በእስራኤል እስር ቤቶች ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ይፋ ያወጡ ፍልስጤማውያን

ሳሚ አል ሳኢ ለቢቢሲ ቃለ ምልልስ በሰጠበት ወቅት - መላጣ ሲሆን አጭር ጥቁር ፂም አለው። ጥቁር ፍሬም ያለው መነጽር እና ጥቁር ካናቴራ አድርጓል።
የምስሉ መግለጫ, ሳሚ አል ሳኢ

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሑፍ ወሲባዊ ጥቃት የሚገልጽ ይዘት ስላለው አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ ይችላል።

በቅርቡ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞች አያያዝን በተመለከተ በወጡ ሪፖርቶች ላይ የተገለጸውን ዓይነት ድብደባ እና ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሁለት ፍልስጤማውያን ወንዶች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የተባበሩት መንግሥታት ፀረ ስቅይት ኮሚቴ ባለፈው ወር በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ በፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ "የተደራጀ እና ሰፊ የሆነ የማሰቃየት እና የጭካኔ አያያዝ" የሚያሳይ "የመንግሥት ፖሊሲ" መኖሩን የሚያሳዩ ሪፖርቶች በጣም እንዳሳሰበው ገልጿል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ክሶች "በእጅጉ እየጨመሩ መጥተዋል" ብሏል።

የእስራኤል እና የፍልስጤም የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሌሎች ሪፖርቶች በበኩላቸው ይህንን "ስልታዊ" ጥቃት ብለውታል።

እስራኤል ግን ሁሉንም ክሶች ውድቅ አድርጋለች።

ነገር ግን የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከሁለት ዓመት በፊት በተፈፀመው ጥቃት እና በጋዛ የእስራኤል ታጋቾች አያያዝ ምክንያት በአገሪቱ የተከሰተው ቁጣ በእስር ቤቶች ውስጥ በተለይም ለሐማስ እና ለጥቃቶቹ ድጋፍ በሰጡ እስረኞች ላይ እርምጃ የመውሰድ ልምድ ፈጥሯል።

ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ የተለቀቁ እና በደኅንነት ካሜራ የተቀረጹ ምሥሎች ከጋዛ የመጣ አንድ ፍልስጤማዊ በእስር ቤት ጠባቂዎች ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመበት አሳይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህም የእስራኤል ወታደራዊ እና የፖለቲካ ተቋማት ባለሥልጣናት ከሥራ እንዲለቁ እና ክስ እንዲመሠረት ምክንያት ሆኗል።

አሁን በቤት ዕቃዎች መደብር ውስጥ የሚሠራው የ46 ዓመቱ ሳሚ አል-ሳኢ ቀደም ሲል እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ቱልካራም ከተማ ውስጥ ጋዜጠኛ ነበር።

ጋዜጠኞች የሐማስ እና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖች አባላትን ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ሲያስተባብር ነበር በእስራኤል ወታደሮች ተይዞ የታሰረው።

"አስተዳደራዊ እስር" በመባል በሚታወቀው አወዛጋቢ የእስራኤል ሥርዓት ለ16 ወራት ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሠረትበት በእስር ላይ ቆይቷል።

አል ሳኢ በሰሜናዊ እስራኤል በሚገኘው የምጊዶ እስር ቤት ታስሮ በነበረበት ወቅት ጠባቂዎቹ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 13/2024 ወይም በዚያ ገደማ በከፊል ልብሱን ገፈው እንደደፈሩት ተናግሯል።

ይህን በመናገሩ በዌስት ባንክ ውስጥ በብዛት ወግ አጥባቂ በሆነው የፍልስጤም ማኅበረሰብ ውስጥ የመገለል አደጋ ሊገጥመው ቢችልም ስለደረሱበት ወሲባዊ ጥቃቶች ለቢቢሲ ለመንገር መወሰኑንም ገልጿል።

"አምስት ወይም ስድስት ነበሩ" ይላል አል ሳኢ ጥቃቱን ስለፈጸሙበት ጠባቂዎች ሲናገር።

"እየሳቁ እና እየተዝናኑ ነበር። ጠባቂው 'እየተዝናናህ ነው? ከአንተ ጋር መጫወት እንፈልጋለን፤ ሚስትህን፣ እህትህን፣ እናትህን እና ጓደኞችህንም ወደዚህ ማምጣት እንፈልጋለን' አለኝ" ይላል አል-ሳኢ።

አል ሳኢ ሊሞት እንደሚችል ነበር ያሰበው። "ህመም የፈጠረብኝ አስገድዶ መድፈሩ ብቻ ሳይሆን ከባድ እና እጅግ የሚያም ድብደባም ጭምር ነበር፤ ልሞት እንደምችል ነበር ያሰብኩት።"

