ቅኝ ግዛት፡ከነጭ ተቀላቅለው በመወለዳቸው በህገወጥ መንገድ ከጥቁር እናቶቻቸው የተነጠቁት ልጆች

የፎቶው ባለመብት, Marie-José Loshi/Metis-Be
የአራት ዓመቷ ማሪ-ሆሴ ሎሺ በቅኝ ግዛት ወቅት በቤልጂየም አገዛዝ ስር ከነበረችው ኮንጎ ከቤተሰቧ ተለይታ ተወሰደች።
600 ኪሎ ሜትር ያህል አርቀው፣ በካቶሊክ የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ በማታውቃቸው ሰዎች መካከል እንድታድግ ተደረገ።
አሁን 76 ዓመት የሆናት ማሪ-ሆሴ "ከሁሉም ነገር ተለያይተን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ቆስለናል። ልጅነታችን እና ወጣትነታችን ተሰርቋል" ብላለች።
ከሁለት ዘር በመገኘታቸው ምክንያት መንግሥት በተደራጀ ሁኔታ ከቤተሰቦቻቸው ወስዶ፣ በካቶሊክ ቤተክርስትያን በሚተዳደሩ ተቋሞች ውስጥ ካኖራቸው በሺህ ከሚቆጠሩት ልጆች መካከል አንዷ ማሪ-ሆሴ ነች።
"የጠፋሁኝ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። እያለቀስኩ ነበር… ከእናቴ ተነጥዬ ቋንቋዬን እንኳን በማይናገሩ እንግዳ ሰዎች መካከል ተጣልኩ" ብላለች።
ከበርካታ ዓመታት በኋላ እሷ እና በተመሳሳይ መልኩ በካቶሊክ ማዕከላት ውስጥ ያደጉ አራት ሴቶች የካሳ ክፍያ ለማግኘት የጀመሩትን ክስ በታሪካዊ ሁኔታ አሸንፈዋል።
ይኹን እንጂ ያለፉት ጠባሳዎች ግን አሁንም አልዳኑም።

የፎቶው ባለመብት, Michèle Hirsch
ታሪካዊ ሕጋዊ ውሳኔ
ሞኒክ ቢቱ ቢንጊ፣ ሊያ ታቫሬስ ሙጂንጋ፣ ኖኤል ቨርቤከን፣ ሲሞን ንጋሉላ እና ማሪ-ሆሴ ሎሺ የቤልጂየም መንግሥት ካሳ ክፍያ እንዲከፍላቸው እአአ በ2021 ክስ መሰረቱ።
ልጆቹ የተወለዱት ከነጭ ሰፋሪዎች እና ከጥቁር ሴቶች ነው።
በሺህዎች የሚቆጠሩት ሕጻናት በ1940ዎቹ እና 1950ዎቹ ከቤተሰቦቻቸው በግዳጅ ተነጥቀዋል።
ጉዳያቸው በቤልጂየም ፍርድ ቤት ሲታይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የታችኛው ፍርድ ቤት ጊዜው መቆየቱን በመጥቀስ የካሳ ጥያቄውን ውድቅ አደረገው።
በታህሣሥ ወር ደግሞ የብራሰልስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል የተሰጠውን ብይን ሽሮ ውሳኔ አስተላለፈ።
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአገሪቱን ድርጊት በሰው ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው ሲል ገለጸው።
"ከጥቁር እናት እና ከነጭ አባት የተወለዱ ሕጻናትን በተደራጀ መልኩ የመፈለግ እና የመንጠቅ ዕቅድ ነው" ሲል ገለጸ።
ዳኞቹ ሁኔታውን "ኢ-ሰብዓዊ የሆነ አፈና" ሲሉ ገልጸውታል።
"ይህ ውሳኔ ታሪካዊ ነው። የቤልጂየም ፍርድ ቤት በቅኝ ግዛት ወቅት ለተፈጸመ ነገር በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው በሚል ዕውቅና ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህ ለቤልጂየም ብቻ ሳይሆን ለቀድሞ ቅኝ ገዥ ኃያላን አገሮች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው" ስትል ከአምስቱ ሴቶች የአንዷ ጠበቃ የሆነችው ሚቸሌ ሂርሽ ተናግራለች።
"ፍርዱ ለእነዚህ አምስት ሴቶች ስቃይ ብቻ አይደለም ዕውቅና ሰጠው፤ የቤልጂየም መንግሥት የፈጸመውን ወንጀልም አረጋግጧል" ብላለች።
ሴቶቹ የመጀመርያ ክፍያ 50 ሺህ ዩሮ በሚል ጠይቀዋል። ምክንያት ያሉት ደግሞ በፍርዱ ከተሸነፉ ለመንግሥት ካሳ ለመክፈል ስለሚገደዱ ነው።
