እስራኤል በኢራን እስር ቤት ላይ ጥቃት በፈፀመችበት ወቅት የሆነው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በፈፀመችበት ወቅት በኤቪን እስር ቤት ለብቻዋ ታስራ የነበረችው የፖለቲካ አክቲቪስቷ ሞታሃረህ ጎኔይ "ለእኔ ገሃነም የሆነብኝ እስራኤል ጥቃት በፈፀመችበት ጊዜ አልነበረም፤ ሲኦል የሆነብኝ [የእስር ቤቱን] በር ሳይከፍቱልን በቀሩበት ጊዜ ነበር" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጎኔይ በኤክስ ገጿ ላይ የኢራንን መንግሥት የሚተች ጽሑፍ ከለጠፈች ከአስር ቀን በኋላ ነው በቁጥጥር ስር የዋለችው።
በአውሮፓውያኑ ሰኔ 23 የ12 ቀኑ ጦርነት ሊያበቃ ሲል እስራኤል ከኢራን እስር ቤቶች መካከል ዝነኛ የሆነውን ኤቪን ማረሚያ ቤትን ደበደበች።
የሳተላይት ምሥሎች፣ የዓይን እማኞች እንዲሁም በቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ተገኝተው የተረጋገጡ ምሥሎች ስለጥቃቱ እና ስለሞቱት ሰዎች አዲስ መረጃን አሳይተዋል።
ቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ከሟች ዘመዶች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል ሦስቱ፣ ኢራናዊ አሜሪካዊ እስረኛን ጨምሮ ማንነታቸውን እና ሁኔታውን በገለልተኝነት አረጋግጧል።
የኢራን ባለሥልጣናት እስካሁን ይፋ ያደረጉት የማረሚያ ቤቱን ሠራተኞች ስም እና ማንነት ብቻ ነው።
በቴህራን ሰሜናዊ ጫፍ ላይ የሚገኘው እና ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት ማረሚያ ቤት ከ1979 አብዮት በፊትም ሆነ አሁን፣ ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ታስረውበታል።
እስራኤል በሰኔ ወር በኤቪን ማረሚያ ቤት ጥቃት በመፈፀም ያደረሰችው ጉዳት በኢራን ምድር ከደረሱት ሁሉ የከፋው ነው ተብሏል።
የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሉት 80 ሰዎች ተገድለዋል።
ከእነዚህም መካከል የእስር ቤቱ ሠራተኞች፣ እስረኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ የመጡ ሰዎች እና በአቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ይገኙበታል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ነሐሴ አጋማሽ ላይ ባወጣው ዘገባ እስራኤል በኢራን ኤቪን እስር ቤት ላይ የፈጸመችው የአየር ድብደባ ከሕግ ውጪ፣ ዒላማ ያልለየ እና ግልፅ የሆነ የጦር ወንጀል መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በኤቪን ማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት የፈፀመበትን ምክንያት ሲገልጽ ተቋሙ "በእስራኤል ላይ ለሚደረገው የስለላ ዘመቻ" ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, User generated content
"እስረኞች ጠባቂዎቻቸውን ሲረዱ ነበር"
ሞታሃረህ ጎኔይ በግቢው ውስጥ ፍንዳታው የደረሰበትን ቅጽበት ታስታውሳለች።
" ሦስተኛውን ፍንዳታ በሰማሁ ጊዜ፣ መውጫ እንደሌለ እርግጠኛ ነበርኩኝ። ያለ የሌለ ኃይሌን ተጠቅሜ በሩን ደበደብኩት፤ ነገር ግን አልተከፈተም። ይህ የሕይወታችን ፍጻሜ ነው ስል አሰብኩና ደህና ሁኑ ብዬ ተሰናበትኩ።"
ከክፍሏ ውስጥ ሌላ እስረኛ ነፃ እንድትወጣ ከረዳቻት በኋላ በጢስ የታፈነ መተላላፊያ ተቀበላት፤ መተንፈስ አልቻለችም።
ጎኔይ መጀመሪያ ላይ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እስረኞች እንዳያመልጡ ለመከልከል ሞክረው እንደነበር እና አንዳንድ የእስር ቤት መርማሪዎችም አስፈራርተዋቸው እንደነበር ታስታውሳለች።
ሆኖም "አስፈሪ ነገር ግን ሰብዓዊነትን የታየበት" ባለችው ትዕይንት እስረኞቹ የተጎዱ ጠባቂዎችን ለመርዳት ሲጣደፉ፣ የተደናገጠች ሴት ፖሊስን ሲያረጋጉ እንዲሁም የሚያለቅስ መርማሪን ቁስሉን ሲያስሩ ተመልክታለች።
የሌላ ክፍል እስረኞች ደግሞ በእስር ቤቱ ክሊኒክ ውስጥ መውጫ ያጡትን ዶክተሮችን እና ነርሶችን ለመርዳት ይጣደፉ ነበር።
በጥቃቱ ክፉኛ የተጎዳው ከኤቪን ዶክተሮች መካከል አንዱ የሆነው ሰኢድ ማካሬም በኋላ ላይ በኢንስታግራም ገፁ "በአንድ ወቅት ያከምኳቸው እስረኞች ሕይወቴን አድነውታል" ሲል ጽፏል።
ለደኅንነቷ ስትል ስሟን ከመግለጽ የተቆጠበች በኤቪን የምትገኝ ሌላ ሴት ጥቃቱን የተፈፀመበትን ቅጽበት ለቢቢሲ ገልጻለች።