እርሱ እንደሚለው ከ15 እስከ 20 ደቂቃዎች ያህል የቆየ ጥቃት ነበር የፈጸሙበት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጠባቂዎቹ ብልቱን በመርገጣቸው ከፍተኛ ህመም እንዳሳደረበትም ተናግሯል።

ድብደባው በየቀኑ ማለት በሚቻል ሁኔታ ይፈጸምበት እንደነበርም ገልጿል። ነገር ግን ፆታዊ ጥቃት ደረሰበት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ብሏል።

በአል ሳኢ ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ቢቢሲ የእስራኤል የእስር ቤት አገልግሎትን የጠየቀ ሲሆን ተቋሙም መግለጫ ልኳል።

በላከው መግለጫ "የምንሠራው በቁጥጥር ሥር ያሉ እስረኞችን ደኅንነት እና መብቶች እያረጋገጥን፤ ሕግን ሙሉ በሙሉ በማክበር ነው " ብሏል።

"ስለተባለው ጥቃት የምናውቀው ነገር የለም። እስከምናውቀው ድረስ ግን በእስር ቤቱ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች አልተፈጸሙም" ሲልም ክሱን አስተባብሏል።

በቀረበው ወሲባዊ ጥቃት ክስ ላይ ምርመራ ጀምሮ እንደሆነ እና የሕክምና ማስረጃዎች ይኖሩ እንደሆነም ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።

የቀድሞዋ የእስራኤል ጦር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ጀኔራል ይፋት ቶመር የሩሻልሚ

የፎቶው ባለመብት, IDF handout

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞዋ የጦር ኃይሎች ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ጀኔራል ይፋት ቶመር የሩሻልሚ በእስራኤል ወታደሮች ተፈፅመዋል የተባሉ ጥቃቶችን ያሳዩ የደኅንነት ካሜራ ምሥሎች ሾልከው ከመውጣታቸው ጋር ተያይዞ ሥራቸውን ለቀዋል።

በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ በደል እንደሚፈጸምባቸው የሚገልጹ ክሶች ለአስርተ ዓመታት ሲቀርቡ ቆይተዋል።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ አንድ ጉዳይ የአገሪቱን አስተዳደር ያንቀጠቀጠ ሲሆን፣ በእስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥ ሐማስን ይደግፋሉ ተብለው በተከሰሱ እስረኞች እና በማቆያ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን አስመልክቶ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት አባብሶታል።

በነሐሴ 2024 በደቡብ እስራኤል ከሚገኘው የስዴ ቴይማን ወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ የተለቀቀው የደኅንነት ካሜራ ምሥል ከጋዛ የመጣ አንድ ፍልስጤማዊ እስረኛ በወታደሮች የስለት ጥቃት ሲፈጸምበት አሳይቷል።

ይህም ግለሰቡ የፊንጢጣ መሸንቆር እንዲገጥመው አድርጓል። ጥቃቱ የተፈጸመው በሐምሌ 2024 እንደሆነም ተገልጿል።

በእስረኛው ላይ ከባድ ጥቃት በመፈጸም እና ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ አምስት የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደሮች ክስ ቀርቦባቸዋል።

ባለፈው ወር በእስራኤል ቴሌቪዥን ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቀርበው የነበሩ ሲሆን፣ ክስ ከቀረበባቸው አራቱ ማንነታቸውን ለመደበቅ ተሸፋፍነው ታይተዋል።

አምስተኛው ወታደር ግን ለቻናል 14 ኒውስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ "ምንም የምደብቀው ነገር የለም" በማለት ፊቱን ለማሳየት ጭምብሉን አውልቋል።

አምስቱም ተጠባባቂ ወታደሮች የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

የደኅንነት ካሜራ ምሥሉ ሾልኮ ከወጣ በኋላ በእስራኤል ጦር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ፣ የጦር ኃይሎች ተሟጋች ሜጀር ጄነራል ይፋት ቶምር የሩሻልሚ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

"ምሥሉ ሾልኮ ለመውጣቱ ሙሉ ኃላፊነት እንደወሰዱ በመግለጽ" ጥቅምት ወር ላይም ሥልጣናቸው ለቀዋል።

የሩሻልሚ በጦር ኃይሉ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ላይ የተሰነዘረውን "የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መቃወም" ፈልገው እንደነበር አስረድተዋል - ይህ ደግሞ ክሶቹ የተጭበረበሩ ናቸው ከሚለው የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች የተወሰደ ነው።

