በፓኪስታን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኩላሊቶችን ለሽያጭ ያዋሉ አዘዋዋሪዎች ተያዙ

ቀዶ ሕክምና እየተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜናዊ ምስራቅ ፓኪስታን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኩላሊቶችን በመውሰድ ለሸያጭ አውለዋል የተባሉ የሰውነት አካል አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሰውነት አካል አዘዋዋሪዎች ቡድን ስምንት አባላት መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

የዚህ እንቅስቃሴ መሪ ዶክተር ፉዋድ ሙክታር ከ300 በላይ ኩላሊቶችን ከህመምተኞች በማውጣት ለሃብታም ደንበኞች በመሸጥ ንቅለ ተከላ አድርጓል በሚልም ተከሷል።

ዶክተሩ ከዚህ ቀደም ከፈጸማቸው የህክምና ስህተቶች ጋር በተያያዘ አምስት ጊዜ በቁጥጥ ሥር ውሎ ነበር።

በእነዚህ ወቅቶችም የዋስትና መብቱን ማስከበር ችሏል።

የአካል ክፍሎቻቸውን በማስወጣት ሂደቱም ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

ቡድኑ በምስራቃዊ ፑንጃብ ግዛት እና ፓኪስታን በምታስተዳድራት ካሽሚር ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ይታመናል።

ንቅለ ተከላዎቹ የተከናወኑት ህመምተኞቹ በማያውቁበት እና በመኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑን የፑንጃብ ግዛት አስተዳዳሪ ሞህሺን ናቅቪ ተናግረዋል።

ዶክተሩ ቀዶ ህክምናውን በሚያደርግበት ወቅት ረዳቱ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው አንድ የመኪና መካኒክ መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

መካኒኩ ተጋላጭ የሆኑና እና አቅመ ደካሞችን ከሆስፒታሎች በማታለልም ወደ መኖሪያ ቤቱ አምጥቷቸዋል ተብሏል።

እያንዳንዱ ኩላሊትም እስከ 10 ሚሊዮን ሩፒ (120 ሺህ ዶላር) መሸጣቸውንም ናቅቪ አስረድተዋል።

“እኛ ጋር የደረሱት እውነታዎች እና አሃዞች ልብን የሚያሸብሩ ናቸው” ሲሉም ናቅቪ እሁድ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

“በርካታ የንቅለ ተከላዎች እና ሕገወጥ ቀዶ ሕክምናዎች ይደረጋሉ። በአሁኑ ወቅት የደረስንባቸው እነዚህን ነው” ብለዋል።

በፓኪስታን የሰዎች የአካል ክፍሎችን ለንግድ ማዋል ሕገወጥ የተደረገው በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር።

የሰዎች አካላትን ሲሸጡ የተገኙ ሰዎችም ረዘም ያለ እስራት እና ከፍተኛ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣሉ።

ይህም ለውጭ አገር ደንበኞች ሽያጭ እንዲውል የሚበዘብዙ ዶክተሮች፣ ደላላዎችና አሻሻጮች ተግባርን ያስቆመዋል በሚል ያለመ ነው።

በጥር ወር የፑንጃብ ፖሊስ ጠፍቶ የነበረ የ14 ዓመት ልጅ ኩላሊቱ ተወስዶ አስከሬኑ በመሬት ውስጥ በሚገኝ ቤተሙከራ አግኝቷል። በዚህም አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረ የሰውነት አካል አዘዋዋሪዎች ቡድን እንዳለም ይፋ አድርጓል።