"መጀመሪያ ላይ ብዙ ፍንዳታዎች በተከታታይ ተሰምተዋል። ድምጹም ለሁለት ደቂቃዎች ያህል ቀጠለ። በመጀመሪያ ላይ መስኮቶቹ ስለተሰባበሩ አልጋችን ላይ ቆየን። ከዚያም ልብሳችንን ለብሰን ሁላችንም በዕድሜ ከፍ ያሉትን ሴቶችን ወደ ታች በማውረድ ረድተናል። ከእስር ቤቱ ውስጥ ማንም አልረዳንም። በሩን ዘግተው መውጣት አትችሉም አሉን።"

የፎቶው ባለመብት, MAXAR
የጥቃቱ መጠን
ቢቢሲ የተመለከታቸውን መረጃዎች መሠረት በማድረግ እስራኤል ኤቪንን በትንሹ ስድስት ተተኳሾች በመጠቀም በግቢው ውስጥ ቢያንስ 28 ሕንፃዎች ላይ ጉዳት ማድረሷን መረዳት ችሏል።
የእስራኤል መከላከያ "በኢራን ሕዝብ ላይ የጭቆና ምልክት" በሆነው እስር ቤትን "ዒላማ ያደረገ ጥቃት" እንደፈፀመ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እርምጃዎች መወሰዱን ገልጿል።
ነገር ግን ፍንዳታው ከደረሰ ከደቂቃዎች በኋላ የፖለቲካ እስረኛ ዘመዱን ለመጠየቅ የመጣ ሰው "ከእስር ቤቱ የሚወጡ ሰዎች በየቦታው አስከሬኖች እንዳሉ ይናገሩ ነበር። አንዳንድ እስረኞች ወጥተዋል፣ አንዳቸውም ለማምለጥ አልሞከሩም፤ ተደናግጠው ነበር።"
የኢራን ባለሥልጣናት በግርግሩ ወቅት 75 እስረኞች ማምለጣቸውን ተናግረዋል። አንዳንዶቹ በኋላ ተይዘው ወይም በፈቃዳቸው ተመልሰዋል።
ከሞቱት መካከል ጠባቂዎች፣ እስረኞች እና ጠያቂዎች ይገኙበታል
የኢራን ባለሥልጣናት በጥቃቱ ከተገደሉት 80 ሰዎች መካከል 42ቱ የእስር ቤቱ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ አምስቱ ደግሞ ታራሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ስማቸውን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ ፐርሺያ ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ወንጀል ተከስሶ የታሰረው የአሜሪካ እና የኢራን ዜግነት ያለው ማሱድ ቤህባሃኒ ከሞቱት ታራሚዎች መካከል አንዱ መሆኑን አረጋግጧል።
ቤተሰቦቹ በጥቃቱ ወቅት በመውደቁ የልብ ድካም አጋጥሞት ሞቷል የሚል፣ እንዲሁም ከእስር ቤት በሚወጡበት ወቅት የልብ ድካም ስላጋጠመው እና ወዲያውኑ ሕክምና ባለማግኘቱ ሕይወቱ አልፏል የሚል የተሳከረ መረጃ ደርሷቸዋል።
የ37 ዓመቱ አርቪን መሐመዲ በጦርነቱ ወቅት አባቱ ከእስር ቤት በዋስ እንዲለቀቁ ለማድረግ የዋስትና ጉዳዮችን በአስተዳደር ሕንፃ ውስጥ እያስጨረሰ ባለበት ወቅት መገደሉን ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, BBC / User generated content
ታዋቂ ሠዓሊ የሆነችው የ61 ዓመቷ መህራንጊዝ ኢሜንፖየር መኖሪያ ቤቷ በኤቪን ማረሚያ ቤት አቅራቢያ የነበረ ሲሆን፣ በጥቃቱ ወቅት መገደሏን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።
ታዋቂው ኢራናዊ ደራሲ እና የኢማንፖየር የቀድሞ ባለቤት ሬዛ ካንዳን ማሃባዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢማንፑር የተገደለችው በእስር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ መግቢያ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ነው።
በፍንዳታው ጥንካሬ የተነሳ አስከሬኗ ከማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪ ተገኝቷል።
በጥቃቱ ከተገደሉት ሌሎች ሰዎች መካከል በአካባቢው የምትኖር የአንድ ዓመት ሕፃን እናት የሆነች ሴት፣ እስረኛን ለማስፈታት የሄደች በጎ አድራጊ፣ አምስት የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች፣ 13 አዲስ ምልምል ወታደሮች እና የአንድ ማኅበራዊ ሠራተኛ የአምስት ዓመት ልጅ ይገኙበታል።
በኤቪን እስር ቤት ላይ ከደረሰው ጥቃት በኋላ የአንዳንድ እስረኞች ዕጣ ፈንታ አልታወቀም። አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች 100 ልውጥ ፆታ ያላቸው እስረኞች መገደላቸውን ቢናገሩም የቢቢሲ ፐርሺያ ምርመራ ግን ይህ እውነት እንዳልሆነ አረጋግጧል።
ልውጥ ፆታ ያላቸውን ታራሚዎች ጉዳይ የሚከታተሉት ጠበቃው ሬዛ ሻፋካህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የእነርሱ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ስጋቶች አሉብን። እነዚህ እስረኞች አሁን የት እንዳሉ ማንም አያውቅም።"
ኢቪን ለምን ዒላማ ሆነ?