የቀኝ ዘመም ደጋፊዎች በበኩላቸው የተከሰሱትን አምስት ተጠባበቂ ወታደሮች ለመደገፍ በስዴ ቴይማን እስር ቤት ደጅ ላይ ሰልፍ አካሂደዋል።

የቀድሞዋ የጦሩ የሕግ አማካሪ ከኃላፊነታቸው ከመልቀቃቸው በፊት ሐምሌ ወር ላይ በእስራኤል ምክር ቤት በተካሄደ የኮሚቴ ስብሰባ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ፖለቲከኛ የሆኑት ሃኖች ሚልዊድስኪ፣ "አንድን እስረኛ አስገድዶ መድፈር ተቀባይነት አለው ወይስ የለውም?" ሲሉ ተጠይቀው ነበር።

"ዝም በል! ዝም በል!" ብለው በማቋረጥ "አዎ! ሁሉም በሐማስ ጥቃት ውስጥ የተሳተፉ ተዋጊዎች ከሆኑ ሁሉም ነገር ሕጋዊ ነው፤ ሁሉም ነገር!" ሲሉ በቁጣ መልሰዋል።

በስፋት በሚታወቀው በእስራኤል ዲሞክራሲያዊ ተቋም በቅርቡ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ጥናት አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን ከጋዛ የመጡ ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ወታደሮች ላይ ምርመራ ማካሄድን እንደሚቃወሙ አመልክቷል።

አሕመድ [ ስሙ የተለወጠ] ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ በሰጠበት ወቅት ጨለማ ውስጥ የተነሳውና ማንነቱን በግልጽ የማያሳይ ፎቶ
የምስሉ መግለጫ, " ሽብርተኝነትን በመደገፍ" ጥፋተኛ ተብሎ ታስሮ የነበረው 'አሕመድ' ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈፀመበት ተናግሯል

ለዚህ ዘገባ አሕመድ ተብሎ ስሙ የሚጠቀሰው ግለሰብ ከባለቤቱ እና ከ11 ልጆቹ ጋር በዌስት ባንክ ነው የሚኖረው።

አሕመድ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጥር ወር ላይ በወታደሮች የተያዘ ሲሆን፣ በሐማስ የተመራውን እና አብዛኞቹ እስራኤላውያን የሆኑ 1200 ሰዎች የተገደሉበትን እና ሌሎች 251 ሰዎች ታግተው የተወሰዱበትን ጥቃት የሚያወድስ ጽሑፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ካጋራ በኋላ ሽብርተኝነትን በመደገፍ ጥፋተኛ ተብሏል።

ለዚህም አንድ ዓመት የሚደርስ እስር እና 935 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበት ነበር።

አሕመድ በእስራኤል እስር ቤት ሳለም ከባድ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰበት ተናግሯል።

አሕመድ በቤቱ ውስጥ በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች [ሦስቱ] ወደ መታጠቢያ ቤት ወስደው ሙሉ በሙሉ ራቁቱን አድርገው መሬት ላይ እንደጣሉት ገልጿል።

"ጭንቅላቴን ሽንት ቤት ሳህን ላይ አድርገው አንድ ግዙፍ ሰው ጭንቅላቴ ላይ ቆመ። ስለዚህ ጎንበስ አልኩ። ከዚያም ከእስር ቤቱ ውሻ ጋር የሚነጋገር ድምጽ ሰማሁ። ውሻው እንደ እግር ኳስ ተጨዋቹ ሜሲ የሚባል ስም ነው ያለው" ይላል።

ከዚያም በውሻው ወሲባዊ ጥቃት እንዲፈጸምበት እንዳደረጉት ተናግሯል።

"ትንፋሹ ይሰማኝ ነበር። ዘሎ ወጣብኝ። መጮኽ ጀመርኩ። ብዙ በጮኽኩ ቁጥር ራሴን እስክስት ድረስ ይደበድቡኝ ጀመር"

እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት አሕመድ ሁልጊዜ በእስር ቤቱ ጠባቂዎቹ ብልቱ ላይ ጭምር ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበር ገልጿል።

ከእስር የተለቀቀውም የተፈረደበትን የእስር ጊዜ ካጠናቀቀ በኋላ ነው።

አሕመድ ላቀረበው ክስ የሕክምና ማስረጃዎች ይኖሩት እንደሆነ በቢቢሲ ተጠይቆ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለው ገልጿል።

የአሕመድን ክስ በተመለከተ እንዲሁም ጥቃቶችን በተያያዘ ምርመራ ተከፍቶ እንደሆነ የእስራኤል የእስር ቤት አግልግሎት ምላሽ እንዲሰጥ ቢቢሲ የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።

በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን የደኅንነት እስረኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም ጥቅምት ወር ላይ በሐማስ ከተፈጸመው ጥቃት በፊት ከነበረው አሃዝ በግማሽ ይበልጣል።

በቅርቡ በተበባሩት መንግሥተት ኮሚቴ የወጣው ሪፖርት የሐማስ ጥቃት አውግዞ፤ እስራኤል ለዚህ እየሰጠችው ያለው የአፀፋ ምላሽ እና በጋዛ የሰዎች ሕይወት መጥፋት ክፉኛ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ከሐማስ ጥቃት በኋላ ታግተው ከተወሰዱ ሰዎች መካከል የተወሰኑት እና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦች በሐማስ እና አጋሮቹ ፆታዊ ጥቃት፣ አስገድዶ መድፈር እና ማሰቃየት ተፈጽሞብናል ብለዋል።

ሐማስም ከእስራኤል ጋር ተባብረዋል ያላቸውን ፍልስጤማውያንን ጋዛ ውስጥ በይፋ ገድሏል።

በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባልሆነውና የሐማስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቀናቃኝ የሆነው የዌስት ባንክ ክፍሎችን የሚመራው የፍልስጤም ባለሥልጣን በሚያስተዳድራቸው እስር ቤቶች ውስጥም ጥቃት ተፈጽሟል የሚሉ ክሶች አሉ።

ቢቢሲም የአስተዳደሩን የፀጥታ መኮንኖች ድብደባ እና የኤሌክትሪክ ንዝረት በመጠቀም ስቅይት እንደተፈጸመበት የገለጸን አንድ እስረኛ አነጋግሯል።

የፍልስጤም አስተደዳር በክሱ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ቢቢሲ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም። ሆኖም ቀደም ብሎ "ስልታዊ ጥቃት" ይፈጽማል በሚል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

 ሳሚ አል ሳኢ ታስሮበት የነበረው ምጊዶ እስር ቤት ከፋይል ተገኘ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳሚ አል ሳኢ ታስሮበት የነበረው ምጊዶ እስር ቤት ከፋይል ተገኘ ምሥል

በጥቅምት ወር ለተባበሩት መንግሥታት ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት፣ አምስት የእስራኤል የሰብአዊ መብት ቡድኖች "በሁሉም እስር ቤቶች ውስጥ የማሰቃየት፣ የጭካኔ፣ ኢ- ሰብአዊ እና አዋራጅ አያያዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል፤ ፍልስጤማውያንን ዒላማ ያደረገ 'የመንግሥት ፖሊሲ' ተግባራዊ ሆኗል" ብሏል።

አዳላህ የተባለው እና በእስራኤል ውስጥ የሚፈጸመውን ስቃይ የሚቃወመው የሕዝብ ኮሚቴ፣ የሕፃናት እስርን የሚቃወሙት ወላጆች- ሃሞኬድ እና ለሰብዓዊ መብቶች የሚታገለው የሐኪሞች ቡድን ክስ አቅርቧል።

"እስራኤል የነበሩትን ከለላዎች አፍርሳለች እና ሠራተኞች በሁሉም እስር ቤቶች ስቅይት እየፈፀሙ ነው፤ በኃይል በተያዘችው ዌስት ባንክ ያሉ ፍልስጤማውያንን እና የፍልስጤም ዜጎችን ዒላማ ወዳደረ እስር ተሸጋግራለች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እነዚህን ጥሰቶች እያገዱ ቢሆንም የፍትሕ እና የአስተዳደር ሥርዓቶች ጣልቃ መግባት አልቻሉም" ሲሉ ወቅሰዋል።

ይህም በእስር ላይ የሚሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ሪፖርቱ ገልጿል። የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካለፈው ነሐሴ ወር ድረስ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ቢያንስ 94 ሞቶች ተመዝግበዋል።

በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር በበኩላቸው በተባበሩት መንግሥታት ኮሚቴ ያቀረበውን ክስ "የተዛባ መረጃ" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

አምባሳደሩ ዳንኤል ሜሮን ባለፈው ወር ለባለሙያዎች ቡድን ሲናገሩ "በሽብር ቡድን የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን እንኳን ሳይቀር ከሥነ ምግባር እሴቶቻችን እና መርሆዎቻችን ጋር በሚስማማ መልኩ ግዴታችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን" ብለዋል።

ጨምረውም የእስራኤል ተቋማት ፀረ ማሰቃየት ሕግን ሙሉ በሙሉ እንዳከበሩ እና እስራኤል በፆታዊ እና ፆታ ላይ የተመሠረተ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ተጠቅማለች የሚሉ ክሶችን ውድቅ እንዳደረገች ተናግረዋል።