አሜሪካ ለዩክሬን እና ለሌሎች አጋሮቿ የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አጸደቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ ለዩክሬን እና አጋሮቿ የ2.7 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ያጸደቀች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 675 ሚሊዮን ዶላሩ ለኪዬቭ ጦር መሳሪያ አቅርቦት የሚውል ነው ተብሏል።
ይህ የተገለጸው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ከአቻዎቻቸው ጋር ጀርመን በሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ሠፈር ውስጥ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
አሜሪካ ለዩክሬን በድጋፍ መልክ ከምትሰጣቸው መካከል ሆዊትዘር የተሰኘ ከባድ መድፍ ፣ ተተኳሾች፣ የጦር ተሸከርካሪዎች፣ ፀረ-ታንክ ሥርዓቶች እና ብረት ለበስ አምቡላንሶች ይገኙበታል።
አሜሪካ ለዩክሬን 13 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብታለች።
ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ 03/2014 ዓ.ም. የባይደን አስተዳደር የዩክሬን እና በቀጠናው የሚገኙ 18 አገራት ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ የ2 ቢሊዮን ዶላር የረዥም ጊዜ ድጋፍ በኢንቨስትመንት መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
እነዚህ አገራት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ደርጅት (ኔቶ) አባል የሆኑ እና ያልሆኑ የሚገኙበት ሲሆን፤ ወደፊት በሩሲያ ወረራ ሊቃጣባቸው የሚችሉ አገራት ናቸው ብሏል የባይደን አስተዳደር።

ይህ የአሜሪካ ድጋፍ የተሰማው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዩክሬን መዲና ኪዬቭ መግባታቸው በተገለጸበት ወቅት ነው።
ዩክሬን የሩሲያን ወረራ መከላከል እንዲቻላት ምዕራባውያን ያልተቋረጠ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያቀረቡላት ይገኛል።
እስካሁን ከ30 ያላነሱ አገራት የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን አቅርበዋል። አሜሪካ ደግሞ ለዩክሬን ሠራዊት የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ከየትኛውም አገር በላይ ከፍ ያለ ወጪ እያደረገች ነው።
ከአሜሪካ በመቀጠል ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፖላንድ በቢሊዮን የሚያስወጡ በርካታ የጦር መሳሪያ ድጋፍን አቅርበዋል።
የሩሲያ ወረራን እየተለላከለ የሚገኘው የዩክሬን ጦር ትናንት በሞስኮ ኃይል ላይ ድል መቀዳጀቱን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በሰሜን ምሥራቅ ኻርኪቭ የሚገኙ የሰፈራ ቦታዎችን ጦራቸው መልሶ መቆጣጠሩን ገልጸዋል። የሩሲያ ፕሬዝዳንት ብላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ጦራቸው የተነጠቀው ቦታ እንደሌላ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋለስ በተመሳሳይ ዩክሬን ወታደራዊ ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው ብለዋል።
ምዕራባውያን ለዩክሬን እያቀረቡ የሚገኙት ረዥም ርቀት ተተኳሾች እና ሮኬቶች የሩሲያ የአቅርቦት መስመርን እና የማዘዣ ጣቢያዎችን ዒላማ ማድረጋቸው ለሞስኮ ጦር ፈተና ሆኗል።












