የእግሮቻችንን ንጽህና አለመጠበቅ ከሽታ በላይ ለጤናችን ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል ያውያቃሉ?

እግር የሚያፀዱ ሰዎች ምስል

የፎቶው ባለመብት, Gorka Olmo/BBC

አንዳንድ ሰዎች እግራቸውን በየዕለቱ በአግባቡ ይታጠባሉ፤ ሌሎች ደግሞ ውሃ አፍስሰው ይተዋቸዋል።

ለቅለቅ አድርገው የሚተዋቸውም ቀላል ቁጥር የላቸውም። ለመሆኑ እግሮችዎ በበቂ ሁኔታ እየጸዱ ነው?

ወደ መታጠቢያ ክፍል ሳሙና እና ፎጣ ይዘው ሲገቡ ምናልባት አንዳንድ የአካል ክፍሎች ከሌሎች የበለጠ የመታጠብ ትኩረት ያገኙ ይሆናል።

ብብት በተደጋጋሚ በሳሙና የመጽዳት፣ የመለቅለቅ፣ የመታሸት ዕድል ማግኘቱ አይጠረጠርም።

ከታች የሚገኘው እግር ደግሞ በአንጻሩ ሲታዩ በቀላሉ የመታለፍ ዕድሉ የበዛ ነው።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት እግሮችዎ ልክ አንደሌሎች የአካል ክፍሎች ሁሉ፣ እንዲያውም በበለጠ፣ ትኩረት አግኝተው መጽዳት ያለባቸው የአካል ክፍሎች ናቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) እና የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) እግርን በየቀኑ በሳሙና እና በውሃ መታጠብን ይመክራሉ።

ለዚህ አንዱ ምክንያት ሽታን መከላከል ነው።

የእግርዎ ውስጠኛው ክፍል ከየትኛውም የሰውነት ክፍል የበለጠ 600 የላብ ዕጢዎች በቆዳዎ ካሬ ሴንቲ ሜትር ተሰልቶ ይይዛል።

ምንም እንኳን ላብ በራሱ የሚሸት ባይሆንም፣ በእግሮችዎ ውስጥ ለሚኖሩ ባክቴሪያዎች ጠቃሚ የሆኑ ምግቦች ሆኖ የሚያገለግል የጨው፣ የግሉኮስ፣ የቫይታሚን እና የአሚኖ አሲድ ቡፌ ይዟል።

እናም ከእግሮችዎ ላይ ይህንን እየተመገቡ የሚኖሩ ብዙ ባክቴሪያዎች አሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ኸል ዩኒቨርሲቲ የቁስል ፈውስ መምህር የሆኑት ሆሊ ዊልኪንሰን "እግር፣ በተለይም በእግር ጣቶች መካከል ያለው አካባቢ ውሃማ፣ እርጥበት አዘል እና ሞቃታማ ነው። ስለሆነም ለማይክሮቦች መራቢያ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።

አብዛኞቻችን እግሮቻችንን በካልሲ እና በጫማ አሽገን ስለምንውል በውስጡ ያለው እርጥበት ታምቆ በመቆየት ሁኔታውን ያባብሳል።

በሰው ልጅ የትኛውም የቆዳ ክፍል በአንድ ስኩዌር ሴንቲ ሜትር ከ10 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ።

እንደ እግር ያሉ ሞቃታማ እና እርጥብ የቆዳ ክፍሎች ደግሞ ብዙ ቁጥር ያላቸው የባክቴሪያ ዝርያዎችን በማኖር እንደ ዋና 'ሪል ስቴት' ተደርገው ይወሰዳሉ።

የእግር ሥዕል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰው ልጅ እግር ከየትኛውም የሰውነት ክፍል በተለየ የፈንገስ ብዝኃ ሕይወት መገኛ ነው ማለት ይቻላል።

ይህ ምናልባት እግርዎን ለማጽዳት ጥሩ ምክንያት ይሆንዎታል።

በአንድ ጥናት ላይ ተመራማሪዎች የ40 ፈቃደኞችን የውስጥ እግር ናሙና ወስደዋል። እግርን መታጠብ የባክቴሪያ ቁጥሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ደርሰውበታል።

በቀን ሁለት ጊዜ እግራቸውን የሚታጠቡ ሰዎች በእያንዳንዱ ካሬ ሴንቲ ሜትር ቆዳ ውስጥ ወደ 8,800 የሚጠጉ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ።

በሁለት ቀን አንዴ እግራቸውን የሚታጠቡ ሰዎች ደግሞ በካሬ ሴንቲ ሜትር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባክቴሪያዎች ተገኝተውባቸዋል።

የውስጥ እግርዎ በባክቴርያዎች ስለተሞላ ብቻ የግድ ይሸታል ወይም የሚያስጨንቅ ነገር አለ ማለት አይደለም። እንደ ሁልጊዜው፣ ቁጥሩ ብቻ ሳይሆን የባክቴሪያ ዓይነትም ወሳኝ ነው።

