ወጣት ቱርካዊያን ተማሪዎች የኤርዶዋን አገዛዝ በቃን ብለው ጎዳና የወጡት ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት የኢስታንቡል ከንቲባ የሆኑት ኢማሞግሉ መታሰራቸውን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ቢያንስ 2 ሺህ ያክል ሰዎች ታስረዋል።
አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎች ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።
ምንም እንኳን በሀገሪቱ ትልቋ ከተማ በሆነችው ኢስታንቡል ውስጥ ተቃውሞ ማድረግ ቢከለከልም ተማሪዎች ግን ይህ እግድ ሳያቆማቸው በየቀኑ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
የሚገናኙት የከተማዋ ንዑስ አደባባይ በሆነው ሳራቼን ፓርክ ነው።
አመሻሹን ተገናኝተው የሚያሰሙት ተቃውሞ በፖሊስ አስለቃሽ ጭስ፣ የፕላስቲክ ጥይት እና ግፊት ያለው ውሀ የታጀበ ነው።
የኢማሞግሉ ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ አሊያም ሲኤችፒ ከሰሞኑ ስትራቴጂውን የቀየረ ይመስላል። በአደባባይ መሰባሰቡ እንደማያዋጣ ለደጋፊዎቹ አሳውቋል።
በምትኩ የፓርቲው ደጋፊዎች ከቤታቸው ሆነው በማጨብጨብ፣ የመኪና ጥሩንባ በማሰማት እና በመስኮታቸው በኩል ባንዲራ በማውለብለብ ተቃውሞቸውን እንዲገልፁ ጠይቋል።
ፓርቲው ቅዳሜ ታላቅ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ አቅዷል። ምንም እንኳ በኢስታንቡል የተቃውሞ ሰልፍ ቢከለከልም ቅስቀሳ ማድረግ ግን ይቻላል።
ተማሪዎቹ ግን ምንም የሚያግዳቸው አይመስልም።
መሐል ኢስታንቡል ማካ ፓርክ የተሰባሰቡ ተማሪዎች ማንነታቸው እንዳይለይ የፊት ጭምብል አጥልቀዋል። ፎቶ መነሳት አይፈልጉም። ለሚያናግራቸው ሰውም ትክክለኛ ማንነታቸውን አይገልጡም።
"ሕልማችን ተቃውሞ ስናሰማ ፊታችንን የማንሸፍንበት ሀገር እንደትኖረን ነው" ሲል አንድ ተማሪ ለቢቢሲ ይናገራል።
ፕሬዝደንት ኤርዶዋን ጭምብል ያጠለቁ ሰልፈኞችን "አሸባሪዎች ናቸው" ሲል ገልፀዋቸዋል።
'የተመረጠ ፍትሕ'
ኢማሞግሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በአውሮፓውኑ መጋቢት 19 ነው። በይፋ የቀረረባቸው ክስ ሙስና ሰርተዋል ይላል።
የሲኤችፒ ፓርቲ ዕጩ ሆነው በተመረጡ ቀን ነው ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሒደቱ እስኪጀመር ድረስ በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ የተደረገው።
ተቃውሚ ፓርቲው ኢማሞግሉ ላይ የቀረበው ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው ብሎ የከንቲባው መታሰር "መፈንቅለ መንግሥት ነው" ሲል ይከሳል። ኤርዶዋን ይህን ወቀሳ አይቀበሉትም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳ በማካ ፓርክ ለተቃውሞ የወጡ ተማሪዎች ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ቢገልፁም "መብት፣ ሕግ እና ፍትሕ" የተሰኘውን የተቃውሚ ፓርቲ መፈክር ሲያሰሙ ታይተዋል።
"ያለንበት ሁኔታ ተመልከቱት እስቲ" የአንድ ተማሪ ድምፅ ነው። "ሰዎች ፍርድ ቤት እንኳ ሳይቀርቡ ነው ለእስር እየተዳረጉ ያሉት።"
ሌላኛው ተማሪ ደግሞ የተመረጠ ፍትሕ አለ ሲል ያማራል።
"ይሄ የኢማሞግሉ መታሰር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሌሎች [በሙስና የተጠረጠሩ] ለምን ምርመራ አይደረግባቸውም" ይላል።
አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኛ አይደለም ባይ ናቸው።
"ፍርድ ቤት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን እንፈልጋለን" የሚሉ ተማሪዎች አሉ። የቱርክ መንግሥት ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ በሆነ መንገድ ነው የሚያገለግሉት የሚል ምላሽ አለው።
