መልከ ብዙው ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ ጊዜን እንዴት አሳለፈ?

የፎቶው ባለመብት, MOH
ሲገነባ ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም ክብር በዓል ነበር።
ስያሜውንም ከዚያው ነው ያገኘው።
ለድግስ እንደ መገንባቱ በርካታ የሙዚቃ ድግሶችን አስተናግዷል።
ለድግስ ብቻ የተገነባሁት በሚል ስብሰባዎች፣ አውደ ርዕዮች፣ የአስከሬን ሽኝት እና ሌላም ሌላም ከማስተናገድ አልቦዘነም።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ አዲስ ተልዕኮ ተሰጠው- የኮቪድ የህክምና እና የድንገተኛ ምላሽ ማዕከል ሆኖ አገለገለ።
ከሁለት ዓመት በፊት ኒውዮርክ፣ ጣሊያን፣ ስፔን እና ቻይና በኮቪድ-19 ቁም ስቅላቸውን ማየት ጀመሩ።
ይህ ደግሞ በመላው ዓለም ‘ፍርሃትን’ ወለደ።
“እኛ የተሻለ የህክናም አቅም ያላቸው ሲቸገሩ ስናይ . .የፈጠረው ፍርሃት ካሉን ማዕከላት በተጨማሪ ቦታ እንፈልጋለን የሚል ትምህርት ሰጠን” ያሉት የሚሊኒየም ኮቪድ ማዕከል ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ውለታው ጫኔ ናቸው።
ዶ/ር ውለታው የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው። ሰብ ስፔሻሊቲያቸው ደግሞ ሃሞት፣ ጉበት እና ቆሽት ላይ ነው። በህክምና አስተዳደርም የዓመታት ልምድ አላቸው።
አሁን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ እያገለገሉ ነው።
በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው አዲስ ፓርክ የሚሌኒየም አዳራሽን ያስተዳድራል።
ቫይረሱ ኢትዮጵያ ደረሰ ሲባል ብዙ ነገሮች ተቀየሩ።
ባለሃብቶች እና ግለሰቦች ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያግዙ ጀመር።
አዲስ ፓርክም አዳራሹን ጤና ጥበቃ እንዲጠቀምበት በነጻ ሰጠ።
ለሕክምና ያልተገነባው ሚሊኒየም አዳራሽ
ሚሊኒየም አዳራሽ ልቅ ሆኖ የተገነባ ነው። 200 ሜትር በ170 ሜትር ገደማ ስፋት አለው።
ሆኖም ለህክምና አገልግሎት የተዘጋጀ አለመሆኑ ፈተና ደቀነ።
ቅድሚያ የተሰጠው የኤሌክትሮ መካኒካል እና የንጽህና መስጫዎች ሥራ ነው።
ብዙዎቹ የህክምና ቁሳቁሶች የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ይፈልጋሉ።
“ይህን በማስተካከል ተጀመረ” የሚሉት ዶ/ር ውለታው “. . . አዳራሹ ሰፊ ስለነበር በተለያዩ ክፍሎችም ተከፋፈለ” ብለዋል።
ለዚህም አዲስ ፓርክ ለአውደ ርዕይ ሲጠቀማቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ዋሉ።
ቀሪው ደግሞ መሃንዲሶች ባደረጉት እገዛ እና ትብብር በአሉሚኒየም ተሠራ።
ቫይረሱ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለ በኋላ የቻይና የሐኪሞች ቡድን ኢትዮጵያ መጥተው ነበር።
ቻይና ስለቫይረሱ የተሻለ ልምድ ስለነበራት ነው አመጣጣቸው።
