የመኪና አምራቹ ቴስላ በዘረኝነት ክስ ለቀድሞ ሰራተኛው 3.2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወሰነበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤሌክትሪከ መኪና አምራቹ ቴስላ ለአንድ የቀድሞ ጥቁር ሰራተኛው 3.2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት።
ኦውን ዲያዝ የተባለው የቀድሞ ሰራተኛ ኩባንያው አጸያፊ የዘረኝነት ስድቦችን ጨምሮ ላልተገባ የስራ ሁኔታ ዳርጓል በሚል ክስ ማቅረቡን ተከትሎም ነው ብያኔው የተላለፈው።
ኦውን ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2016 በፍሪሞንት ፋብሪካ በማሽን ሰራተኛነት ያገለግልበት በነበረበት ወቅት ዘር ላይ ባነጣጠረ መልኩ ለአደገኛ የስራ ሁኔታ ተጋልጧል ብለዋል የፌደራል ዳኞች።
ሆኖም ክፍያው በአውሮፓውያኑ 2021 ከተወሰነለት 137 ሚሊዮን ዶላር 98 በመቶ ቀንሷል።
ባለፈው ዓመት አንድ ዳኛ የካሳ ክፍያው ከመጠን በላይ እንደሆነ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተከትሎም ነው ይህ የገንዘብ መጠን የተወሰነው።
ኦውን ዲያዝ በስራው ምክንያት ለደረሰበት ጭንቀት 175 ሺህ ዶላርን ጨምሮ በአጠቃላይ 3.2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፍሎታል።
“ችሎቱ አዲስ ማስረጃ እንድናቀርብ ቢፈቅድልን ኖሮ ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ዜሮ ይሆን ነበር” በማለት የቴስላ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤለን ማስክ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
“ዳኞች ባገኙት መረጃ የቻሉትን ሁሉ አድርገው ውሳኔ አስተላልፈዋል። ይህንንም ውሳኔ አከብራለሁ” ሲልም ኤለን አክሏል።
ሆኖም ቴስላ ምን አይነት አዲስ ማስረጃ እንደሚያቀርብ ኤለን መስክ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የቴስላ ጠበቃ አሌክስ ስፒሮ እንዲሁ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ኩባንያው አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄም ምላሽ አልሰጠም።
በመጀመሪያው ክስ ኦውን ዲያዝ ጥቁር ሰራተኞች በካሊፎርኒያ በሚገኘው የመኪና ማምረቻ ከባርነት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እንደገጠማቸው አቅርቧል።
በፋብሪካው ግድግዳዎች አጸያፊ የዘረኝነት ስድቦች እንዲሁም በመታጠቢያ ቤቶች በተመሳሳይ አጸያፊ ጽሁፎችና ምስሎች እንደሚያጋጥማቸው ተጠቅሷል።
ጥቁሮች በአብዛኛው የሚሰሩባቸው ቦታዎች የባርነት ታሪካዊ ሁኔታን በሚጠቅስ መልኩ “ዘ ፕላንቴሽን” (የእርሻ ቦታ) በሚልም በዘረኝነት እንደሚጠቀስም ተገልጿል።
አንድ ሰራተኛ በቀን ከ50 እስከ 100 ያህል የዘረኝነት ስድቦችን ማስተናገዱ ተገልጿል።
ቅሬታው ለቴስላ ተቆጣጣሪዎች ቢቀርብም ኩባንያዎች ምንም አይነት እርምጃ አልወሰደም ሲልም ጥፋተኛ ሆኖ ያገኘው በሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ነው።












