በፓኪስታን ‘ቅዱስ ቁርዓንን አራክሷል’ የተባለ ቱሪስት በደቦ ጥቃት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፓኪስታን ቅዱስ ቁርዓንን አራክሷል በሚል የተወነጀለ ጎብኝ ከፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ በደቦ ፍርድ ተገደለ።
ድርጊቱ የተፈፀመው በስዋት ወረዳ በምትገኘው ማድያን ከተማ ሲሆን ፖሊስ ጎብኝውን ከተሰባሰበው ቡድን ለመከላከል ሞክሮ ነበር።
ሐሙስ ዕለት ነዋሪዎች የተሰባሰቡት ግለሰቡ ቅዱስ ቁርአንን አራክሷል ከተባለ በኋላ ነበር።
ሃይማኖትን ማራከስ በፓኪስታን በሞት የሚያስቀጣ ሲሆን በዚህ ድርጊት የተወነጀሉ ሰዎችን ያለፍርድ በደቦ ጥቃት መግደል የተለመደ ነው።
ባለፈው ወር አንድ የክርስትና እምነት ተከታይ የቁርዓንን ገጾች አቃጥሏል በሚል ተወንጅሎ ጥቃት ከተፈፀመበት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱ አልፏል።
ሐሙስ ዕለት የተፈፀመውን ጥቃት የሚያሳይ ቪዲዮ ከወጣ በኋላ በፓኪስታን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ቪዲዮው የግለሰቡ አስክሬን በመንገድ ላይ ሲጎተት እና በኋላም ላይ ሲቃጠል አሳይቷል።
ፖሊስም የግለሰቡ አስክሬን መቃጠሉን ያረጋገጠ ሲሆን ከክስተቱ ጋር ተያይዞ 11 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል።
የማላንካንድ ፖሊስ አዛዥ መሐመድ አሊ ፣ በበጋ ወቅት የሚጎበኘውን የስዋት ሸለቆ ለመጎብኘት ወደ አካባቢው ያመራውን ግለሰብ ፖሊስ ከታደገው በኋላ በአካባቢው የሚገኝ መስጊድ ሰዎች እንዲሰባሰቡ በመቀስቀስ ጥቃቱን አቀጣጥሏል ሲሉ ወንጅለዋል።
የፖሊስ አዛዡ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከተጎዱት መካከል ስምንቱ የፖሊስ መኮንኖች ናቸው።
በስዋት ክልል የፖሊስ መኮንን የሆኑት ዛሂዱላህ በበኩላቸው የኡርዱ ፖሊስ በቁጣ የተሰባሰቡ ሰዎችን ለመበተንና የተዘጉ መንገዶችን ለመክፈት ጥረት ማድረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በድርጊቱ ላይ በተሳተፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ክስ መክፈቱንም ፖሊስ ገልጿል።ፖሊስ እንዳለው በድርጊቱ ከተሳተፉት መካከል እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችም ይገኙበታል።
ከክስተቱ በኋላ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል አሰማርተዋል።
ቢቢሲ ኡርዱ እንደዘገበው ከሆነ በከተማዋ ያሉ ሆቴሎች በቱሪስቶች ሙሉ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ከተማዋን ለቀው ለመውጣት እየተጣደፉ ነው።
ፓኪስታን ሃይማኖትን ማራከስ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጋ ከደነገገች በኋላ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ጨምረዋል።
ያልተረጋገጡ ክሶችም ተቃውሞ እና የደቦ ጥቃት ያስነሳሉ።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብዙውን ጊዜ የጥቃቱ ኢላማ እንደሚሆኑ ሲገልጹ ቆይተዋል።
በፓኪስታን 96 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ሙስሊም ሲሆን ኢራን፣ ብሩኔ እና ሞሪታኒያን ጨምሮ በሌሎች አገሮችም ሃይማኖትን ማራከስ እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት ያስቀጣል።












