አሌንከሳንደር ኢሳክ በተፈጸመበት "ግድ የለሽ" ጥፋት ምክንያት ለሁለት ወራት ከሜዳ እንደሚርቅ ተሰማ

አሌክሳንደር ኢሳክ ጉዳት ደርሶበት ሜዳ ላይ ተኝቶ የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢሳክ ለሊቨርፑል በ16 ጨዋታዎች 3 ጎሎች ብቻ ነው ያስቆጠረው

የሊቨርፑል አሠልጣኝ አርነ ስሎት አጥቂያቸው አሌክሳንደር ኢሳክ "ለጥቂት ወራት" ከሜዳ እንደሚርቅ አስታወቁ።

ኢሳክ የቶተንሀሙ ተከላካይ ሚኪ ቫን ደ ቬን በፈጸመበት "ግድየለሽ ጥፋት ምክንያት" ነው ለሁለት ወራት ከሜዳ የሚርቀው ብለዋል።

ኤርትራዊ-ስዊዲናዊው አጥቂ ሊቨርፑል ቶተንሀምን 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር ነው ጉዳት የደረሰበት።

ኢሳክ ግራ እግሩ ላይ የመሰጠንጠቅ አደጋ እንዳጋጠመው እና ቀዶ ሕክምና እንደተደረገለት ክለቡ ሊቨርፑል ይፋ አድርጓል።

"ረዥም ጊዜ ከሜዳ የሚያርቅ ጉዳት ነው። ለጥቂት ወራት አናየውም" ያሉት ስሎት፤ጉዳቱ "እሱንም ሆነ እኛን በጣም አበሳጭቶናል" ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል።

በጨዋታው ሚኪ ቫን ደ ቬን ባደረሰው ጉዳት ምክንያት ቅጣት ባይገጥመውም የቡድን አጋሩ ዣቪ ሲመንስ የአገሩ ልጅ በሆነው ቨርጂል ቫንዳይክ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ይታወሳል።

ኢሳክ ላይ የደረሰው ጉዳት ያንገበገባቸው የሚመስሉት ስሎት "ይህ ለኔ ግድ የለሽ የሆነ ጥፋት ነው" ብለዋል።

"ዣቪ ሲመንስ ያደረሰው ጥፋት አስቦበት ያደረገው አይደለም። ቫን ደ ቬን ግን 10 ጊዜ ይህን ታክል ቢደጋግመው 10 ጊዜ ተጫዋች ላይ ጉዳት ያደርሳል።"

የቀድሞው የሊቨርፑል ተከላካይ ጄሚ ካራገር ኢሳክ መጎዳትን ለሊቨርፑል "ትልቅ ኪሳራ" ብሎ፤ ነገር ግን ቫን ደ ቬን የፈጸመውን ጥፋት "እኔም ልፈጽመው የምችለው ነው" የሚል አስተያት አክሏል።

ሊቨርፑል በመጪው ቅዳሜ በሜዳው ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል።

የሊቨርፑሉ የክንፍ መስመር ኮከብ ሞሐመድ ሳላህ ከአገሩ ግብፅ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ሞሮኮ በማቅናቱ የቀያዮቹ የአጥቂ መስመር የሳሳ ይመስላል።

ሌላኛው የፊት መስመር ተጫዋች ኮዲ ጋክፖ ጉዳት ላይ ቢሆንም ቅዳሜ ከዎልቭስ ጋር ለሚኖረው ግጥሚያ ሊደርስ እንደሚችል ተነግሯል።

ከጉዳት የተመለሰው ጀረሚ ፍሪምፖንግ ባለፈው ቅዳሜ ከቶተንሀም ጋር በነበረው ፍልሚያ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት ለስሎት አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል።

አሌክሳንደር ኢሳክ በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት የብሪታኒያ ክብረ ወሰን በሆነ 125 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ከኒውካስል ወደ ሊቨርፑል መምጣቱ ይታወሳል።

የ26 ዓመቱ አጥቂ ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ ጊዜ የወሰደበት ሲሆን ለቀያዮቹ በ16 ጨዋታ ሦስት ግቦችን ብቻ ነው ማስቆጠር የቻለው።

ኢሳክ በክረምት ወቅቱ ክለቡ ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ እስያ ሲያቀና አብሮ አልተጓዘም። ክለቡ ይህ የሆነው አነስተኛ ጉዳት ደርሶበት ነው ቢልም የኋላ ኋላ በተጨዋቹና በኒውካስል መካከል አለመስማማት እንደነበር ይፋ ተደርጓል።

ኢሳክ በቀድሞ ክለቡ ሪያል ሶሲየዳድ ካምፕ ሲሰለጥን ቆይቶ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ሊዘጋ ሰዓታት ሲቀሩት ነው ለሊቨርፑል የፈረመው።

አርነ ስሎት ኢሳክ ወደፊት ለሊቨርፑል ትልቅ ሚና ይጫወታል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።