ለማሪ-ሆሴ ፍርዱ የገንዘብ ጉዳይ አይደለም። እንደሌሎቹ ተጎጂዎች ሁሉ የልጅነቷን አሰቃቂ ታሪክ ከልጆቿ እና ከልጅ ልጆቿ ሚስጥር አድርጋ ቆይታለች።
"በእፍረት ውስጥ ነበር የምንኖረው። ስለዚህ ዓይነት ሕይወት ለልጆቻችን መንገር አንችልም። ለጠበቆቻችን ምስጋና ይግባውና ለመመስከር ድፍረት አግኝተናል።"

የፎቶው ባለመብት, Michèle Hirsch
"በሕግ የተተዉ"
ቤልጂየም እአአ በ2019 በዲሞክራቲክ ኮንጎ በግዳጅ ከቤተሰባቸው የመለያየት ዕጣ የገጠማቸውን ወደ 20 ሺህ የሚገመቱ ሰዎችን በይፋ ይቅርታ ጠይቃለች።
ይቅርታው ለብሩንዲ እና ለሩዋንዳም ጭምር ነበር።
በቤልጂየም የቅኝ ግዛት ዘመን ፖሊሲ ምክንያት ምን ያህል የሜቲስ ወይም ከነጭ እና ከጥቁር ዘር የተገኙ ልጆች ሰለባ እንደሆኑ በትክክል ማወቅ አይቻልም ይላሉ አንትሮፖሎጂስቱ እና የቤልጂየም የመካከለኛው አፍሪካ ሮያል ሙዚየም ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ባምቢ ሴፔንስ።
"ከኮንጎ በተለየ መልኩ በሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ሕጻናቱ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ይገቡ ነበር" ብለዋል።
ይህ የሆነው በአገሮቹ ስፋት ምክንያት ነው ይላሉ ዶ/ር ሴፔንስ።
በቤልጂየም ቅኝ ግዛት ስር ከነበረችው ኮንጎ አንጻር ሁለቱ አገራት በስፋት ትንሽ ሲሆኑ በሕዝብ ቁጥር ደግሞ ከፍተኛ ናቸው።
ልጆቹን አገር ውስጥ ከማዘዋወሩ በተጨማሪ ወደ ቤልጂየም ጭምር ተወስደዋል፤ ስማቸውም ተቀይሯል። ዘመዳሞችን ከመከፋፈል ባለፈ ለአቅመ አዳም ከደረሱ በኋላም የቤልጂየም ዜግነት ሳይሰጣቸው ቆይቷል።
ዶ/ር ሴፔንስ ከቤታቸው ስለተወሰዱ ሁለት ልጆች መቼም አይዘነጉም።
በተለያዩ የቤልጂየም ክልሎች በማደጋቸው አንደኛው ደች ሌላኛው ፈረንሳይኛ ነው የሚናገሩት። ዕድሜያቸው ስልሳዎቹ ሲደርስ ነው ተፈላልገው የተገናኙት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ ባለሥልጣናቱ የሄዱበት ርቀት የቅኝ ግዛት አገዛዝን ለማጠናከር እና ለማስከበር አስፈላጊ ነበር።
"ከቅኝ ግዛት አንጻር አንዲት ጥቁር ሴት ከነጭ ልጅ ከወለደች ልጇን በሕግ እንደተወችው ይቆጠር ነበር።
ምክንያቱ ደግሞ ከነጭ እና ከጥቁር የተወለዱ ልጆች የዘር ልዩነትን ለማስጠበቅ እንቅፋት ስለሚሆኑ ነው።
ወንዶቹ ልጆች እንደ ዓመጸኞች ይታዩ ነበር። ሴቶቹ ደግሞ ገላቸው ሸጠው ወደ ማደር ይዞራሉ የሚል አስተሳሰብ ነበር" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Metis-Be
"ቅኝ ለተገዙ ህዝቦች በሙሉ ድል ነው"
ለጠበቃ ሚቸል ሂርሽ ውሳኔው ብዙ በሮች የመክፈት ዕድል አለው።
"ይህ ድል በየቦታው በቅኝ ግዛት ውስጥ ላሉ ሕዝቦች ነው" ብላለች።
"ከዚህ ፖሊሲ የተረፉ እና እንደ ደንበኞቼ ተመሳሳይ ነገር ያጋጠማቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁን ፍትህ ሊጠይቁ ይችላሉ።"
"ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሚያሳዝን ሁኔታ በሕይወት ባይኖሩም ዘሮቻቸውስ? የተጎጂዎቹ ልጆች እና የልጅ ልጆችም ፍትህ የሚጠይቁበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።"
የቤልጂየም ፓርላማ እንደ አውስትራሊያ ወይም ካናዳ ያለ ፖሊሲ እንዲያወጡ ሂርሽ ትፈልጋለች።
