የኬብሮን ከንቲባ እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ በምታደርገው መስፋፋት " ከለላ የሚሰጠን የለም" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእስራኤል በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ቴልአቪቭ በቅርቡ በአካባቢው እያደረገች ያለችው መስፋፋት በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር ሒደት "ማብቂያ" ነው አሉ።
የኬብሮን ተጠባባቂ ከንቲባ አስማ አል ሻራባቲ በእስራኤል የሚኒስትሮች ካቢኔ በቅርቡ ይፋ የተደረጉት አዲስ የሕግ ለውጦች የፍልስጤም መንግሥት በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች በከተማ ዕቅድ እና ልማት ላይ የሚያስተላልፉት ውሳኔ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
"ከለላ አለማግኘታችንን እያየን ነው" ያሉት የኬብሮን ከንቲባ አል-ሻራባቲ "ተቋማት እየጠበቁን አይደለም። ዓለም የጋዛን ሰርጥና የጅምላ ጭፍጨፋ እያየ ነው፤ እና ስለእሱ እያወራ ነው፤ ግን ከዚያ በላይ ምንም የለም" ብለዋል።
ኬብሮን በዌስት ባንክ የምትገኝ ፍልስጤምን እና እስራኤልን የምታወዛግብ ከተማ ናት።
በአካባቢው የእስራኤል ወታደሮች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ እስራኤላውያን ሠፋሪዎችን ይጠብቃሉ።
እሁድ እለት የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ በዌስት ባንክ ውስጥ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በአሜሪካ በሚደገፈው የኦስሎ ስምምነት መሠረት በእስራኤልም ሆነ በፍልስጤም መሪዎች የተፈረመውን የሥልጣን ክፍፍል በተመለከተ ከፍተኛ ለውጦችን አጽድቋል።
እነዚህም የእስራኤልን ቁጥጥር ከወታደራዊ ወረራ ባሻገር ማስፋት፣ በፍልስጤም በሚተዳደሩ አካባቢዎች የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን መስጠት እንዲሁም ውሃ፣ የአካባቢ እና የአርኪኦሎጂ ሀብቶችን ለመጠበቅ በዌስት ባንክ ውስጥ "የቅርስ ቦታዎችን" ለመቆጣጠር ሰፊ ሥልጣንን ያካትታሉ ይላሉ።
እስራኤል የፓትሪያርኮች ዋሻ ተብሎ የሚታወቀውን እና በአይሁዶች ዘንድ ቅዱስ ስፍራ ተደርጎ የሚቆጠረውን በኬብሮን በኢብራሂሚ መስኪድ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ስፍራ ለመረከብ እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።
"አሁን የትኛውንም ሕንፃ በቀላሉ ወስደው ጥንታዊ ሲሉ የማወጅ ሥልጣን አላቸው፤ እናም የፍልስጤም አስተዳደር በአካባቢው የሚኖር የከተማ ዕቅድ ወይንም ልማት ላይ በሚኖር ውሳኔ ላይ ተሳትፎ አይኖረውም" ሲሉ አል ሻራባቲ ተናግረዋል።
ተጠባባቂ ከንቲባዋ ስለ እስራኤል ዕቅዶች ምንም ይፋዊ ማስጠንቀቂያዎች እንዳልደረሷቸው እና ዝርዝር ጉዳዮችን ከእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደሰሙ ተናግረዋል።
እስራኤል በኬብሮን ለሚገኙ የአይሁድ ሰፋሪዎች የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት መስጠት ለመጀመር እና በዌስት ባንክ በኩል ለእስራኤል ዜጎች የመሬት ባለቤትነትን ለመስጠት አቅዳለች።
ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ እና በፍልስጤም ሕግ መሠረት ንብረታቸውን ፍልስጤማውያን ላልሆኑ ሰዎች እንዳይሸጡ ታግደዋል።

ቀደም ሲል ለእስራኤላውያን በድብቅ መሬታቸውን የሸጡ ግለሰቦች በዚህ የቴህራን አዲስ እቅድ መሠረት አደጋ ይገጥማቸዋል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ የእስራኤል ውሳኔ ዶናልድ ትራምፕን በቀጠናው ውስጥ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደናቅፍ እና ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ የአሜሪካ መንግሥት "ጠንካራ ምላሽ" እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
እስካሁን ድረስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል ዌስት ባንክን ሙሉ በሙሉ ወደ ግዛቷ ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ያላቸውን ተቃውሞ ከመናገር ባለፈ ያሉት ብዙ ነገር የለም።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገሮች ባለፈው ዓመት የፍልስጤም መንግሥትን እውቅና ሰጥተዋል።
አሁን እስራኤል በፍልስጤም ቁጥጥር ስር ባለው ግዛት ውስጥ ለሲቪል ሥልጣን ሰጥታለች። ቢቢሲ እርምጃውን በተመለከተ የዩኬን መንግሥት ምላሽ ጠይቋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃሚሽ ፋልኮንነር ሰዎች በሚቀጥሉት ቀናት ከዩኬ መንግሥት የሚሰሙት ነገር እንደሚኖር ጠቁመዋል።
"ውሳኔውን አጥብቀን እናወግዛለን፤ ተቀልብሶ እናያለን ብለን እንጠብቃለን።ሁሉም የእስራኤል ወዳጆች ይህ ከባድና አስከፊ ስህተት ነው እያሉ ነው።" ብለዋል።
የዓለም ትኩረት በጋዛ ላይ በሆነበት ወቅት እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የምታደርገው መስፋፋት ቀጥሏል።
ነገር ግን ትራምፕ ለጋዛ ያላቸው እቅድ የተመሰረተው የአረብ አገራት ድጋፍ ላይ ሲሆን ብዙዎቹም የፍልስጤም መንግሥት ላይ የሚኖረው ድጋፍም እንዲጠናከር እየጠየቁ ነው።
በኬብሮን እና በቀሪው የዌስት ባንክ ክፍል የሚሆነዉ ነገር አሁንም ትራምፕ ለጋዛ ያላቸውን ራዕይ እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ያላቸውን እቅድ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።















