፈ።
በስፔን ስፖርት መገናኛ ብዙኃን ሁሌም ራሞስን በመደገፍ የሚታወቁ ሰዎች አሉ። በእነዚህ ሰዎች የታገዘው ራሞስ “ከቡድኑ ልሰናበት የሚገባው በራሴ ውሳኔ አሊያም አቋሜ ቢወርድ ነበር፤ ነገር ግን ዕድሜ አሊያም የማላውቀው ምክንያት ተጠቅሞ እኔ ማሰናበት ተገቢ አይደለም” ሲል አስተያየቱን ሰጠ።
ይህን የሰማው የስፔን እግር ኳስ ማኅበር “ድሮም ክብር አይወድለትም” ማለቱን የውስጥ ምንጮች ዘገቡ።
ሲቪያ ተወልዶ ያደገው ራሞስ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን 180 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል። ነገር ግን በፈረንጆቹ 2021 በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ እንደተገለለ በዚያው ቀርቷል።
ራሞስ ከብሔራዊ ቡድን የተሰናበተበት መንገድ መራር መሆኑ በ16 ዓመታት ያገኘውን ድል እንዳያጠለሽበት ስጋት አለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሆቴል፣ ጉዳት፣ እንግሊዝኛ. . .
ራሞስ ከሪያል ማድሪዱ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጋር የነበረውን እሰጥ አገባ ተከትሎ ባለፈው ዓመት የፈረንሳዩን ፒኤስጂ መቀላቀሉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ዓመታት የራሞስ እና የክሪስቲያኖ ሮናልዶን ተፅዕኖ ለራሳቸው ጥቅም ሲያውሉት ነበር ተብለው ይተቻሉ።
ነገር ግን ራሞስ ያለው ተፅዕኖ እየገዘፈ ሲመጣ፣ ፕሬዝዳንቱ ተከላካዩን ማስወገድ እንዳለባቸው ተረዱ።
አመፀኛው ተከላካይ ለብዙ ክብር ካበቃው ቤት ከተሰናበተ በኋላ ወደ ፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ቢመጣም በጉዳት ምክንያት በመጀመሪያው ዓመት እንደልቡ አልተጫወተም።
በወቅቱ ‘እያገገምኩ ነው’ ሲል መልዕክት ቢያስተላልፍም እውነታው ግን ለ16 ዓመታት ደም እና ላቡን ከሰጠለት ክለብ እንደማንም መሰናበቱ ጎድቶት ነበር።
የመጀመሪያዎቹን የፓሪስ ቀናት ለ ሮያል ሞንሲዩ በተሰኘው ቅንጡ ሆቴል አሳለፈ። በወሩ ሊዮኔል ሜሲ ፒኤስጂን ሲቀላቀል የሰነበተው እዚሁ ሆቴል ነበር።
ሆቴሉ የእግር ኳስ ከዋክብት ለፒኤስጂ ሲፈርሙ ቋሚ መኖሪያ እስኪያገኙ ድረስ የሚያርፉበት ቢሆንም፣ አድናቂዎች በሩን ዘግተው መጠበቃቸው ለተጫዋቾች ምቹ አልነበረም።
የቀድሞው የማድሪድ ግብ ጠባቂ እና የሰርጂዮ ራሞስ የቅርብ ወዳጅ የሆነው ኬይለር ናቫስ፤ ራሞስን ተቀብሎ በገዛ ቤቱ ያኖረው ጀመር።
የራሞስ ሚስት እና አራቱ ልጆቻቸውን ይዛ ባሏ በፓሪስ ቋሚ መኖሪያ እስኪያገኝ ድረስ ወደ ማድሪድ ተመለሰች።
ራሞስ፤ ማድሪድ እንደለመደው ያለ ከግርግር የፀዳ ቅንጡ መኖሪያ ቤት ፓሪስ ውስጥ ሊያገኝ ባለመቻሉ መጨረሻው በምዕራቡ የከተማዋ ክፍል ሆነ።
ቱጃሩ እግር ኳሰኛ በአዲሱ ቤቱ ለማገገም የሚያስፈልገውን ሁሉን ያሟላ ጂም አደራጀ። ከእግር ኳስ ውጭ የሚዝናናበት ሙያው ሥዕል በመሆኑ የመሳያ ስቱዲዮም አመቻቸ።
ራሞስ በየቀኑ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ይወስዳል፤ አብዛኞዎቹ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ስፓኒሽ ስለሚናገሩ ፈረንሳይኛ መማር አላሻውም።
ስፔናዊው ተከላካይ በአንድ ወቅት ደመኛው ከነበረው አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲ ጋር አብሮ ይጫወታል። ምንም እንኳ በመሃከላቸው ፕሮፌሽናል ግንኙነት ቢኖርም ጓደኛሞች ናቸው ማለት ከባድ ነው።
ልጆቻቸው ግን ጓደኛሞች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደገና ከሮናልዶ ጋር?
ጋዜጠኛ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ የሆነችው የራሞስ ሚስት ፒላር ሩቢዮ ስፔን ውስጥ ከራሞስ ያላነሰ ዝና አላት ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ራሞስ ከእግር ኳስ ባለፈ የተለያዩ ተሰጥዖዎች ባለቤት እንደሆነ ይነገርለታል።
አንድ የስፔን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰርጂዮ ራሞስ የጥበብ ሥራዎቹን በአንድ ድብቅ የኢንስታግራም ገፅ ላይ ይለጥፋል ይላል።
ራሞስ ከፒኤስጂ ጋር ያለው ፊርማ በሚመጣው ሰኔ ይጠናቀቃል።
ብዙዎች ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ተከትሎ ወደ ሳዑዲ አራቢያው ክለብ አል ናስር ያቀናል ይላሉ። ነገር ግን አሁንም ትላልቅ በሚባሉ ሊጎች ውስጥ መጫወት እንደሚፈልግ ይነገራል።
ምናልባት ወደ አሜሪካው ኤምኤልኤስ ሊያቀናም እንደሚችል ፍንጮች አሉ። ካልሆነም ወዳደገበት ክለብ ሲቪያ ሊመለስ ይችላል የሚሉ ወሬዎችም ተሰምተዋል።
የራሞስ የተጣራ ሃብት ከ80 እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።
ራሞስ በፒኤስጂ ቤት በዓመት 15 ሚሊዮን ዩሮ ነው የሚከፈለው። ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካላቀና በስተቀር ይህን ያክል ገንዘብ የሚከፍለው ያገኛል ብሎ መገመት ከባድ ነው።