ባለሙያዎቹ የጽኑ ህሙማን ክፍል የአየር ዝውውር ‘ቬንትሌትድ መሆን አለበት’ ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቀረቡ።
ምክንያታቸው ደግሞ የአየር ዝውውሩ ካልተስተካከለ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ የሚል ነው።
ይህ ደግሞ ቫይረሱን የመካለከል ሥራውን ያደናቅፋል።
በምክረ ሃሳቡ መሠረት የአየር ዝውውሩ የተሻሻለ እንዲሆን ሆኖ ተዘጋጀ።
“ትልቁ ፈተና የነበረው የንጽህና መስጫው” ነው ይላሉ ዶ/ር ውለታው።
“ምንም አይነት የእጅ መታጠቢያ እና ውሃው የሚወጣበት መንገድ አልነበርም። ይህንን በሚፈለገው መልክ ሠርተነዋል” ሲሉ ያስታውሳሉ።
ይህ ሁሉ ወደ ስምንት ሳምንት ወስዷል።
ቫይረሱ ኢትዮጵያ መግባቱ በተገለጸ በሁለተኛው ወር ሚሊኒየም የኮቪድ ማዕከል በሩን ለህሙማን ከፈተ።
“በእኛ ሃገር አሠራር እና ካለን ልምድ በፍጥነት ጨርሰነዋል ብለን እናስባለን” ይላሉ የቀድሞው የማዕከሉ ዳይሬክተር።

የፎቶው ባለመብት, MOH
ሕሙማንን ማስተናገድ
ቀጣዩ ተልዕኮ ህሙማንን ማስተናገድ ነው።
“ከመሠረተ ልማት በተጨማሪ የባለሙያ ስልጠና እና የማብቃት ሥራ ተከናውኗል። ፍርሃት ስለነበር የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ ነበረብን። "ፍርሃቱን ተቋቁሞ ሌሎችን ማዘጋጀት አንድም ሥራ ነው፤ አንድም ፈታኝ ነው።“
“የግዢ ስርዓቱ ለድንገተኛ ነገሮች የተመቻቸ አይደለም። አሠራሩን ተከትሎ መስራት መጓተት ይፈጥራል። እንደ ማህበረሰብ፣ ባለሙያ፣ ሴክተር፣ እና ሚዲያም ፈተና ነበረብን። አልፍሎ አልፎም ከእኛ በተቃራኒ እንዲህ ሊሆን ነው የሚል ስጋትም ይወጣ ነበር። ተስፋ መቁረጥ እና ባይሳካስ የሚለው ስለሚበዛ ያንን ኃላፊነት መሸከም ከባድ ነበር” ሲሉ የነበረባቸውን ጫና ያስታውሳሉ።
“በጣም ከባድ ፈታኝ ጊዜ አሳልፈናል። ዝም ብሎም አላለፈም። ብዙ ወገኖችን አክመናል። ብዙዎችንም አጥተንበታል። ይህ ሁሉ ሲያልፍ የተማርናቸው ብዙ ነገሮች አሉ” ይላሉ ከሂደቱ ምን ተማራችሁ ሲባሉ።
የመጀመሪያው የከፋው ቢመጣስ ብሎ መዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑን ተምረናል ይላሉ።
ችግሩ ከከፋ ለመከላከል ካልሆነም በቀላሉ ለማለፍ ይረዳል በሚል።
“ሚሊኒየምን ወደ ሜክ ሺፍት ሆስፒታል ስንቀይር የነበረን ሞዴል እነ ኒው ዮርክንና ጣሊያንን ነበር። እነጣሊያን አስከሬን መቀበሪያ ጊዜ እንኳን አልነበራቸውም። ከዚህ ብዙ ተምረናል” ብለዋል።
“ሁለተኛው የተማርነው አንዳንድ ጊዜ አሳማኝ ሳይንሳዊ ሂደቶችን ጨምረን ህሙማን ያክማል ብለን እስካሰብን መተግበርን ተምረንበታል። አዳዲስ ሳይንሳዊ ነገሮችን ለመሞከረም ተምረንበታል።”
የጽኑ ህሙማን ህክምናን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑም ሌላው የተገኘው ትምህርት ነው።
የውጭ ድጋፍ ከመጠበቅም ያለውን ሃብት መጠቀምን ያስተማረ ጊዜ ሆኗል።
ታካሚዎች ሲበዙ በጋራ መሥራት ቁጥራቸው ሲቀንስ ደግሞ ወደ መደበኛ ሥራ መመለስን መማራቸውንም ይገልጻሉ።
ኮቪድ ለብዙዎች አስጨናቂ ነበር። በተለይም የመጀመሪያዎቹ ቀናት ከባድ ነበሩ። ለዶ/ር ውለታውስ?