ከፍርድ ቤት ገለልተኛነት በተጨማሪ ምጣኔ ሀብታዊ አለመረጋጋት፣ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መጨመር እና የወደፊት ዕጣቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አለማወቃቸው ተማሪዎቹ አደባባይ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
ኢማሞግሉ ከዩኒቨርሲቲ ያገኙት ዲፕሎማ እንዲሰረዝ መደረጉ ተሰምቷል። ይህ ማለት ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆነው መቅረብ አይችሉም ማለት ነው።
"የእሱን ዲፕሎማ ነጠቁ ማለት የኛንም ላለመንጠቃቸው ምንም ማረጋገጫ የለውም ማለት ነው" ሲል አንድ ተማሪ ይጠይቃል።
ምንም እንኳ በቱርክ ያለው ሁኔታ አስተማማኝ ባይሆንም ሁሉም ወጣቶች ሀገሪቱን ጥለው ለመሄድ ፈቃደኛ አይደሉም።
"አብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቼ ወደ ውጭ ሀገር ሄደዋል። እኔ ግን መውጣት አልፈልግም። ወጣት ቱርካዊ ነኝ። ወደፊት መኖር የምፈልገው እዚህ ነው።"
ነፃ ንቅናቄ
ሲኤችፒ ፓርቲ ማታ ማታ በሳራቼን ፓርክ እንዲቋረጥ ቢያደርግም ተቃውሞው ግን የተቋረጠ አይመስልም።
ፓርቲው በአዳዲስ መሰባሰቢያ ቦታዎች ቅስቀሳ ለማድረግ ሐሳብ እንዳለው አሳውቋል። ወጣቶቹ ግን አደባባይ ወጥተው ሰልፍ ማድረግ ይሻሉ።
"ለኢማሞግሉ ስንል ብቻ አይደለም ወደ አደባባይ የወጣነው። ለዲሞክራሲም ጭምር ነው። ተቃውሞ የምንወጣባቸው በርካታ አደባባዮች አሉን" የአንድ ተማሪ አስተያየት ነው።
ሌላ ተማሪ ደግሞ ፓርቲው ስትራቴጂውን መቀየሩን ተቃውሞ ንቅናቄው ገለልተኛ እንዲሆን ይጠይቃል።
"የፓርቲው መሪ የሚሉት ነገር እኛን አይመለከተንም። የራሳችንን ውሳኔ መወሰን እንችላለን። በነፃ ንቅናቄ ሁኔታዎችን መቀየር እንችላለን። የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አያስፈልገንም።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተማሪዎቹ ጎዳና በመውጣት እና ምጣኔ ሀብታዊ አድማ በመምታት በተቃውሟቸው ለመቀጠል ቆርጠዋል።
ሕዝቡ "ፖለቲካዊ ዕውቀት እንዲጨብጥ" እንሻለን የሚሉት ተማሪዎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እውነታውን ሸሽገዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
"ከሚድያ የምናገኘው ዜና ከመንግሥት እውቅና የተሰጠው ነው። መንገድ ላይ ያለውን ስንመለከት ግን እውነታው ሌላ ነው። ፖሊስ ምን ኃይል እየተጠቀመ እንዳለ እና ተቃዋሚዎቹ ተንኳሽ ናቸው ወይ የሚለውን መመልከት ይቻላል።"
የቱርክ ሚዲያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የተቃውሞው ዘገባ ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር አጥብቋል። በያዝነው ሳምንት መባቻ ከተቃውሚ ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ሊታገዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
ተቃውሞን ሲዘግብ የነበረውን የቢቢሲ ሪፖርተር ማርክ ሎዌን "የሕዝብ ሰላም ይበጠብጣል" በማለት ቱርክ ከሃገር እንዲወጣ ማድረጓን ቢቢሲ ተናግሯል።
ሎዌን ኢስታንቡል ከሚገኝ ሆቴል ተወስዶ እንደነበር የቢቢሲ ኒውስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዴቦራህ ተርነስ አሳውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የታሰሩ እስኪፈቱ ድረስ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንደማይመለሱ ቃል ገብተዋል።
ተማሪዎች በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞ እንዲፋፋም ጥሪ ያቀርባሉ።
"ሁሉም ሠራተኞች፣ ፕሮፌሽናል ድርጅቶች እንዲቀላቀሉን ጥሪ እናቀርባለን። ሕዝባዊ ተቃውሞ ያሻል። ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ እንዲል ማድረግ አለብን" ይላል አንድ ተማሪ።