ሁለቱ አገራት ነባር ተወላጆች ለደረሰባቸው ጉዳት የሚሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማዘጋጀት የካሳ ፖሊሲዎችን አስተላልፈዋል።
በአውስትራሊያ እና በካናዳ በተደረጉት የካሳ ክርክሮች እንዳነሳሳት የምትናገረው ሂርሽ፣ ይህ ጉዳይ ቤልጂየምን ብቻ ሳይሆን "ሌሎች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎችም" ፖሊሲዎችን እንዲያዘጋጁ ሊገፋፋቸው እንደሚችል ታምናለች።
የሰሞኑ ብይን ከሕግ አንጻርም ብዙ ሊሠራ ይችላል ትላለች።
ይህ ጉዳይ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ተብሎ በመገለጹ ምንም ያህል ዓመታት ቢቆይም በቅኝ ገዥ መንግሥታት ለተፈጸሙ ሌሎች ወንጀሎች ካሳ ሊያስገኝ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Métis du Monde
የቀጠለው መገለል
ለአንቶኔት ኡዎንኩንዳ ከእነዚህ የቅኝ ገዥ ፖሊሲዎች የሚደርሰው መገለል እና መዘዙ አሁንም አለ።
ሜቲስ ዱ ሞንድ (የዓለም የተቀላቀሉ ሕዝቦች) ማኅበር የተመሠረተው ቤልጅየም ውስጥ ነው።
የተቋቋመው ግን በሩዋንዳ ያሉ ከነጭ እና ጥቁር የተወለዱ ሰዎችን ለመርዳት ነው። ቡድኑ አባላቱን ከቤተሰቦቻቸው ለማገናኘት ይሠራል። ወጣቶችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እና ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ገንዘብ ይሰበስባል።
ኡዎንኩንዳ ማኅበሩን ያቋቋመችበት አንደኛው ምክንያት በቅኝ ግዛት ወቅት ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ሲለያዩ በዓይኗ ስላየች እንደሆነ ተናግራለች።
"እኔ ያደግኩት በደቡብ ሩዋንዳ ውስጥ ነው። ልጆቹ ከሚገቡበት የካቶሊክ ተቋማት በአንዱ አቅራቢያ ነበር። ልጆቻቸው ወደ ቤልጂየም የተላኩ እናቶችን ታሪክ እየሰማሁ 'ለምን?' እያልኩ ማደጌን አስታውሳለሁ" ትላለች።
ልክ እንደ ብዙዎች ሁሉ ኡዎንኩንዳም የመጨረሻውን የፍርድ ቤት ውሳኔ ስትሰማ "ደስተኛ" ነበረች።
"ይህ በሮችን መክፈት አለበት። በእኔ አስተያየት ቤልጂየም ምርጫ የላትም። አንዳንድ ጥያቄዎችን ራሷን መጠየቅ መጀመር አለባት" ትላለች።
"እንደ ሴቶቹ የተሰቃዩ ብዙ ሰዎች ስላሉ እኛ እዚህ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ምክንያት የለም።"
በገጠር ለሚኖሩ እና አሁንም በመድልዎ ለሚሰቃዩ 'የሜቲስ' ሰዎች ብዙ የሚሠራ ነገር አለ ትላለች ኡዋንኩንዳ።
"ሰዎች አሁንም የአገሬውን ቋንቋ እንዴት መናገር እንደቻልኩ ይጠይቁኛል" ስትል እየሳቀች ትናገራለች።
"በሩዋንዳ ለሚገኙት ሜቲሶች ከምንነግራቸው ነገሮች አንዱ ይህ አገራችሁ ነው እና ቦታ ማግኘት አለባችሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Marie-José Loshi
የቤልጂየሙ ውሳኔ ከተሰጠ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ማሪ-ሆሴም ሃሰቧን አጋርታለች።
"ይህን ስል እንባዬ ዓይኖቼ ቢሞላም ግን ከነጭ እና ከጥቁር የተወለደን ልጆች መገለል እስከ ዛሬ ድረስ ተከትሎናል። ተቀባይነት አይሰማንም። ጥቁርም ነጭም አይደለንም። የእኛ እንደሆነ የሚሰማን ቦታ የለንም" ትላለች።
"አሁን አንገታችንን ቀና አድርገን እንራመዳለን። ከእኛ ጋር ለረዥም ጊዜ የያዝነው ሚስጥራችን በአደባባይ ወጥቷል። ሰዎች መሳለቃቸው ወይም ማጨብጨባቸው ምንም ለውጥ አያመጣም። ማድረግ ያለብንን አድርገናል። ምክንያቱም ሸክሙ በጣም ከባድ ስለነበር ነው።"