“መጀመሪያ ያስጨንቅ ነበር። ከአቅማችን በላይ ሆኖ ነው የመጣነው የሚል ስሜትን ይፈጥራል” ሲሉ ይመልሳሉ።
በጣም አይረሴና አስደሳች የሚሉት 900 ታካሚ አስገብተው ከወር በኋላ በአንዴ ከ200 በላይ ሰዎች አገግመው የወጡበትን ቀን ነው።
“በስም የማውቃቸውን ጨምሮ በጣም ትልልቅ ሰዎች እና ተጓዳኝ ህመም ያላቸው ሰዎች አገግመው ሲወጡ በጣም የተለየ ስሜት ነው የፈጠረብኝ” ይላሉ።
'መላው ቤተሰቤ በኮሮና ተያዘ'
ዶ/ር ውለታው የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት ወደ ቤት አልተመለሱም።
ሥራቸውም አዳራቸውም ሚሌኒየም አዳራሽ ነበር።
ፍርሃቱ ስላለ ጓደኛ፣ ቤተሰብ እና ልጆች ላይ 'ምክንያት' ላለመሆን ‘ከሞትኩም ራሴን ችዬ ልሙት’ ብለው እዛው ከረሙ።
በኋላ ግን ወደ ቤት መመለስ ጀመሩ።
ሥራ ቦታ ታጥበው መኪናቸው ውስጥ ልብስ ይቀይራሉ።
ቤት አካባቢ ሲደርሱ ደግሞ ጫማ ይቀይራሉ።
ቤት ደርሰው ድጋሚ ታጥበው ልብስ ቀይረው ነበር ቤተሰቦቻቸውን የሚያገኙት።
ይህ ዑደት ለወራት ዘለቀ።
ይህ ግን መላውን ቤተሰብ ኮሮና ከመያዝ አልዳነም።
ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ላይ ቫይረሱ አልጠናም።
የእርሳቸው ግን ትንሽ ከበድ ያለ ነበር።
“ትንሽ ጠንቶብኝ ነበር። ከፍተኛ ሳል እና ለመተንፈስ ችግር እና የኦክስጂን መጠኔም ይቀንስ ነበር።”
"[ቫይረሱን]ማን እንዳመጣው አልታወቀም። ለሳምንታት ተኝቼ ነው እንደገና ወደ ሥራ የተመለስኩት” ሲሉ ያስታውሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያሳለፏቸው አስደንጋጭ ቀናት
ዶ/ር ውለታው በኮቪድ ከመያዝም በላይ አስደንጋጭ የነበሩ ቀናትን በሚሊኒየም አዳራሽ አሳልፈዋል።
ቀን ደህና ውለው ማታ ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ ህይወታቸው ያለፉ ታካሚዎች ነበሯቸው።
“ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ተነስተው አልጋቸው አጠገብ ወድቀው ህይወታቸው አለፈ የሚል ዜና የሰማንባቸው ሁለት ሦስት ቀኖች ነበሩ። እሱ በጣም አስደንጋጭ ነው። በተለይ በጣም የማስታውሰው አንድ የ26 ዓመት ወጣት ነበር። እሱን ያጣን ቀን ‘ይሄ ነገር አልገባንም ማለት ነው? የምንሠራው ሥራ በትክክልም ታካሚዎቻችንን እየደገፈ አይደለም ማለት ነው?’ የሚል ስሜት ፈጥሮብኝ ያውቃል” ይላሉ ቀዝቀዝ ባለ ድምጸት።
አስደሳች ቀናትም የትየለሌ ነበሩ።
ዶ/ር ውለታው የማይረሷቸው ጥንዶች አሉ።
ሚስት በጣም ታማ ነበር።
ባልየው ደግሞ በፍጥነት ማገገም ቻለ።
ባል አገግመሃል በል ውጣ ቢባልም ከሚስቴ ጋር ልቆይ እና ላስታማት ብሎ ጠየቀ።
የኮቪድ ታካሚዎች ያለ አስታማሚ ህክምና እንዲከታተሉ አስገድዶ ነበር።
ባልየው ተፈቀደለት። ለተወሰኑ ቀናት እዛው ቆይቶ ሚስቱን አስታመመ።
ሚስቱም ተሽሏት ለቤቷ በቃች።
ባል በአራተኛው ቀን ሚሌኒየም አዳራሽ ተመለሰ።
“ዕውቀታችሁን ጉልበታችሁን ካፈሰሳችሁ በመድሃኒት መቸገር የለባችሁም ብሎ ሁለት ሦስት ጊዜ መድኃኒት ገዝቶ ይዞ መጣ።”