እስራኤል ማረሚያ ቤቱ "ለስለላ ሥራ እየዋለ ነው" ያለች ቢሆንም ቢቢሲ ትክክለኛ ዒላማዎችን እና ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎችን በተመለከተ እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎች ሞትን በተመለከተ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአንድ ወር በኋላ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለ ድርጊቱ ሪፖርት አውጥቷል።
የድርጅቱ ከፍተኛ ዳይሬክተር የሆኑት ኤሪካ ጉቬራ ሮሳስ "ወታደራዊ ተቋማት ባልሆኑ ላይ ጥቃቶችን መፈፀም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ በጥብቅ የተከለከለ ነው። እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶችን አውቆ እና ሆን ብሎ መፈጸም የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ኤቪን "ወታደራዊ ተቋም አይደለም" ካለ በኋላ ጥቃቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋትን ይጥሳል ብሏል።
በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ቶም ዳነንባም ለቢቢሲ እያንዳንዱ የእስር ቤቱ ክፍል በወታደራዊ ጠቀሜታው መመዘን አለበት ብለዋል።
አሁን ባለው መረጃ መሠረት የተገደሉት በሙሉ ሰለማዊ ዜጎች ጠባቂዎች፣ እስረኞች፣ ጠያቂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ብለዋል።
ከጥቃቱ በኋላ የእስረኞቹ ዕጣ ፈንታ
እስራኤል በኤቪን እስር ቤት ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ታራሚዎች ማረሚያ ቤቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል መሰማራቱን ተከትሎ እስረኞቹ፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ እጃቸው እና እግራቸው ታስሮ በኃይል ወደ ሌላ ቦታ መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሴት እስረኞች ወደ ቃርቻክ ማረሚያ ቤት፣ ወንዶች ደግሞ ወደ ቴህራን ቦዝርግ (ፋሻፉዬህ) እስር ቤት ተልከዋል።
ሁለቱም ማረሚያ ቤቶች የሚገኙት ከቴህራን በስተደቡብ በረሃ ውስጥ ነው።
የኢራን የፍትህ አካላት ጥቃቱ ከተፈጸመ ከ45 ቀናት በኋላ በእስረኞች እና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በፖለቲካ እስረኞች ላይ ዳግም ጥቃት እና ማንገላታት መፈጸሙ ከተገለፀ በኋላ እስረኞች ወደ ኤቪን እየተመለሱ መሆኑን አስታውቋል።
አንዳንድ እስረኞች ለቢቢሲ እጅና እግራቸው በካቴና እንዲታሰር እና እምቢ ሲሉም በጠባቂዎች ተከብበው ከተሽከርካሪዎች በኃይል እንዲወርዱ ተደርጎ አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
በዕድሜ የገፉ እስረኞች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ አንዳንዶቹም መንገድ ላይ እንዲተኙ ተደርገው እጃቸው በካቴና ታስሯል።
የኢራን የፍትሕ ባለሥልጣናት እስረኞች ላይ አካላዊ ጥቃት መድረሱን ወይም እጃቸው እና እግራቸው መታሰሩን ክደዋል።
አንዳንድ እስረኞች ከእስር ቤቱ እንዲወጡ በተደረጉበት ወቅትም ሆነ ወደ ኤቪን እስር ቤት ከተመለሱ በኋላ የተፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ወቅት የማምለጥ ዕድል እያላቸው በፍርስራሽ ስር የተቀበሩትን ለመርዳት በመረጡት ላይም ያነጣጠረ ነው ይላሉ።
ቢቢሲ ፐርሺያ በኢራን ውስጥ በመንግሥት እገዳ ተጥሎበታል።
የኢራን ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየትም ሆነ ቃለ መጠይቆች ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።















