ሐኪሞች የንግሥት ኤልዛቤት የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም እና የኮመን ዌልዝ አገራት ንግሥት የሆኑት ንግሥት ኤልዛቤት ዳግማዊት ሐኪሞች የንግሥቲቱ ጤና አሳሳቢ ነው አሉ።
የንግሥቲቱ ይፋዊ መኖሪያ ቤት ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት እንዳስታወቀው ንግሥት ኤልዛቤት ሁለተኛ በጤና ክትትል ስር እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።
የንግሥት ኤልዛቤት ልጅ ልዑል ቻርልስ ንግሥቲቱ ወደሚገኙበት ባልሞራል ቤተ-መንግሥት አቅንተዋል።
የ96 ዓመቷ የዩኬ እና የኮመን ዌልዝ አገራት ንግሥት ኤልዛቤት ዳግማዊት በ70 ዓመት የንግሥና ዘመናቸው በርካታ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን ተመልክተዋል።
ከቀናት በፊት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሊዝ ትረስ በንግሥት ኤልዛቤት የንግሥና ዘመን 15ኛዋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
የንግሥቲቱን የጤና መቃወስ ዜና መሰማቱን ተከትሎ አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ "መላው አገር" በዜናው "እጅጉን ተረብሿል" ብለዋል።
የንግሥቲቱ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ በርካርታ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ወደ ስኮትላንድ እያቀኑ ነው።
ለባልሞር ቤተ-መንግሥት ቅርበት ባለው አበርዲን አየር መንገድ ከወትሮ በተለየ እንቅስቃሴ እየታየ ነው።
ንግሥቲቱ ወዳሉበት ስኮትላንድ ከተጓዙት መካከል ልዑል ቻርልስ ይገኙበታል።
የሰሴክስ መስፍን እና ሶፋኒት ሄሪ እና ሜጋን ወደ ስኮትላንድ እንደሚሄዱ የጥንዶቹ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የዮርክ መስፍን ልዑል አንድሩ ወደ ስኮትላንድ እያቀኑ ሲሆን፣ ልዕልት አን ቀደም ሲል ስኮትላንድ ደርሰዋል።
አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ የእኔ እና የዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ መልካም ምኞት ከንግሥት ኤልዛቤት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው ብለዋል።
የንግሥት ኤልዛቤት የጤና ሁኔታ ማሽቆልቆሉ መገለጹን ተከትሎ በርካታ በአገሪቱ ያሉ ተዋቂ ግለሰቦች እና ፖለቲከኞች መልካም ምኞታቸውን እየገለጹ ነው።
የካንትበሪ ሊቀጳጳስ ጀስቲን ዌብሊ፤ እኔ፣ የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያ እና መላዋ አገሪቱ ንግሥቲቷን በጸሎታቸው እያሰቡ ነው ብለዋል።
የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚንስትር ኒኮላ ስተርጅን የንግሥቲቱ ጤና እጅጉን አሳስቦኛል ብለዋል። ተቀዳሚ ሚኒስትሯ ለንግሥት ኤልዛቤት እና ለመላው ንጉሣውያን ቤተሰቦች መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ብለዋል።