“የሚገርመው ቆይቶ ቤት ተከራይቶ ሲገባ ጎረቤታሞች ሆንን [ሳቅ]።"
ተጨማሪ ህመም ያለባቸውን አንዲት እናትንም ዶ/ር ውለታው አይረሱም።
ህክምናቸውን ተከታትለው ከወጡ በኋላ የማዕከሉ ሐኪሞች የመዝናኛ ዝግጅት እንዳላቸው ይሰማሉ።
‘ያለችኝን’ ብለው 10 ሺህ ብር 'ላከሙኝ ሐኪሞች ይሁንልኝ' ብለው መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።
ከኮቪድ ጋር የነበረው ውጣ ውረድ እንደ ሃገር፣ ማህበረሰብ እና ግለሰብ በየጊዜው ተለዋውጧል።
ይህን ውጣ ውረድ ያሳለፉበት ሚሊኒየም አዳራሽ ለባለቤቱ አዲስ ፓርክ ተመልሷል።
ከምስጋና ጋር ነው የተመለሰው።
የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ ማዕከሉን ከቀናት በፊት ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስረክበዋል።
ዶ/ር ውለታው የማዕከሉ መዘጋት የተሳሳተ መልዕክት እንዳያስተላልፍ ይሰጋሉ።
“ኮቪድ አልጠፋም። አልፋ፣ ቤታ፣ ዴልታ እና ኦሚክሮን እያለ ራሱን እየቀያየረ ነው። አሁንም ስርጭቱ እና የሆስፒታል የማስገባት ቁጥሩ ብዙ ነው።“
ማዕከሉ የተዘጋው ህክምናውን በመደበኛ የህክምና ተቋማት ለማከናወን ዝግጅት በመደረጉ ነው ይላሉ።
ሌላው ደግሞ አዳራሹን ለባለቤቱ ለመመለስ እና ማስተዳደሩም ሐብትን ስለሚጠይቅ ነው።
“ኮቪድ ሰለጠፋ ግን አይደለም።“
ከኮቪድ ምን ተማሩ?
ቢቢሲ፡ ከኮቪድ ምን ተማሩ?
ዶ/ር ውለታው፡ እኔ እንደ ባለሙያ ኮቪድ ላይ በደንብ እንደሠራሁት ሌሎችም ህመሞች ላይ ብሠራ ብዬ ተምሬያለሁ። ታማሚዎቹ አስታማሚ የላቸውም። ከፈጣሪ ውጭ የሚያይ የለም። ሁሌም ፈጣሪን በሃዘኔታ ብናክም እያልኩ እጠይቅ ነበር። እንደዛም ነው ያከምነው። ሁሌም እንደዚህ ብናክም የህሙማኖቻችን እርካታ በጣም ይጨምራል። አንዱ እንደ ባለሙያ የተማርኩት እሱን ነው። እንደ ማህበረሰብ ግን በተለይም መከላከል ላይ መዘናጋት አለ። የመከላከያ መንገዶችን ባህል አድርገን ብንቀጥላቸው መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ፡ ለኮቪድ ማዕከል ከመሆኑ በፊትም ሚሊኒየም አዳራሽ ገብተው ያውቃሉ?
ዶ/ር ውለታው፡ አውቃለሁ። የሴኔት አባል ሆኜ ሁለት ዙር ተማሪዎችን አስመርቄበታልሁ። ሌሎችም የኤግዝቢዥን እና ስብሰባዎች ሲደረጉ ተሳትፌበታለሁ።
ቢቢሲ፡ አዳራሹ ለባለቤቱ ከተመለሰ በኋላ ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?
ዶ/ር ውለታው፡ አዳራሹን ባስረከብን በሦስተኛው ሳምንት ተማሪዎችን ሲያስመርቅ አይቻለሁ። ያንን ሁሉ ሥራ ሠርተን ያከምንበት ቦታ ተማሪ አስመርቋል። ዕድለኛ ሆነን ብዙዎች በቫይረሱ ቢያዙም ባለሙያ በህይወት አላጣንም። ያንን ነገር ማሰብ ደስታ አለው። ውጤታማ ሆኖ የመጨረስ ስሜት ፈጥሮብኛ። የይቻላል መንፈስም ፈጥሮብኛል። ለካ እንዲዚህ አይነት ተቋማትን በመቀያየር መጠቀም ይቻላል የሚል መንፈስ አሳድሮብኛል።