ለእግር ጠረን ተጠያቂ የሆኑትን ፋቲ አሲዶች በማምረት ረገድ ስታፊሎኮከስ (Staphylococcus) ወሳኝ ናቸው።

በእግሮቹ ቆዳ ላይ ያሉ የላብ ዕጢዎች የኤሌክትሮላይቶች፣ የአሚኖ አሲዶች፣ የዩሪያ እና የላቲክ አሲድ ድብልቅ ይለቅቃሉ።

የስታፊሎኮከስ ባክቴሪያ ይህንን እንደ አውደ ዓመት ድግስ ይቆጥሩታል።

በሚመገቡበት ሂደት ውስጥም አሚኖ አሲዶችን የሚረብሽ ጠረን ወዳላቸው አሚኖ አሲዶች ይለውጧቸዋል።

እዚህ ውስጥ ዋናው ጥፋተኛ ኢሶቫሌሪክ አሲድ ነው። አፍንጫ የሚረብሽ ሽታ በመፍጠር እግርዎን ያሸተዋል።

እአአ በ2014 በተደረገ አንድ ጥናት ተመራማሪዎች የ16 ግለሰቦችን የውስጥ እግር ናሙና ወስደዋል።

እናም 98.6 በመቶው በውስጥ እግራቸው ላይ የተገኙት ባክቴሪያዎች ውስጥ ስታፊሎኮከስ ናቸው።

በቀላሉ ሽታ የሚፈጥሩት ባክቴሪያዎች ከላይኛው የእግር ቆዳ ጋር ሲነጻጸሩ በውስጠኛው የእግር ክፍል ላይ በብዛት ይገኛሉ።

የእግር ሥዕል

በአጠቃላይ ጥናቱ እንዳመለከተው የእግር መጥፎ ጠረን መጠን ከጠቅላላው የስታፊሎኮከስ ብዛት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ለዚህ ነው ሳሙና እና ውሃ ሁነኛ መፍትሄ የሚሆኑት።

ሆኖም፣ እግርዎን መታጠብ የሚረዳው የእግር ጠረንን ለመከላከል ብቻ አይደለም። ጥሩ የእግር ንጽህናን በመጠበቅ ብዙ በሽታዎችን እና የእግር ችግሮችን መከላከል ይቻላል።

በኒው ዮርክ በሚገኘው የማውንት ሲናይ ሆስፒታል የቆዳ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሹዋ ዘይችነር፤ "በእግር ጣቶች መካከል ባለው ትንሽ ቦታ የተነሳ እነዚህ ስፍራዎች በተለይ ለጥቃቅን ተህዋሲያን ኢንፌክሽኖች ተጋላጭ ናቸው" ብለዋል።

"ይህ ወደ ማሳከክ፣ እብጠት እና መጥፎ ሽታ ሊያመራ ይችላል። የቆዳው መከላከያ ሲጋለጥ ደግሞ ረቂቅ ተህዋስያን ቆዳን የማጥቃት ዕድላቸው ይጨምራል። እናም ሴሉላይትስ በመባል የሚታወቁት ለስላሳ አካል ክፍሎች (ቲሹዎች) ለኢንፌክሽኖች ከፍተኛ ተጋላጭነት ይኖራቸዋል" ይላሉ።

የእግርዎን ንጽህና መጠበቅ በስታፊሎኮከስ ወይም ፒዩዶሞናስ ባክቴሪያ የሚመጡትን የቆዳ በሽታዎችን ይከላከላል።

እነዚህ ባክቴሪያዎች በቆዳዎ ላይ በተፈጥሮ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ወደ ደምዎ ውስጥ ከገቡ ግን ከባድ ኢንፌክሽን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ትንሽ የስታፊሎኮከስ ኢንፌክሽን እንኳን ወደ እብጠቶች ሊያመራ ይችላል።

ጥሩ የእግር ንጽህና ካለ የቆዳ ኢንፌክሽን ሊከሰት ቢችል እንኳን፣ እግርን አዘውትሮ መታጠብ የባክቴሪያዎችን ብዛት ይቀንሳል።

ስለዚህ በአጋጣሚ እግርዎ ላይ ጉዳት እንኳን ቢደርስ ወደ ደም ውስጥ የሚገቡት ጥቃቅን ባክቴሪያዎች ይቀንሳሉ።

በተለይም በስኳር በሽታ የሚሠቃዩ ከሆነ እግርዎን መታጠብ በጣም አስፈላጊ ነው። የስኳር በሽታ ካለብዎት ለቁስል እና ለቆዳ ኢንፌክሽን የተጋለጡ ያደርግዎታል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የስኳር ሕሙማን በእግር ቆዳቸው ላይ በርከት ያሉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ይገኛሉ።

"ከሚገባው በላይ በተደጋጋሚ መታጠብ የቆዳን ተፈጥሯዊ መከላከያው ይጎዳዋል። የቆዳን የተፈጥሮ ዘይቶችን ያስወግዳል፤ ለድርቀት እና ለእብጠት አስተዋጽኦ ያደርጋል" ይላል ዘይችነር።

ይህ ወደ ማሳከክና የቆዳ ድርቀት ያመራል።

"በተጨማሪም ከመጠን በላይ መፈግፈግ ወይም በእግር ላይ ያለውን የሞተ ቆዳ ማላቀቅ አስፈላጊ አይደለም" ይላል ዘይችነር።

"ቆዳው በሚደርስበት ጉዳት የተነሳ ድድር ያለ ቅርፊት መሳይ ነገር ይፈጥራል። ይህ ማለት የእግር ቆዳዎ ራሱን እየተከላከለ ነው። ይህንን ድድር ቆዳ ማንሳት የቆዳውን መከላከያ እንደ ማሳጣት ነው።"

በተጨማሪም ፀረ-ባክቴሪያ ሳሙናዎች የምንጠቀም ከሆነ በቆዳ ላይ ያለውን ረቂቅ ተህዋስያን ሚዛንን በማዛባት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ዝርያዎች ሊገድሉ እና አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም አቅም ያላቸውን ጠንከር ያሉ በሽታ አምጪ ተውሳኮች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ የሚል ስጋት በመኖሩ እግራችንን የምንታጠብበትን ሳሙና በመምረጥ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።